1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስአፍሪቃ

የዘረመል ማሻሻያ የአይን ህክምና እና ያሳደረው ተስፋ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 30 2016

የሰው ልጅ በተፈጥሮ ከተጎናጸፋቸው የስሜት ህዋሳት ስስ የሆነው እና በዚያው ልክ ለተለያዩ አደጋዎች በእጅጉ ተጋላጭ የሆነው አይን እንደማንኛውም የሰውነት ክፍል ሊታከም ይችላል። አሁን አሁን ያለንበት የቴክኖሎጂ ዘመን ልክ እንደሌሎች የህክምና ዘርፎች ሁሉ ለአይነስውርነት መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ የምርምር ውጤቶች ይፋ እየሆኑ ነው ።

https://p.dw.com/p/4fcPe
Symbolbild Gentechnik
ምስል focalpoint/IMAGO

አዲሱ የዘረ መል ማሻሻያ ህክምና አይነስውርነትን እስከመጨረሻው ያሰናብት ይሆን?

የዘረመል ማሻሻያ የአይን ህክምና እና ያሳደረው ተስፋ 

አይነስውርነት በውልደት አልያ በዕድገት ሊከሰት የሚችል በተለያየ ደረጃ የእይታ መጠን መጋረድ አልያም ሙሉ በሙሉ ማየት እስከአለመቻል ሊደርስ ይችላል።

የሰው ልጅ በተፈጥሮ ከተጎናጸፋቸው የስሜት ህዋሳት ስስ የሆነው እና በዚያው ልክ ለተለያዩ አደጋዎች  በእጅጉ ተጋላጭ የሆነው አይን እንደማንኛውም የሰውነት ክፍል ሊታከም ይችላል። አሁን አሁን ያለንበት የቴክኖሎጂ ዘመን ልክ እንደሌሎች የህክምና ዘርፎች ሁሉ ለአይነስውርነት መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ የምርምር ውጤቶች ይፋ እየሆኑ ነው ። 

 በመላው ዓለም 38 ሚሊዮን ብርሃናቸውን ያጡ ወይም አይነስውራን ሰዎች እንደሚገኙ የዓለም ጤና ድርጅት ይፋ ያደረገው አንድ ጥናታዊ ጽሁፍ ያመለክታል። ጥናቱ እንደሚለው ወደ 110 ሚሊዮን የሚጠጉ በተለያየ የዕድሜ ደረጃ የሚገኙ ሰዎች ደግሞ ብርሃናቸውን ወደ ማጣት አልያም ወደ አይነስውርነት እያመሩ ይገኛሉ።

የ2013 ዓ.ም ሳይንሳዊ ግኝቶች ቅኝት በከፊል

የአይን ብርሃንን ሊያሳጡ የሚችሉ የተለያዩ በሽታዎች ቢኖሩም በዓለም አቀፍ ደረጃ ስማቸው ጎልቶ የሚታወቀው እና በበርካታ ሃገራት ጉዳት በማድረስ የሚታወቁት የተወሰኑት ናቸው ። ከእነዚህም ውስጥ ትራኮማ ግላኮማ ፣ ኦንኮ ሰርኪያሲስ እና ዜሮፍታልሚያ ተጠቃሾች ናቸው። ኢትዮጵያ በዓለም ላይ የአይን አጠባበቅ ከከፋባቸው እና በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ ሃገራት እንዷ እንደ ሆነች ነው በአይነስውርነት ላይ ጥናት ያደረገ አንድ ሃገራዊ መረጃ የሚያመለክተው ። ኦርቢስ የተሰኘው ዓለማቀፍ የግብረሰናይ ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው 1.6 በመቶ ኢትዮጵያውያን ከአይነስውርነት ጋር አብረው ሲኖሩ ፤ 3.7 በመቶ የሚሆኑቱ ደግሞ አይነስውርነት በተጋለጠ እይታ ውስጥ ይኖራሉ።

ምስለ ዘረመል
የአይን ብርሃንን ሊያሳጡ የሚችሉ የተለያዩ በሽታዎች ቢኖሩም በዓለም አቀፍ ደረጃ ስማቸው ጎልቶ የሚታወቀው እና በበርካታ ሃገራት ጉዳት በማድረስ የሚታወቁት የተወሰኑት ናቸው ።ምስል Science Photo Library/IMAGO

ለአይነ ስውርነት የሚዳርጉ በሽታዎች የትኞቹ ናቸው ?

ዶ/ር ኩመሌ ቶሎሳ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የአይን ህክምና ስፔሻሊስት እና በዩኒቨርሲቲው ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው ። ኢትዮጵዩane ጨምሮ በዓለማቀፍ ደረጃ በርካቶችን ለአይነስውርነት የሚዳርጉ የተለያዩ በሽታዎች ቢኖሩም የአይን ሞራ ግርዶሽ ቀዳሚ ተጠቃሽ ነው ይላሉ ።

«ከሁለቱ የተሻለ ያያል ተብሎ የሚታሰበው ዓይን ከሶስት ሜትር በታች ካየ አንድ ሰው አይነስውር ነው እንላለን። ይህ የኦለም የጤና ድርጅት መስፈርት ነው። ይህን ሊያመጡ የሚችሉ ደግሞ በዋናነት በዓለም ላይ ትልቁ ምክንያት ከ50 በመቶ በላይ አይነስውርነትን የሚያመጣው የአይን ሞራ ግርዶሽ ነው። የአይን ሞራ ግርዶሽ ደግሞ ቀለል ባለ ኦፕሬሽን መስተካከል ይችላል።»

በእርግጥ ነው በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰቱ እና በሂደት ለዓይነስውርነት ሊዳርጉ የሚችሉ በሽታዎች ከቀላል እስከ ቀዶ ህክምና በሚደርስ ህክምና መፍትሄ ሊያገኙ እንደሚችሉ መረዳት ይቻላል።

በጀርመን ድርጅት የሚደገፈዉ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ታካሚዎች

በመግቢያችን ላይ ስለጠቀስነው እና በውልደትም ይሁን በዕድገት የዓይናቸውን ብርሃን ላጡ ሰዎች ዘረ መል ህክምናን ተግባራዊ ለማድረግ እየተደረጉ የነበሩ የምርምር ውጤቶች ተስፋ እየታየባቸው ነው ።

ዶ/ር ኩመሌ ቶሎሳ
በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰቱ እና በሂደት ለዓይነስውርነት ሊዳርጉ የሚችሉ በሽታዎች ከቀላል እስከ ቀዶ ህክምና በሚደርስ ህክምና መፍትሄ ሊያገኙ እንደሚችሉ መረዳት ይቻላል።ምስል Silte zone culture office Werabe/Ethiopia

አዲሱ ምርምር እና ውጤቱ 

ከሰሞኑ ይፋ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚመለክተው የእንግሊዘኛ ምህጻሩ CRISPR-Cas9 በመጠቀም እና በተፈጥrሯቸው አይነስውር የሆኑ አዋቂ እና ልጆች የአይን ብርሃናቸውን መመለስ የሚያስችል ውጤት አግኝተዋል። እንደተመራማሪዎቹ ምርምሩ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ የችግሩ ተጠቂ የሆኑ ሰዎችን ለመፈወስ ተስፋ ሰንቀዋል።

በአሜሪካው የሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ት/ቤት ተመራማሪዎች እንደሚሉት በዚህ በዘረመል ህክምና ጥናት ውስጥ ከተካተቱ 14 ሰዎች ውስጥ አስራ አንዱ የማየት  ችሎታቸው ተመልሶላቸዋል።

እንደተመራማሪዎቹ ጥናቱ በአይነ ስውርነት የተወለዱ ህጻናትን ለማከም የዘረመል ህክምናን  በመጠቀም የመጀመሪያው ነው  ።

የይን ሀኪሟ ዶ/ር ኩመሌ በዘረመል ህክምና የዓይን ብርሃን ለመመለስ የሚደረገውን የምርምር ስራ ይከታተላሉ ፤ አይነስውርነትን ከሚያስከትሉ እና ለመዳን የመነመነ ዕድል ያላቸውን የአይን በሽታዎችን በተለያየ መንገድ በሚሰጡ ህክምናዎች ፈውስ ለማምጣት ተስፋ ተጥሎባቸዋል።

ዶ/ር ኩመሌ ቶሎሳ
ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት ጥናቱ በአይነ ስውርነት የተወለዱ ህጻናትን ለማከም የዘረመል ህክምናን  በመጠቀም የመጀመሪያው ነው ምስል Silte zone culture office Werabe/Ethiopia

« የአይናችን የእይታ ዙፋኑን እንደመጃጀት እና እንደ መሸብሸብ አይነት ነገር ነው፤ ይህም እንግዲህ አንዴ አይነስውርነትን ካስከተለ መልሶ ማዳን አይቻልም ነበር ፤ አሁን ግን እንደነዚህ አይነት በሽታዎች ጂን ቴራፒ የሚባል ጥናት ላይ ነው ያለው ፤ በዚህም የነርቩን ጂን ረቲና የሚባለውን የአይናችንን ክፍል ዘረመሉን የሚቀይር መድሃኒት ይሰጣቸዋል ማለት ነው ።»

አዲሱ የምርምር ዉጤት ምን ያህል ተደራሽ ይሆን?

በእርግጥ ነው ቴክኖሎጂ ወለድ የህክምና ጥናት እና የምርምር ስራዎች በዓለማችን ላይ ለበርካታ የጤና ጠንቅ በሽታዎች መልስ ሰጥተዋል፤ የሰውን ልጅ ከተጋረጠበት የህልውና ስጋት ታድገውታልም። በዚያው ልክ ግን አዳዲስ የፈውስ የጥናት እና የምርምር ስራ ዉጤቶች በፍጥነት እና በርካሽ ዋጋ ሁሉምጋ ይደርሳሉ ብሎ መጠበቅም የዋህነት ነው። ዛሬ ዛሬ ፈውስ የተገኘላቸው ነገር ግን ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቁ የህክምና አይነቶች ለሃብታሞች ብቻ የተተው የሚመስሉበት ሁኔታም በተደጋጋሚ ሲታዩ ቆይተዋል። አሁን የምርምር ዉጤቱ ተስፋ የተጣለበት አይነስውርነትን እስከወዲያኛው ይሸኛል የተባለለት ህክምናም እንዲሁ በቀላሉ የሚገኝ ስለመሆኑ ያጠራጥራል። ዶ/ር ኩመሌም ይህኑንኑ ሃሳብ ይጋራሉ።

ተስፋ ሰጭው የወባ በሽታ መከላከያ ክትባት

«በጣም አስቸጋሪ ነው በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያን ስናስብ የጤና ስረዓቱ በጣም ጠንካራ ነው። ዝም ተብሎ ማንኛውም ሰው ገብቶ የሚልበት አይደለም ። እንደገና ደግሞ ትኩረታችን እንደኢትዮጵያ የአይን ህክምና ላይ አይደለም። አሁን ትኩረታችን እናቶችን ማዳን፤ ህጻናትን ማዳን ማትረፍ የሚል ነገር ነው እንደ ሀገር ያለው ፤ ከትኩረት እጥረት የተነሳ ፣ከማጣት የተነሳ ይዘገያል የሚል ፍርሃት አለኝ ፤ »

የሆነ ሆኖ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተደረጉ ያሉ የአይን ህክምና እና ተጨማሪ የፈውስ ምርምሮች ተስፋ ሰጭ ናቸው ። የአሜሪካ ተመራማሪዎች ይፋ ያደረጉት የዘረ መል ህክምናም የአይን ብርሃናቸውን ያጡ ሰዎች ደረጃ በደረጃ ማየት እንዲችሉ አድርጓል። የጥናት እና ምርምሩን ዉጤት ይፋ ያደረገው ዘገባው እንደሚያመለክተው  በጥናቱ ውስጥ ከተካተቱ 14 ሰዎች ከሶስቱ በቀር አስራ አንዱ ሰዎች ህክምናውን ከወሰዱ በኋላ የማየት ችሎታቸው እጅጉን ተሻሽሎላቸዋል። እንዲያውም ከእነዚህ ውስጥ ስድስቱ ቁሶችን እስከ መለየት እና በቻርት ላይ የሰፈሩ ፊደሎችን እስከማንበብም ደርሰዋል። ይህ በእርግጥ በምርምሩ ብሎም በህክምናዊ ዘርፍ አመርቂ እርምጃ ነው። የምርምሩ ሌላው መልካም ዜና ደግሞ ዘረመልን በማሻሻል የሚሰጠው ህክምና ፤ ህክምናውን በሚወስደው ሰው ላይ ምንም አይነት የጎንዮሽ ጉዳት አለማስከተሉ ነው።

ምስለ ዘረ መል ህክምና
የአሜሪካ ተመራማሪዎች ይፋ ያደረጉት የዘረ መል ህክምናም የአይን ብርሃናቸውን ያጡ ሰዎች ደረጃ በደረጃ ማየት እንዲችሉ አድርጓል። ምስል Gregor Fischer/dpa/picture alliance

በአሜሪካ ፣ብሪታኒያ እና አውሮጳ ህብረት ውስጥ ከ200 ሰዎች በላይ CRISPR በተሰኘው የዘር መል ማሻሻያ ቴክኖሎጂ ህክምና እንደወሰዱ መረጃዎች ያመለክታሉ ። ነገር ግን እስካሁን ድረስ  በክሊኒክ ደረጃ ለመሞከር አንዱ ብቻ ፈቃድ ማግኘቱ ነው የተነገረው።

ሳይንቲስቶች ግን አንድ ነገር ይላሉ ። የዘረ መል ማሻሻያ ህክምና ዘርፉን አንድ እርምጃ እያራመደው ነው። ይህ ደግሞ ህሙማንን በአስተማማኝ ሁኔታ መርዳት ብቻ ሳይሆን በተለያዩ በሽታዎች ለሚሰቃዩቱ ጭምር መፍትሄ ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ተስፋ አላቸው።

ታምራት ዲንሳ 

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሄር