1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተስፋ ሰጭው የወባ በሽታ መከላከያ ክትባት

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 21 2013

የወባ በሽታ በየአመቱ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት የሚዳርግ የጤና ችግር መሆኑን የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል። ለዚህ በሽታ ውጤታማ ክትባት ለማግኘት በርካታ ምርምር ሲደረግ የቆየ ሲሆን፤ የኦክስፎርድ ተመራማሪዎች ሰሞኑን በአፍሪቃ ባደረጉት የመጀመሪያ ደረጃ የክትባት ሙከራ አበረታች ውጤት መገኘቱን ገልፀዋል።

https://p.dw.com/p/3sgZp
Medizin Forschung l Weltweit erste Malaria-Impfkampagne l Impfstoff
ምስል picture alliance/dpa/K.-J. Hildenbrand

ተሰፋ ሰጭው የወባ በሽታ መከለከያ ክትባት


 የወባ በሽታ  የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ለህይወት አስጊ ብሎ ካስቀመጣቸው በተውሳክ አማካኝነት ከሚተላለፉ በሽታዎች ውስጥ አንዱ ነው።ይህንን በሽታ  በቅድመ ጥንቃቄ  መከላከል፤ እንዲሁም በበሽታው ከተያዙ በኋላ በህከምና ማዳን የሚቻል ቢሆንም፤ በበሽታው ሳቢያ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ግን ቀላል አይደለም።የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በጎርጎሪያኑ 2019 ዓ/ም ብቻ በዓለም ላይ 229 ሚሊዮን ሰዎች በወባ በሽታ ተይዘዋል። 409 ሺህ ሰዎች ደግሞ ለሞት ተዳርገዋል። በሽታው በተለይም ከ5 ዓመት በታች ባሉ ህፃናትላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያድረስ  ነው። 
ይህንን የጤና ችግር የሚፈታ ተስፋ ሰጪ የመከላከያ ክትባት በሙከራ ላይ መሆኑን ተመራማሪዎች በመግለፅ ላይ ናቸው።
ሙከራው በአፍሪቃዊቷ ሀገር ቡርኪናፋሶ የተካሄደ ሲሆን፤በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት የነጠቀውን በሽታ ለመዋጋት ተስፋ ሰጭ ውጤት አሳይቷል ተብሏል።«ላንሴት» የተባለው የህክምና መጽሔት ሰሞኑን ያወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው በአሁኑ ወቅት በሙከራ ላይ የሚገኘውና  « R21/Matrix-M» በመባል የሚጠራው የወባ በሽታ መከላከያ ክትባት ለ12 ወራት በተደረገ የሙከራ ክትትል  77 በመቶ ውጤታማ ነው ተብሏል ፡፡ የወባ በሽታ ተመራማሪና በእንግሊዝ ካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት ጁሊያን ራይነር የሙከራ ሂደቱን« አበረታች ነው» ይሉታል ፡፡
«በጣም የሚያበረታታ ነው።ሙከራው የወባ በሽታ አሁንም ቢሆን አስቸኳይና አዳዲስ መፍትሄዎች የሚያስፈልጉት  ትልቅ ችግር መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው።  ቅድመ  ሙከራ ደረጃ ላይ በመሆኑ፤ ከዚህ ሙከራ የተገኘው መረጃ በጣም አበረታች  ነው ።ነገር ግን መረጃው የተሰበሰበው አነስተኛ ቁጥር ካላቸው ልጆች  ስለሆነ፤ በሌሎች  አካባቢዎች  ሰፋ ያሉ ሙከራዎችን ለማካሄድ ግልፅ ማረጋገጫ የሚሰጥ ነው።»
ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት የዓለም የጤና ድርጅት የወባ በሽታ ክትባት ቴክኖሎጅን  በተመለከተ ያስቀመጠው ዝቅተኛ  የውጤታማነት ግብ 75 በመቶ ነው። ከዚህ አንፃር ይህ ክትባት 77 በመቶ ውጤታማ በመሆን  የድርጅቱን ግብ ያሳካ የመጀመሪያው የወባ በሽታ መከላከያ ክትባት ነው ፡፡
በዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት የማላዊ የወባ ክትባት የሙከራ መርሀ ግብር የቴክኒክ ሀላፊ ዶክተር ራንዲ ሙንግዊራ እንዳሉት ኮቪድ-19 በጤና ስርዓቱ ላይ ጫና እያዳሳደረ ባለበት ወቅት  የህፃናትን ህመሞች የሚቀንሱ ፣ ህይወትን የሚያድኑ እና በጤናው ዘርፍ ያለውን ጫና ለማቃለል የሚረዱ እነዚህን መሰል  የክትባት ሙከራዎች መቀጠላቸው እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ገልፀዋል። 

Mücke, Blut saugend
ምስል picture-alliance/dpa/P. Pleul

በአዲሱ ክትባት የመጀመሪያ ዙር ሙከራ  ከ5-17 ወራት ዕድሜ ያላቸውን 450 ሕፃናትን በሶስት ቡድን በመክፈል  ያሳተፈ ሲሆን፤ከውጤታማነቱ ባሻገር በሙከራው ምንም አይነት ከባድ የጎንዮሽ ጉዳት አለመታየቱንም ተመራማሪዎቹ ገልፀዋል። 
ተመራማሪዎቹ በቀጣይ  ከ5-36 ወር እድሜ ባላቸው  4,800  ሕፃናትን  በማሳተፍ በክትባቱ  ደህንነት እና ውጤታማነት ላይ በአራት የአፍሪካ ሀገሮች  ላይ ሰፋ ያለ ሙከራ ለማድረግም አቅደዋል። 
ሙከራው በህጻናት ላይ እንዲያተኩር የተደረገው ህፃናት ልጆች ለወባ በሽታ በጣም ተጋላጭ  በመሆናቸው ሲሆን፤በ2019 ዓ/ም ከተመዘገበው ከ400 ሺህ በላይ የሞት መጠን ውስጥ 67 በመቶው  ከአምስት አመት በታች በሚገኙ  ህፃናት ልጆች ላይ የተከሰተ መሆኑን የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል።
ሬይነር እንደሚሉት በህፃናት ሊጆች ላይ በሽታው ቢበረታም።  በወባ በሽታ በተደጋጋሚ ተይዘው በህይወት የተረፉ አዋቂዎች  ግን በተወሰነ ደረጃ የመከላከል አቅምን ስለሚያዳብሩ በሽታው ላይጠናባቸው ይችላል። 
« ወባ በበዛበት አካባቢ ካደክ እና  በተደጋጋሚ በበሽታው ከተያዝክ  በተወሰነ ደረጃ በተፈጥሮ  የመከላከል አቅምን ማዳበር ትችላለህ። ያ ማለት ግን ሙሉ በሙሉ የበሽታ መከላከል አቅም አለህ ማለት አይደለም። ወባ በጭራሽ በድጋሜ አይዝህም ማለትም አይደለም። ነገር ግን በሽታው ከባድ ምልክቶች እና ከባድ ተጽዕኖዎች ላያስከትል ይችላል ።ለዚህም  ነው በአብዛኛው ከባድ ህመም በትናንሽ ሕፃናት ላይ የሚከሰተው። ምክንያቱም ከብዙ ጊዜ በፊት በሽታውን ተቋቁመው በሕይወት የተረፉትና በእድሜ የገፉት ያንን ተፈጥሮአዊ የመከላከል አቅም ያዳበሩ ናቸው።» 

Fiebermuecke, Stechmuecke, Anopheles spec., malaria mosquitoe
ምስል picture alliance/dpa/blickwinkel/Hecker/Sauer

የወባ  በሽታ «አኖፊለስ» በተባለች ሴት ትንኝ ንክሻ አማካኝነት ወደ ሰዎች በሚተላለፍ ጥገኛ ተውሳክ የሚከሰት በሽታ ነው። በሽታውን የሚያስከትሉ  የተውሳክ ዝርያዎች አምስት ሲሆኑ፤ ከእነዚህም ውስጥ «ፕላዝሞዲየም ፋንሲፈርም»እና «ፕላዝሞዲየም ቫይቫክስ» የተባሉት ሁለት ዝርያዎች በሰዎች ጤና ላይ ትልቅ ጉዳት የሚያስከትሉ  ናቸው- ፡፡
በሽታው ትኩሳት ፣ ራስ ምታት ፣ የጨጓራና የአንጀት ችግርን ፣ የጀርባ ህመም ፣ ሳል፣  ማዞር ና ግራ መጋባትን የመሳሰሉ የነርብ ህመሞች ጨምሮ የተለያዩ ምልክቶችን ያሳያል። ተገቢ ህክምና እና ክትትል ካልተደረገም ታማሚውን ለሞት የሚያበቃ በሽታ ነው።
ይህ በሽታ አፍሪቃን በተለይም ከስሃራ በታች ያሉ የአፍሪቃ ሀገሮችን በእጅጉ የሚያጠቃ ሲሆን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ  በበሽታው ከተያዙም ሆነ ህይወታቸውን ካጡ  ሰዎች ውስጥ 94 በመቶ የሚሆነው የተመዘገበው  በአፍሪቃ ነው ።
በኢትዮጵያም ከሌሎች ከቀጠናው ሀገራት ጋር ሲነጻፀር ዝቅተኛ ነው ቢባልም፤በ2019 ዓ/ም በወጣ መረጃ መሰረት 60 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ለበሽታው የተጋለጠ ነው።
በሽታው  በአብዛኛው የሚከሰተው ዋናውን የክረምት ዝናብ ተከትሎ በመኸር ወይም በምርት መሰብሰቢያ ወቅት በመሆኑ  ሰዎችን ለህመምና ለሞት ከመዳረጉ ባሻገር   የግብርና ሥራውን በማስተጓጎል በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖም  ከፍተኛ ነው። 

Infografik Häufigkeit des Auftretens resistenter Mücken Deutsch

ያም ሆኖ በሰፊው ጥቅም ላይ የሚውል ክትባት ባለመኖሩ  በሽታው  ከፍተኛ የህብረተሰብ የጤና ችግር ሆኖ ቀጥሏል። በሌላ በኩል በሽታው መድኃኒቶችን እየተለማመደ መምጣቱም ሌላው ፈተና መሆኑን ተመራማሪው ጁሊያን ሬይነር ገልፀዋል።

"ተውሳኩ በሽታ የመከላከል አቅም ምላሽን ለማምለጥ እጅግ የረቀቀ ዘዴ አለው። የወባ ትንኝ በትንኞች እና በሰዎች መካከል የሚዘዋወር ውስብስብ የሕይወት ዑደት አለው ፣ ነገር ግን ወደ ሰውነት በሚገባበት ጊዜ  በደም ውስጥ ነው የሚቆየው። ይህ ማለት ሁል ጊዜ  በሽታ የመከላከል አቅምህ ተጋላጭ ነው ማለት ነው።ስለዚህ የሰውነት በሽታ የመከላከል ስርዓትን ቀስ በቀስ የማዳከም ስልት ነው።ያ ደግሞ የመከላከያ ክትባት ማግኘትንም አስቸጋሪ ያደርገዋል።»

እንደ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት መረጃ እስከአሁን የወባ በሽታን የሚከላከል   «RTS ,S» የተባለ አንድ ክትባት  ብቻ ሲሆን ውጤታማነቱም 50 በመቶ ብቻ ነው።
ይህ ክትባት ከ 5 እስከ 17 ወራት ዕድሜ ላላቸው ሕፃናት  4 የክትባት መጠን ከተሰጡ  ከ4 ዓመት ክትትል በኋላ 39 በመቶ በወባ በሽታ የመያዝ ዕድልን ይቀንሳል።  29%  በመቶ ደግሞ በሽታው የሚመጣውን ከባድ ህመም ይከላከላል ።
ከዚህ አንፃር  የወባ በሽታን በስፋት የሚከላከል  እና ጥቅም ላይ የሚውል የመከላከያ ክትባት ማግኘት  በህክምናው ዘርፍ ለሚደረጉ  ምርምሮች  ታላቅ ግኝትና ውጤት ነው ተብሏል። ክትባቱ በቀጣይ በሚካሄዱ ሙከራዎች  ውጤታማነቱ  በተገቢ ሁኔታ ከተረጋገጠና  በስኬት የሚጠናቀቅ ከሆነ፤በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ከሞት የሚታደግ ይሆናል።

ፀሀይ ጫኔ 
ነጋሽ ሙሀመድ