1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚየመካከለኛው ምሥራቅ

በጋዛ የወደመውን መልሶ ለመገንባት እስከ 50 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 30 2016

እስራኤል በጋዛ ለሰባት ወራት ባካሔደችው ወታደራዊ ዘመቻ የወደመውን መልሶ ለመገንባት እስከ 50 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ የተመድ አስታውቋል። ጦርነቱ ከ1.7 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ወደ ድሕነት ሲገፋ ሥራ አጥነት ከ25% ወደ 46 አሻቅቧል። በጦርነቱ የወደሙ መኖሪያ ቤቶችን መልሶ ለመገንባት እስከ 80 ዓመታት ሊወስድ ይችላል።

https://p.dw.com/p/4fcNM
በጋዛ በእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ የወደመ ሕንጻ
በተባበሩት መንግሥታት ስሌት መሠረት በጋዛ የወደሙ ቤቶችን ለመገንባት ብቻ 80 ዓመታት ሊወስድ ይችላል። ምስል Mohammed Salem/REUTERS

በጋዛ የወደመውን መልሶ ለመገንባት እስከ 50 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል

የቤልጅየም ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ደ ክሮ እስራኤል በኃይል በያዘቻቸው የፍልስጤም ግዛቶች የተመረቱ ሸቀጦች ላይ ዕገዳ እንዲጣል የአውሮፓ ሀገራት ግፊት እንዲያደርጉ ይፈልጋሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሳቡን ያቀረቡት እስራኤላውያን ሠፋሪዎች በፍልስጤማውያን ላይ የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች በበረቱበት ወቅት ነው።

ተምር፣ የወይራ ዘይት እና ወይንን ጨምሮ አሌክሳንደር ደ ክሮ እስራኤል በኃይል በያዘቻቸው የፍልስጤም ግዛቶች በሠፋሪዎች የተመረቱ ሸቀጦች ወደ አውሮፓ ገበያ እንዳይገቡ ለማቆም ዘመቻ ጀምረዋል።

ደ ክሮ የቤልጅየም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም በእስራኤል ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ያደረጓቸውን ግፊቶች ሲቃወሙ ነበር። በዚህ ሣምንት ግን “በኃይል በተያዙት ግዛቶች ጨምሮ መጠነ-ሰፊ ግጭት አለ። በጋዛ ነገሮች መጥፎ እየሆኑ መሔዳቸው ብቻ ሳይሆን በዌስት ባንክ ሥምምነቶች እየተከበሩ አይደለም” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ደ ክሮ አቋማቸውን ያስለወጣቸውን ጉዳይ አስረድተዋል።

“በዚህም ግጭት እየጨመረ ሲሔድ እያየን ነው። ይኸ ደግሞ ሁለት መንግሥታት የመመሥረት መፍትሔ እንቅፋት ነው” ያሉት ደ ክሮ “በፍልስጤም እና በእስራኤል ሰላም እንዲወርድ ከፈለግን ሁለት ሀገራት ወደ መመሥረት መፍትሔ ማተኮር አለብን” የሚል አቋም አላቸው።

ማሕደረ ዜና፣ የጋዛ ጦርነት እንዲቆም የሚጠይቁ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጥሪ

“እንደ አውሮፓውያን ሀገሮች በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት የተፈረሙ ሥምምነቶች በሙሉ በሚጣሱባቸው አካባቢዎች የሚመረቱ ሸቀጦች መነገድ መቀጠል አለብን ብዬ አላምንም” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቨርተ ኒውስ ለተባለው የቤልጅየም የቴሌቭዥን ጣቢያ ተናግረዋል። 

የቤልጅየም ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ደ ክሮ
የቤልጅየም ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ደ ክሮ እስራኤል በኃይል በያዘቻቸው የፍልስጤም ግዛቶች የተመረቱ ተምር፣ የወይራ ዘይት እና ወይን የመሰሉ ሸቀጦች ወደ አውሮፓ እንዳይገቡ ለማድረግ ዘመቻ ጀምረዋል።ምስል Juliette Bruynseels//Belga/IMAGO

በዌስት ባንክ እና በኢየሩሳሌም በፍልስጤማውያን ላይ በሚፈጸሙ ብርቱ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ሳቢያ የአውሮፓ ምክር ቤት “አክራሪ” ባላቸው አራት ሠፋሪዎች እና ሁለት ቡድኖች ላይ ማዕቀብ ጥሏል።

ማዕቀብ የተጣለባቸው ግለሰቦች እና ተቋማት በዌስት ባንክ በፍልስጤማውያን ላይ “የንብረት ባለቤትነት መብት እና የቤተሰብ ሕይወትን የሚጻረሩ ሥቅየት እና ሌሎች ኢ-ሰብዓዊ ወይም አዋራጅ አያያዝ ወይም ቅጣት ጨምሮ ብርቱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች” መፈጸማቸውን ምክር ቤቱ ሚያዝያ 11 ቀን 2016 አስታውቋል።

አሜሪካ በዌስት ባንክ ለሚገኙ አክራሪዎች ገንዘብ በማሰባሰብ በከሰሰቻቸው ሁለት ተቋማት ላይ በተመሳሳይ ዕለት ማዕቀብ መጣሏን የሀገሪቱ ግምዣ ቤት ይፋ አድርጓል። ካናዳ፣ ፈረንሳይ እና ዩናይትድ ኪንግደም ተመሣሣይ እርምጃ ወስደዋል።

የእስራኤል አጋሮች ባለፉት ሣምንታት በጋዛ የተፈጠረው ሰብአዊ ቀውስ እንዳይባባስ ተጨማሪ እርዳታ ወደ አካባቢው እንዲደርስ የሚያደርጉት ግፊት ተጠናክሮ ታይቷል። ይሁንና በእስራኤል ላይ ማዕቀብ የጣሉ ወይም ምርቶቿን ከግብይት ያገዱ ጥቂቶች ናቸው።

እስራኤል ለጋዛ ዕርዳታ እንዳይደርስ መከልከሏን እንድታቆም ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት አዘዘ

በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በኤኮኖሚ ረገድ ጠንከር ያለ እርምጃ በመውሰድ ቀዳሚ የሆነችው ቱርክ ናት። በጋዛ “በከፋው ሰብአዊ ቀውስ” ምክንያት ቱርክ ከእስራኤል ጋር የነበራትን የንግድ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ እንዳቋረጠች ባለፈው ሣምንት አስታውቃለች።

የቱርክ ፕሬዝዳንት ረቺብ ጠይብ ኤርዶኻን
ፕሬዝዳንት ረቺብ ጠይብ ኤርዶኻን የሚመሩት የቱርክ መንግሥት ከእስራኤል ጋር የነበረውን የንግድ ግንኙነት አቋርጧል። ምስል Valery Sharifulin/TASS/dpa/picture alliance

በጎርጎሮሳዊው 2023 ብቻ ሁለቱ ሀገሮች 6.8 ቢሊዮን ዶላር ወይም 6.3 ቢሊዮን ዩሮ የሚያወጣ ግብይት ነበራቸው።

እስራኤል ወደ ጋዛ በቂ እርዳታ ያለ ገደብ እንዲደርስ እስክትፈቅድ ድረስ እርምጃው ገቢራዊ ሆኖ እንደሚቆይ የቱርክ ንግድ ሚኒስቴር መግለጫ ይጠቁማል። የቱርክ የንግድ ሚኒስትር ኦመር ቦላት ሀገራቸው እርምጃውን የወሰደችው እስራኤል “ግትር አቋም” እና በደቡባዊ ጋዛ በምትገኘው ራፋ ያለው ሁኔታ እየተባባሰ በመሔዱ መሆኑን ተናግረዋል።

የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ ግን “የፕሬዝደንት ረቺብ ጣይብ ኤርዶኻን እርምጃ ዓለም አቀፍ የንግድ ሥምምነቶች ይጥሳል” ሲሉ ከሰዋል። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ “የአምባገነን ጠባይ እንዲህ ነው” ሲሉ በቀድሞው ትዊተር በአሁኑ ኤክስ ረቺብ ጣይብ ኤርዶኻንን ወረፍ አድርገዋል።

ፕሬዝደንት ረቺብ ጣይብ ኤርዶኻን በበኩላቸው “መላው ምዕራቡ ዓለም በተለይ አሜሪካ ለእስራኤልን ይሠራል። እንዳለመታደል ሆኖ ደሀው፣ የተቸገረው እና ምስኪኑ የፍልስጤም ሕዝብ በእስራኤል ቦምብ እንዲሞት ተፈርዶበታል። ይኸንን ዝም ብለን ማየት አንችልም” ሲሉ መንግሥታቸው እርምጃ የወሰደበትን ምክንያት ተናግረዋል።

እስራኤል 1,200 ገደማ ሰዎች ለተገደሉበት እና ሌሎች ከ250 በላይ ለታገቱበት የመስከረም 26 ቀን 2016 ጥቃት በዋናነት ተጠያቂ በምታደርገው ሐማስ ላይ የጀመረችው ወታደራዊ እርምጃ ሰባት ወራት ሞልቶታል።

ባለፉት ሰባት ወራት 34 ሺሕ 789 ሰዎች መገደላቸውን ሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። አብዛኞቹ ሴቶች እና ሕጻናት ናቸው። ጦርነቱ ከ78 ሺሕ በላይ ሰዎችን አቁስሏል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ መሠረት 1.7 ሚሊዮን ሰዎች ወይም ከጋዛ ነዋሪ 75 በመቶው ተፈናቃይ ለመሆን ተገደዋል። ሚሊዮኖች ከጠኔ የሚስተካከል ረሐብ ተጋርጦባቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ የሚመሩት የእስራኤል መንግሥት በጋዛ የሚያካሒደው ወታደራዊ ዘመቻ ሰባት ወራት ሞልቶታልምስል Abir Sultan via REUTERS

ከብርቱ ሰብአዊ ቀውስ ባሻገር ጦርነቱ በፍልስጤም ማኅበረ-ኤኮኖሚያዊ ዳፋ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ በመሔድ ላይ እንደሚገኝ በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም የአረብ ሀገሮች ቢሮ ዳይሬክተር አብዳላሕ አል ዳራዲ ተናግረዋል።

የእስራኤል እና የኢራን ቁርቁስ ወዴት ያመራል?

አብዳላሕ አል ዳራዲ እንደሚሉት “በስድስት ወራት ጦርነት አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (GDP) ከጦርነቱ በፊት ከነበረው ትንበያ በ25 በመቶ ቀንሷል። ጦርነቱ ለዘጠኝ ወራት ቢቀጥል ኪሳራው 29 በመቶ እንደሚደርስ ይጠበቃል”

የተባበሩት መንግሥታት የልማት መርሐ-ግብር ይፋ ያደረገው ሠነድ እንደሚያሳየው የፍልስጤም ኤኮኖሚ በሰባት ወራት ጦርነት 7.1 ቢሊዮን ዶላር ቀንሷል። ተጨማሪ 1.74 ሚሊዮን ሰዎች ወደ ድሕነት ተገፍተዋል።

“ድህነት በጦርነቱ ስድስት ወራት ከ38 በመቶ በከፍተኛ መጠን ጨምሮ ከ60 በመቶ በላይ ደርሷል” ያሉት በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም የአረብ ሀገሮች ቢሮ ዳይሬክተር “በሁሉም የፍልስጤም ግዛቶች 25 በመቶ የነበረው ሥራ አጥነት አሁን 46 በመቶ ደርሷል” ሲሉ አስረድተዋል።

“ምሥራቅ ኢየሩሳሌም፣ ዌስት ባንክ እና ጋዛን ጨምሮ በሁሉም የፍልስጤም ግዛቶች የሰብአዊ ልማት 20 ዓመታት ወደ ኋላ ተመልሷል” ያሉት አብዳላሕ አል ዳራዲ በተለይ በጋዛ የከፋ መሆኑን አልሸሸጉም።

ሰብአዊ ልማት “በጋዛ ብቻ ከ40 ዓመታት በላይ ወደ ኋላ ተመልሷል” ያሉት ኃላፊው “በሁሉም የፍልስጤም ግዛቶች ላለፉት 20 ዓመታት በጋዛ ደግሞ ላለፉት 40 ዓመታት በሰብአዊ ልማት ላይ የተደረገው ኢንቨስትመንት ከስሯል ማለት ነው” ሲሉ ብርታቱን ገልጸውታል።

ማሕደረ ዜና፣ የጋዛ እልቂት፣ የምዕራባዉያን ድምፀት መለወጥ

የዓለም ባንክ ከአንድ ወር ገደማ በፊት ይፋ ያደረገው ጊዜያዊ የግምገማ ሪፖርት በጋዛ ብቻ የደረሰው የቁልፍ መሠረተ-ልማት ውድመት 18.5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚገመት ያሳያል።  ሪፖርቱ እንደሚያሳየው በጋዛ 84 በመቶ የጤና ተቋማት ወድመዋል፤ የትምህርት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ቆሞ ሁሉም ሕጻናት ከትምህርት ቤት ውጪ ሆነዋል።

ራፋ በእስራኤል ወታደራዊ እርምጃ የፈረሰ ቤት እና ዕቃ የሚሰበስቡ እናት
ከጋዛ ነዋሪ ከ75 በመቶ በላይ የሚሆነው መፈናቀሉን የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያልምስል Said Khatib/AFP

በፍልስጤም ማዕከላዊ ስታስቲክስ መሥሪያ ቤት መረጃ መሠረት በሰባት ወራት ጦርነት ከ25 ሺሕ በላይ ሕንጻዎች፣ 86 ሺሕ የመኖሪያ ቤቶች ወድመዋል። በመረጃው መሠረት በጦርነቱ 100 ትምህርት ቤቶች እና ዩኒቨርሲቲዎች ሲወድሙ 32 ሆስፒታሎች ከአገልግሎት ውጪ ሆነዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ስሌት መሠረት በጋዛ የወደሙ ቤቶችን ለመገንባት ብቻ 80 ዓመታት ሊወስድ ይችላል። የድርጅቱ ግምት በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን የመኖሪያ ቤቶች ለመጠገን የሚያስፈልገውን ጊዜ የሚጨምር አይደለም።

ትምህርት እና ጤናን በመሠሉ መሠረታዊ አገልግሎቶች ረገድ አስቸኳይ የመፍትሔ እርምጃ ተግባራዊ ካልተደረገ የጦርነቱ ጠባሳ ለረዥም ዓመታት ሊዘልቅ እንደሚችል አብዳላሕ አል ዳራዲ ገልጸዋል።

“ጋዛን መልሶ ለመገንባት በእኛ ግምት መሠረት ዛሬ ቢያንስ ከ 40 እስከ 50 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል” ያሉት በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም የአረብ ሀገሮች ቢሮ ዳይሬክተር አብዳላሕ አል ዳራዲ ጦርነቱ በተራዘመ ቁጥር ለመልሶ ግንባታ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠንም እያሻቀበ እንደሚሔድ አስጠንቅቀዋል።

አሜሪካ እና የአውሮፓ ሀገራትን ጨምሮ ምዕራባውያን በጋዛ የተቀሰቀሰው ሰብአዊ ቀውስ እንዳስደነገጣቸው በተደጋጋሚ ቢገልጹም ከፍተኛ የጦር መሣሪያ እና የገንዘብ ድጋፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ለሚመሩት የእስራኤል መንግሥት ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

የእስራኤልን ወታደራዊ እርምጃ ለመተቸት አሊያም የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ ለማቅረብ ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት የቀረቡ የውሳኔ ሐሳቦችን ልዕለ-ኃያላኑ ድምጽን በድምጽ በመሻር መብታቸው በመጠቀም ውድቅ ሲያደርጉ ነበር።

እሸቴ በቀለ

ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር