1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፍሬድሪክ ቬሌም ዴ ክለርክ ሲታወሱ 

ቅዳሜ፣ ኅዳር 4 2014

ዴ ክለርክ ከማንዴላ ምክትሎች አንዱ በመሆን አገልግለዋል።ዴ ክለርክ ይህን ያልተጠበቀ እርምጃ መውሰዳቸው ሲያነጋገር የቆየ ጉዳይ ነው። አፓርታይድን ገርስሰው የመጣላቸው ምክንያት ምን ይሆን የሚለው ከብዙ አቅጣጫ ጥያቄ ሲያንሳ ቆይቷል። ዴክለርክ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት ድንገት አይደለም። ይልቁንም አፓርታይድ መወገድ እንዳለበት ስላመኑ እንጂ።

https://p.dw.com/p/42wcb
Südafrika Fredrik Willem de Klerk Bekanntgabe Mandela Freilassung
ምስል picture-alliance/dpa

ፍሬድሪክ ቬሌም ዴ ክለርክ ሲታወሱ 

ለአራት አሥርት ዓመታት በደቡብ አፍሪቃ ተንሰራፍቶ የቆየውን የአፓርታይድ ማለትም ዘር መድልዎ ስርዓት ለማስወገድ በተጫወቱት ዐቢይ ሚና ስማቸው ከፍ ብሎ ይነሳል፤ባለፈው ሐሙስ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የመጨረሻው ነጭ የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝዳንት ኤፍ ደብሊው ዴ ክለርክ። የዛሬው ትኩረት በአፍሪቃ የእኚህን ታላቅ ደቡብ አፍሪቃዊ ታሪክ ያስቃኘናል።
«ድንገት ነቅቼ አይደለም አፓርታይድ ስህተት ነው ያልኩት።ይልቁንም አጠቃላይ ሂደት ነበር።» 
ኤፍ ደብሊው ደክለርክ ከዛሬ 31 ዓመት በፊት ጥቁር ደቡብ አፍሪቃውያን በተቋማዊ ዘረኝነት ለበርካታ አሥርት ዓመታት የተጨቆኑበት ስርዓት እንዳበቃ ያሳወቁበት ንግግር ነበር። ዴክለርክ የዘር መድልዎን ስርዓት ከደቡብ አፍሪቃ በመገርሰስ ለተጫወቱት ትልቅ ሚና ፣ስርዓቱ ለዓመታት በእስር ካንገላታቸው ከኔልሰን ማንዴላ ጋር የሰላም የኖቤል ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ሙሉ ስማቸው ፍሬድሪክ ቬሌም ዴክለርክ ነው ።የተወለዱት በጎርጎሮሳዊው 1936 ከወግ አጥባቂ ወላጆቻቸው ነው። አባታቸው ከደቡብ አፍሪቃ የዘር መድልዎ ስርዓት መሥራቾች አንዱ ናቸው።ዴክለርክ ሲወለዱ አባታቸው የካቤኔ አባል ነበሩ። ዴክለርክ ሕግ ካጠኑ በኋላ የሀገሪቱ NATIONAL PARTY ብሔራዊ ፓርቲን ተቀላቀሉ።ከርሳቸው አስቀድሞ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር  ቦታ ከሥልጣን ሲወርዱ ዴ ክለርክ በምትካቸው ተመርጠው በ1989 ሥልጣኑን ተረከቡ።ወቅቱ በደቡብ አፍሪቃው የዘር መድልዎ ስርዓት ላይ ዓለም አቀፍ ጫና የሚደረግበትና በሀገር ውስጥም ተቃውሞው እየተጠናከረ የሄደበት የነበረ ቢሆንም ደቡብ አፍሪቃውያን በጠቅላይ ሚኒስትር ዴክለርክ አመራር ያን ያህል ለውጥ ይመጣል ብለው አልጠበቁም። ይሁንና ዴክለርክ ከ5 ወራት የስልጣን ቆይታ በኋላ ለሀገራቸው ምክር ቤት ባሰሙት ንግግር የዘር መድልዎ ስርዓትን ከሃገሪቱ ለማስወገድ ስርነቀል ለውጥ እንደሚደረግ አስታወቁ። ይህ እውን ሆኖም ከ40 ዓመታት በላይ በደቡብ አፍሪቃ ጥቁሮች ላይ ጭቆናን ሕጋዊ አድርጎ የቆየው የዘር መድልዎ ስርዓት አበቃ ።ከዚህ ሌላ ዴክለርክ ስርዓቱ ለሶስት አሥርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በእስር ያንገላታቸውን የደቡብ አፍሪቃ የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላን እና ሌሎች የፖለቲካ እስረኞችን እንደሚፈቱም በይፋ አስታወቁ
«መንግሥት ሚስተር ማንዴላን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመፍታት ጥብቅ ውሳኔ ማሳለፉን ልነግራችሁ እፈልጋለሁ።»
በጎርጎሮሳዊው የካቲት 2 ቀን 1990ዓም ባደረጉት በዚህ ንግግር በኔልሰን ማንዴላ ፓርቲ የአፍሪቃ ብሔራዊ ምክር ቤት ላይ የተጣለውን እገዳ መነሳቱን አስታወቁ። ቃላቸውም ቃል ብቻ ሆኖም አልቀረም። ከ9 ቀናት በኋላ ተግባራዊ አደረጉት። ከ27 ዓመታት በላይ በሮቢን ደሴት በእስር የማቀቁት ማንዴላ ተፈቱ ። እድሜ ዘመናቸውን ወግ አጥባቂና  በዘር መድልዎ ስርዓትም ያምኑ ከነበሩት ከዴክለርክ ይህን ማንም አልጠበቀም። እርምጃው ደቡብ አፍሪቃውያንን ብቻ ሳይሆን መላውን ዓለም አስደመመ። በጎርጎሮሳዊው 1993 ዴ ክለርክና ማንዴላ በጋራ የሰላም የኖቤል ሽልማት ተሰጣቸው።ሆኖም በተለይ የዴክለርክ የሰላም ኖቤል መሸለም ማወጣገቡ አልቀረም።ብዙዎች በርሳቸው አመራር  በመንግሥት ድጋፍ የተፈጸሙ ወንጀሎች ጉዳይ ጥያቄ አስነስቶም ነበር።በጎርጎሮሳዊው 1994 ጥቁር ደቡብ አፍሪቃውያን መሪያቸውን ለመምረጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ድምጻቸውን ሰጡ።የኔልሰን ማንዴላ ፓርቲ የደቡብ አፍሪቃ ብሔራዊ ምክር ቤት በእንግሊዘኛው ምህጻሩ ኤ ኤን ሲ በአብላጫ ድምጽ አሸነፈ።ማንዴላም የመጀመሪያው የደቡብ አፍሪቃ ጥቁር ፕሬዝዳንት ሆኑ። ከምርጫው በኋላ በተቋቋመው የብሔራዊ አንድ መንግሥትም ዴ ክለርክ ከማንዴላ ምክትሎች አንዱ በመሆን አገልግለዋል።ዴ ክለርክ ይህን ያልተጠበቀ እርምጃ መውሰዳቸው ሲያነጋገር የቆየ ጉዳይ ነው። አፓርታይድን ገርስሰው የመጣላቸው ምክንያት ምን ይሆን የሚለው ከብዙ አቅጣጫ ጥያቄ ሲያንሳ ቆይቷል። በበኩላቸው አፓርታይድን አንቅረው የተፉበትን ምክንያት እንዲህ ነበር ያስረዱት።
«በተለይ ከ1980 ዎቹ መጨረሻ ወዲህ ስናራምደው የነበረው አቋማችን በሞራል ረገድም ተቀባይነት እንደሌለው፣አፓርታይድም ስህተት መሆኑን ፣ሊሻሻል እንደማይችልና መወገድ እንዳለበት አመንኩ።አፓርታይድን ለማስወገድም ወሳኙን ሚና ተጫወትኩ፤። በእውነትና እርቀ ሰላም ኮሚሽን ፊትም ከልብ የመነጨ ይቅርታም ጠየኩ። ይቅርታ የጠየኩትም አፓርታይድ በቆዳ ቀለማቸው ምክንያት ለደረሰባቸው ሰቆቃና ውርደት ነው። »
ቀደም ሲል ዴክለርክ በአፓርታይድ ወይም በዘር መድልዎ ስርዓት ወቅት በደቡብ አፍሪቃ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ወንጀሎችን ለመመርመር የእውነትና የእርቅ ኮሚሽን መቋቋሙን ተቃውመው ነበር። ዴክለርክ ስለ አፓርታይድ ዘመን ያላቸው አመለካከት አሁንም ብዙ ጥያቄዎችን ማስነሳቱ ቀጥሏል። ዴ ክለርክ በአንድ መግለጫቸው «አፓርታይድ በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ነው»መባሉን አለመቀበላቸው ብዙ ተቃውሞ አስነስቶባቸው ነበር። ከዚያ ይልቅ ዴ ክለርክ በስርዓቱ የተፈጸሙ የፖለቲካ ወንጀሎች፣ በሙሉ በምህረት እንዲታለፉ ነበር ፍላጎታቸው። ኋላ ላይ ግን መግለጫውን ስበውታል። ይህ ልዩነቱን አስፍቶ በጎርጎሮሳዊው 1996 ፓርቲያቸውን ከማንዴላ መንግሥት አስወጥተው እርሳቸውም የምክትል ፕሬዝዳንትነት ሃላፊነታቸውን ለቀቁ። ብዙም ሳይቆዩ ራሳቸውን ከፖለቲካው ዓለም አገለሉ።
በማንዴላ የስልጣን ዘመን በምክትል ፕሬዝዳንትነት ያገለገሉትን ዴ ክለርክን ፣ማንዴላ ታላቅ  ሰው ሲሉ አወደሱዋቸው ነበር።
«ሚስተር ዴክለርክ ታላቅ ሰው ናቸው።ብዙ ጊዜ እንጋጭ ነበር።ግን አከብራቸዋለሁ ። ምክንያቱም በስተመጨረሻ እጃችንን ተያይዘን ተቀምጠን ቡና ስንጠጣ ሁሉንም እንረሳለን።»
ደቡብ አፍሪቃውያን በርሳቸው ህልፈት የተሰማቸውን ለዶቼቬለ ተናግረዋል። እኚህ አስተያየት ሰጭ አፓርታይድ እንዲቆም ምክንያቱ ዴ ክለርክ ሳይሆኑ የደቡብ አፍሪቃ የነጻነት ታጋዮች ናቸው ይላሉ።
«ነፍስዎን ያሳርፍ አንድ ሰው ሞቷል። ሆኖም  ርሳቸው መጥተው አላዳኑንም።ከርሳቸው ይልቅ የ1980ዎቹና ከዛም ቀደም ያሉት ወጣቶች ናቸው ሀገሪቱን ነጻ ያወጡት »
ሌላው አስተያየት ሰጭ ግን የደቡብ አፍሪቃ ህዝብ ባለውለታ የሚሉት ዴክለርክንና ማንዴላ ነው።
«እርሳቸውና ሚስተር ማንዴላ ትተውት የሚያልፉት ቅርስ እንደሚመስለኝ ለዘላለም ይኖራል። ይህ የርሳቸው ትልቅ አስተዋጽኦ ውጤት ነው።የርሳቸው መንግሥት የከዚህ ቀደሙ መንግሥት አካል ነበር።የሚመስለው። ሆኖም ደቡብ አፍሪቃን ከዚያ አውጥተው ወደ ትክክለኛ መስመር አምጥተዋታል።ሁሉም ከማንዴላ ጋር በሀገሩ ጉዳይ ድምጽ እንዲኖረው አድርገዋል።»
እኚህኛው ደግሞ ዴክለርክ ስልጣናቸውን ለማንዴላ መስጠታቸውን ትክክለኛ ውሳኔ ይሉታል።
«በዚያን ጊዜ ስልጣኑን ለኔልሰን ማንዴላ ነው የሰጡት። ትክክለኛ ነው። ትክክለኛ ውሳኔ ነው ያደረጉት። ይህን እያሰብን ነፍስዎን ይማር እንላለን።»
እኚህ አስተያየት ሰጭ በበኩላቸው ከዴክለርክ መውሰድ እንደሚገባ ያሳስባሉ።
«እኔ ያደግኩበት ጊዜ ኔልሰን የታሰሩበትና ልዩ ልዩ አወዛጋቢ ጉዳዮች ያሉበት ነበር። በኔ አመለካከት ታላቅ ሰው ነበሩ። እርሳቸውን የማግኘት እድል አጋጥሞኝ ነበር። 17፣ 18ና 19 ዓመት ሳለሁ አግኝቻቸው ነበር።ሕይወት እንዲሁ የሚተው አይደለም። ለውጥ ከፈለግክ ራስህ ነህ ለውጡን ማምጣት ያለብህ። ሌሎች እንዲያደርጉልህ መጠበቅ የለብህም።» 
የማንዴላንና የዴ ክለርክን አስተዋጽኦ አየሚያጎሉት ደግሞ
«ርሳቸውና ሚስተር ማንዴላ ይህች ሀገር አሁን የምትገኝበት ደረጃ ላይ አድርሰዋል።ስለዚህ ማረፋቸው ያሳዝናል።»ሲሉ
በዘመነ-አፓርታይድ ደቡብ አፍሪቃ ከአብዛኛው ዓለም ተግላ የነበረችበትን ጊዜ ወደ ኋላ መለስ ብለው ያስታወሱት፣ እኚህ የዚያን ጊዜዋ ወጣት ድግሞ ፣ ዴክለርክ የዘር መድልዎ ስርዓትን ለማስወገድ ያበቃቸው ከሀገር ውስጥና ከውጭ ያጋጠማቸው ጫና ነበር ይላሉ።
«በዚያን ጊዜ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ መኖር ማለት በአጭር ጊዜ ውስጥ በእንፋሎት ምግብን በሚያበስል ድስት ውስጥ ውስጥ ከመኖር ጋር ማነጻጸር ይቻላል። ያኔ የትም መሄድ አይቻልም ነበር።በሃገሪቱ ላይ በርካታ ማዕቀቦች ተጥለው ነበር። ስለዚህ ምንም ምርጫ የነበራቸው አልመሰለኝም።ማድረግ የነበረባቸውን ነው ያደረጉት።» 
ዴ ክለርክ አፓርታይድን በመገርሰስ በታሪክ መዝገብ ስማቸው ቢሰፍርም አሁንም ዘርን መሰረት ያደረገ ኢፍትሃዊነት ያስከተላቸውን ተጽእኖዎች በመታገል ላይ ባለችው በደቡብ አፍሪቃ ብዙዎች ለረዥም ጊዜ የተሰቃዩበት የዚህ ስርዓት አካል አድርገው ነው የሚያስታውሷቸው ጥቂት አይደሉም። የአፓርታይድን ግብዐተ መሬት የፈጸሙት ዴክለርክ በሌላ በኩል በወግ አጥባቂዎችና በቀኝ አክራሪዎች በከሀዲነት ክፉኛ ሲተቹ ነበር። የቀድሞው የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝዳንት ኤፍ ደብሊው ዴ ክለርክ ከትናንት በስተያ ሐሙስ ኬፕታውን በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ነበር በ85 ዓመታቸው ያረፉት።ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት እንዲሁም የልጅ ልጆች አያት ነበሩ።
ኂሩት መለሰ

Südafrika l 25 Jahre Demokratie - Ende der Apartheid l Nelson Mandela 1994
ምስል picture alliance/AP Photo/j. Parkin
Friedensnobelpreisträger, Frederik Willem de Klerk, ehemaliger Präsident Südafrikas
ምስል Getty Images/R.Bosch
Bildergalerie Leben Nelson Mandela
ምስል picture-alliance/AP

አዜብ ታደሰ