1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጎርፍ መከላከያ ፕሮጀክት በድሬደዋ

ሰኞ፣ ግንቦት 5 2016

በድሬደዋ በተለያዩ ጊዜያት የጎርፍ ጉዳት በሚከሰትበት የደቻቱ ወንዝ ሳቢያ የሚደርስን ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ለመቀነስ ይረዳሉ የተባሉ የመከላከል ሥራዎች ተግባራዊ የሚሆኑበት ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ።

https://p.dw.com/p/4fnvV
የድሬደዋ የችግኝ ማፍያ ጣቢያ
የድሬደዋ የችግኝ ማፍያ ጣቢያ ምስል Messay Teklu/DW

የጎርፍ መከላከያ ፕሮጀክት በድሬደዋ

 

በእንግሊዝኛ ምዕፃሩ SANCASA የሚል መጠርያ ያለው ይህ ፕሮጀክት ከካናዳ መንግሥት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት የሚከወን ነው። የፕሮጀክቱን ጥናት ያካሄደው የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ እና የድሬደዋ አስተዳደርን ጨምሮ አራት አካላት በትግበራው ይሳተፋሉ ተብሏል። የተፋሰሱን ዳርቻዎች መሠረት ያደረገ የአፈር እና ውሀ ጥበቃ ሥራን ጨምሮ በርካታ ተግባራት እንደሚከናወኑ በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የፕሮጀክቱ መሪ ዶ/ር ክበበው ክብረት ለዶይቼቬለ ተናግረዋል።

በፕሮጀክቱ ትግበራ ሴቶች ዋነኛ ተሳታፊ እንደሚሆኑም አስረድተዋል።

 ዶ/ር ክበበው ክብረት በፕሮጀክቱ ትግበራ አንድ አካል በሆነው የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የ SANCASA ፕሮጀክት መሪ ሲሆኑ በፕሮጀክቱ ይከናወናሉ ያሏቸውን ተግባራት ለዶይቼ ቬለ ዘርዝረዋል።  

እሳቸው እንደሚሉትም የአካባቢውን ማኅበረሰብ በዋነኛነትም ሴቶችን በማሳተፍ በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት መሬት ላይ በሚከወኑ ተግባራት ከረዥም ጊዜ በኋላ ጎርፍ መከላከልንጨምሮ ሌሎች ውጤቶች ይሳካሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ፎቶ፤ የድሬደዋ የችግኝ ማፍያ ጣቢያ
ድሬደዋ ለጎርፍ አደጋ እንዳትጋለጥ በሚደረገው ጥረት ሴቶችም እንደሚሳተፉ ተገልጿል። ፎቶ፤ የድሬደዋ የችግኝ ማፍያ ጣቢያምስል Messay Teklu/DW

የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር በበኩላቸው ዋነኛ የከተማዋ ስጋት የሆነውን ደቻቱ በመባል የሚታወቀውን አካባቢ የሚያጠቃውን ጎርፍ ትኩረት አድርጎ ይከናወናል ካሉት የ SANCASA ፕሮጀክት ትግበራ ተሳታፊዎች ጋር በቅርበት እንሠራለን ብለዋል። ከተማዋን በተለያዩ ጊዜያት በሚያጠቃው ጎርፍ ብዙ ጉዳት መድረሱን ያነሱት የከተማዋ ነዋሪ አቶ ሻሜ አብዱረህማን በፕሮጀክቱ የሚሠሩ ሥራዎች መፍትሄ ይሆናሉ የሚል እምነታቸውን ለዶይቼ ቬለ ገልፀዋል። በካናዳ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ አግኝቶ ለትግበራ ይፋ የሆነው የ SANCASA ፕሮጀክት ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራልም ተብሏል።

መሳይ ተክሉ

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ