1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደም እጥረት የአማራ ክልል ሆስፒታሎችን አገልግሎት እየተፈታተነ ነው

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 30 2016

በግጭት ምክንያት በአማራ ክልል ደም ባለመሰብሰቡ ሆስፒታሎች ሕሙማን ለማከም ችግር ገጥሟቸዋል። በፍኖተ-ሰላም ሆስፒታል በሦስት ወራት ብቻ ሦስት እናቶች በደም እጥረት ምክንያት መሞታቸውን የሆስፒታሉ ሐኪም ተናግዋል። የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ እንደሚሉት የቀዶ ሕክምና ቀጠሮ ያላቸው 12,000 ገደማ ሕሙማን በደም እጥረት ሕክምና አላገኙም።

https://p.dw.com/p/4fdEt
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አበበ ተምትም
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አበበ ተምትም በደም እጥረት ለቀዶ ሕክምና ቀጠሮ የያዙ 12,000 ገደማ ሕሙማን ሕክምና እንዳላገኙ ተናግረዋል። ምስል Alemnew Mekonen/DW

የደም እጥረት የአማራ ክልል ሆስፒታሎችን አገልግሎት እየተፈታተነ ነው

በፍኖተሰላም ሆስፒታል የማህፀንና የፅንስ  ስፔስያሊስት ዶ/ር ልየው እውነቱ ለዶይቼ ቬሌ እንደገለፁት በደም እጥረት ምክንያት ባለፉት 2 ወራት ብቻ 3 እናቶች ህይወታቸው አልፏል፣ ሌሎች ህሙማንም በደም እጥረቱ  አስፋላጊውን ህክምና አላገኙም ብለዋል፡፡

“... ወደ ሶስት እናቶች ደም በማጣት ብቻ ሞተውብናል፣ ደም የሚያስፈልጋቸው ያለደም የማይሰሩ ህክምናዎችን በድፍረት እየሰራን ነው ያለነው፣ በቅርቡ የሰሞነ ህማማት መግቢያ ቀን  ማሕፀናቸው ተጎድቶ ወደ ሆስፒታላችን ከመጡ እናቶች መካከል አንዷ ወደ ባህር ዳር ተልካ ደም አግኝታለች፣ አንዷ ግን ወደ ሌላ ደም ልገሳ ወደ አለበት ቦታ መሄድ ባለመቻሏ እየተጣጣረች ነው ያለችው፡፡” ብለዋል፡፡

ስማቸው እንዳጠቀስ የፈለጉ አንድ የባሕር ዳር ፈለገ ህይወት ሆስፒታል ሀኪም፣ አሁን አሁን ደም እየለገሰ ያለው የጤና ባለሙያው ብቻ በመሆኑና መሰላቸት ስለተፈጠረ ደም የሚፈልጉ ህሙማን ለሞት እየተዳረጉ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር ያቀረበው ጥሪ

“የጤና ባለሙያ ብቻ ነው ደም የሚሰጠው፣ ለጤና ባለሙያዎች ተነግሮናል፣ ባለሙያዎቹ ስራ ሰርተው፣ ደም ሰጥተው፣ ስለሰለቻቸው አሁን ደም መስጠቱን ንተውታል፣ አሁን በአደጋ የሚመጣው፣ ወላዶች፣ የደም ማነስ በተደጋጋሚ የሚያጋጥማቸው ነፍሰ ጡሮች ኤረን የሚባለውን ኝጥረ ነገር ስለማይወስዱ፣ ያን ካልወሰዱ ደግሞ የደምማነስ ይገጥማቸዋል፣ ስለዚህ እነኚህ እናቶች እየሞቱ ነው፡፡”

ደም የሚሰጡ ግለሰብ
በአማራ ክልል ሆስፒታሎች የተከሰተው የደም እጥረት የሆስፒታሎችን ሥራ እያስተጓጎለ ነውምስል Alemnew Mekonen/DW

 የደም ክምችት እጥረትን ለመቅረፍ የሚሠሩ ወጣቶች

በዚህ ዓመት ከፍተኛ የደም እጥረት በማጋጠሙ እናቶችንና ሌሎች ደም የሚፈልጉ ህሙማንን ለማከም መቸገራቸውን ደግሞ የወልዲ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ፍሰሐ የኋላ ተናግረዋል፣ አስፈላጊ መሳሪዎችና አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች እያሉን ወቅታዊ ሁኔታው ደም እንድንሰበስብ አላደረገንም ነው ያሉት፡፡፡፡

በደብረማርቆስ ሆስፒታል የሚሰሩ የህክምና ዶክተር በተመሳሳይ በሆስፒታሉ የደም እትረት እንዳለ አመልክተዋል፡፡

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አበበ ተምትሜ በዚህ ዓመት በክልሉ ካለው ወቅታዊ የፀጥታ ችግር አኳ የተፈለገው የደም መጠን አልተሰበሰበም ብለዋል፣ በዚህም ምክንያት ደም የሚፈልጉ ከ12 ሺህ በላይ ህሙማን ህክምናውን አላገኙም ነው ያሉት፡፡

ደም የሚሰጡ ግለሰብ
በአማራ ክልል የሕክምና ባለሙያዎች ደም በመስጠት እና ሕሙማን በማከም ላይ ይገኛሉምስል Alemnew Mekonen/DW

በአማራ ክልል የመድሃኒት እና የህክምና ግብአት አቅርቦት መስተጓጎል

አቶ አበበ አክለውም፣ “የደም ማሰባሰብ ስራችን በዚህ ዓመት ዝቅተኛ አፈፃፃም ነው ያለው፣ 80ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ አቅደን የሰበሰብነው ወደ 40ሺህ ዩኒት ደም ብቻ ነው፡፡፣ በአማራ ክልል 10 የደም ባንኮች አሉ፣ በነኚህ የደም ባንኮች በቂ የደም አቅርቦት እየሰራን ነው የነበረው፣ ከወቅቱ የፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ባለሙያዎች እንደልባቸው ተንቀሳቅሰው ማህበረሰቡን አግኝተው፣ የግንዛቤ ስራ ፈጥረው፣ በቂ ደም ለማሰባሰብ ግን አልቻሉም፣ ይህም ባለመሰብሰቡ 12 ሺህ ቀዶ ህክምና የሚፈልጉ ህሙማን ህክምናውን አልወሰዱም፡፡ እነርሱም አገልግሎቱን እንዲያገኙ ጭምር ነው አሁን የደም ልገሳውን የጀመርነው፡፡” ሲሉ ገልፀዋል፡፡

በመሆኑም ያለውን የደም እጥረት ለማቃለል ዛሬ የቢሮው ሰራተኞች ደም መስጠጣቸውን ተናግረዋል፣ ንቅናቄው ወደ ሌሎች የቢሮ ሰራተኞች እንደሚወርድና ደም የማሰባሰብ ስራው እንደሚቀጥል ተናግረዋል፣ ህብረተሰቡም አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

ዓለምነው መኮንን

እሸቴ በቀለ

ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር