1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሚያዝያ 26 ቀን 2016 የዓለም ዜና

Yohannes Gebre Egziabher ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 26 2016

https://p.dw.com/p/4fVgO

ኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኞች ሥራቸውን ስለሠሩ ብቻ ለእሥር እንደሚዳረጉ የ18 ሐገራት ኤምባሲዎች አስታወቁ

የአውሮፓ ሕብረት እና አዲስ አበባ ተቀማጭ የሆኑ የ18 ሀገራት ኤምባሲዎች የዓለም ፕሬስ ነፃነት ቀንን ታሳቢ አድርገው ትናንት በጋራ ባወጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኞች ሥራቸውን ስለሠሩ ብቻ ፍትኃዊ ባልሆነ መልኩ ለእሥር እንደሚዳረጉ አስታውቀዋል።

ኢ- ፍትኃዊ በሆነ ሁኔታ የታሠሩ ያሏቸው ጋዜጠኞች እንዲፈቱ የጠየቁት ኤምባሲዎቹ እውነትን ለመዘገብ ጥረት የሚያደርጉ ጋዜጠኞች እና መገናኛ ብዙኃንን መከላከል የሚያሳስብ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከጋዜጠኞች ጋር እንዲወያዩ ጥያቄ ያቀረበው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ይህንኑ የፕሬስ ነፃነት ቀን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ "ጋዜጠኞች ሥራቸውን ከሥጋትና ፍርሃት ነፃ ሆነው በኃላፊነት ስሜት የሚሰሩበት ሁኔታ ትኩረት ማግኘት ያለበት" መሆኑን እንደሚያምን የምክር ቤቱ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ታምራት ኃይሉ ከዚህ ቀደም ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

ለኤምባሲዎች መግለጫ ቀጥተኛ ምላሽ የሰጠው የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር "በመሰባሰብ በደቦ የሚወጡ" ያላቸው መግለጫዎች ለሁለትዮሽ ግንኙነት የማይጠቅሙ ናቸው  ብሏል። "ከተለመደውና ቅቡልነት ካለው፤ በሁለትዮሽ የዲፕሎማሲያዊ ስምምነት ከተመሠረተው ግንኙነት ደንቦችና አሰራሮች ጋር የሚጣረሱ" ናቸው በማለትም የሀገራቱን አካሄድ ተቃውሟል። 
ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህን መሳዩ አካሄድ የሀገሪቱን "የሕግ የበላይነት ያዳክማል" ሲልም ከተቀባይ ሀገር ጋር እንዲህ ያለውን የግንኙነት አካሄድ መከተል ጠቀሜታ የለውም ብሏል ሲል ሰሎሞን ሙጬ ከአዲስ አበባ ዘግቧል።

 

የአሜሪካና የርዋንዳ ውዝግብ

በምዕራባዊ ዴሞክራስያዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ በሚገኘው የስደተኞች ካምፕ ላይ ጥቃት ፈጽማለች በማለት አሜሪካ የሰነዘረችውን ወቀሳ ሩዋንዳ ውድቅ አደረገች። በአጸፋው ለጥቃቱ ሃላፊነት የሚወስዱት በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ እና በኮንጎ ወታደሮች የሚደገፉ ሚሊሻዎች ናቸው ብላለች።
በስደተኞች መጠለያ ጣቢያው ትላንት በተፈጸመው ጥቃት ቢያንስ 9 ሰዎች መሞታቸውን ተዘግቧል። ጥቃቱን ተከትሎ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ጥቃቱ የተፈጸመው በሩዋንዳ የጦር ሰራዊት በሚደገፈው M 23 በተባሉ አማጺ ሃይሎች መሆኑን በመግለጽ ሩዋንዳን ክፉኛ ወቅሷል። የርዋንዳ ወታደሮችና የM23 ዓማጽያን ወደ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ድንበር የሚያደርጉትን መስፋፋት እንዳሳሰባትም አሜሪካ አስታውቃለች።
ይሁንና የርዋንዳ መንግስት ቃል አቀባይ ዮላንደ ማኮሎ ይህን የአሜሪካ ክስ አጣጥለው ውድቅ አድርገውታል። በአንጻሩ ለጥቃቱ ሃላፊነት የሚወስዱት በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ እና በኮንጎ ወታደሮች የሚደገፉ ሚሊሻዎች ናቸው ብለዋል። የኛ የመከላከያ ሰራዊት በሙያ የታነጸ ስለሆነ ስደተኞችን አያጠቃም በማለት ቃል አቀባዋ አክለዋል ሲል የዘገበው ሮይተርስ ነው።

የእስራኤል የጦር ጀቶች የሐማስ የሮኬት ማስወንጨፍያ ስርዓት ማውደማቸውን ተሰማ።

የእስራኤል የጦር ጀቶች በደቡብ ጋዛ በካንዩኑስ የሚገኘውን የሐማስ የሮኬት ማስወንጨፍያ ስርዓት ማውደማቸውን ተሰማ። በሌላ ወገን እስራኤል በአለፉት 24 ሰዓታት በጋዛ በፈጸመችው ጥቃት 32 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የእስራኤል የመከላከያ ሰራዊት በሰጠው መግለጫ የጦር አውሮፕላኖቹ በካንዩኑስ የሚገኘውን የሐማስ የሮኬት ማስወንጨፍያ ስርዓት ላይ ጥቃት የፈጸሙት፤ ሐማስ በትላንትናው ዕለት ከዚሁ ቦታ ወደ እስራኤል የተለያዩ ከተሞች ሚሳይሎችን በማስወንጨፉ ነው ብሏል።
አየር ሃይሉ ሌላ የሞርታር ቅምቡላ ማስወንጨፍያ ቦታም በጥቃቱ ማውደሙን ነው  ያሳወቀው። የእስራኤል ባሕር ሃይል በፈጸመው ጥቃትም በካንዩኑስ አካባቢ በሚገኘው የስደተኞች ጣቢያና ሕንጻዎች ላይ ጉዳት መድረሱና እስከአሁን የአንድ ፍልስጤማዊ ሕይወት ማለፉን የጀርመን ዜና አገልግሎት DPA ዘግቧል።
የጋዛ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበኩል በአለፉት 24 ሰዓታት እስራኤል በጋዛ ሰርጥ በፈጸመችው ጥቃት 32 ንጹሃን ፍልስጤማውያን ተገድለዋል ብለዋል። 
በእስራኤልና ሐማስ መካከል ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የሞቱ ፍልስጤማውያን ቁጥር 34,654 ሲደርስ የቆሰሉት ደግሞ  77,908 መሆናቸውን የዘገበው አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ነው።
በሌላ ዜና በእስራኤልና ሐማስ መካከል ሰላማዊ እና ፖለቲካዊ መፍትሄ ለማማጣት የሚደረገው ጥረት አሁንም እንደቀጠለ ነው። በግብጽ አደራዳሪነት በሚካሄደው ውይይት የሚሳተፉ የሐማስ ተወካዮች ካይሮ መግባታቸውን አንድ የግብጽ ቴሌቪዥን ዘግቧል። ቀጠር፣ ግብጽና አሜሪካ በሚሳተፉበት የአሁኑ ድርድ ለ40 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስና የእስረኞችና ታጋቾች ልውውጥ እንዲደረግ ለማስማማት ያለመ መሆኑን የወጡ ዘገባዎች ያመላክታሉ።

ዩክሬይን ለጥቃት የተሰማሩ 13 አጥፍቶ ጠፊ ድሮኖችን ማውደሟን ገለጸች።

ሩስያ በደቡብ ምዕራብ ዩክሬይን የምትገኘውን ካርኪየቭ ከተማን መደብደቧን አስታወቀች። ዩክሬይ በበኩሏ ለጥቃት የተሰማሩ 13 አጥፍቶ ጠፊ ድሮኖችን ማውደሟን ገልጻለች።
ሩስያ ድሮኖችንና ሚሳይሎችን ቀላቅላ በፈጸመችው ጥቃት በአንድ መጋዝን ላይ ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ የፈጠረ ሲሆን፤ እሳቱ በአካባቢው በስፋት መዛመቱን የጀርመን ዜና አገልግሎት DPA ዘግቧል።
በካርኪየቭና ዶኒፕሮፕትሮቭ ዞኖች በድምሩ ወደ 6 የሚሆኑ ሰዎች መቁሰላቸውንና መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ በርካታ መሰረተ ልማቶች መውደማቸውን ክየቭ አስታውቃለች። የክየቭ ባለስልጣናት እንዳሉ ለጥቃቱ የተሰማሩ 13 አጥፍቶ ጠፊ ድሮኖች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል።
በሩስያና ዩክሬይን መካከል በበረዷማ የአየር ጸባይ ምክንያት በተለይ የእግረኛ ውግያ ጋብ ብሎ የቆየ ሲሆን አሁን የጸሃያማ ወቅትን ተከትሎ ውግያው ሊያገረሽ እንደሚችል ግምቶች መኖራቸውን ዜናው አክሏል።

አሜሪካ ሰራሽ ሚሳይሎች ማክሸፏን ሩስያ አስታወቀች

የሩስያ የመከላከያ ሚኒስቴር ከዩክሬን የተተኮሱ አሜሪካ ሰራሽ ረዥም ርቀት ተምዝግዛጊ ሚሳይሎች ማክሸፉን አስታወቀ። ሚሳይሎቹ በሩስያ በተያዙ የክሬምያ የባሕር ወሽመጥ ወደሚገኙ የሩስያ ወታደሮች የተተኮሱ ነበሩ ተብሏል።
የሩስያ የመከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ከነዚህ ከተተኮሱ አሜሪካ ሰራሽ ረዥም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳይሎች 6ቱን መትቶ ማክሸፉን አስታውቋል። 
ሚሳይሎቹ 300 ኪሎሜትር ድረስ ተጉዘው የማጥቃት ዓቅም ያላቸው ሲሆን፤ አሁን ዩክሬይን ጥቃት ከፈጸመበት የሩስያ የአየር መቃወምያ ምድብተኞች አሉበት ወደተባለው ወታደራዊ ግንባር ድረስ 165 ኪሎሜትሮች እንደሚርቅ ሮይተርስ ዘግቧል።
ሩስያ ሰሞኑን አሜሪካና ጀርመንን ጨምሮ ከተለያዩ ሃገራት ለዩክሬይን ከተሰጡ ታንኮችና ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችን ማርካ ለሕዝብ ዕይታ ይፋ ማድረጓ ይታወቃል።
በምዕራባውያን በኩልም ወደ ዩክሬይን ከተተኮሱ ሚሳይሎች ሰሜን ኮሪያ ሰራሽ እንደሚገኙበት በምርመር ማረጋገጣቸውን ቀደም ሲል አስታውቀዋል።
ፔንታጎን በበኩሉ የረዥም ርቀት ሚሳይሎቹ ከክምችቱ ወጥተው መሄዳቸውን ተቃውሟል። ይሁንና በዩክሬይን እጅ የገቡት በቀጥታ ከአሜሪካ ወታደራዊ ግምጃቤት ይሁን ከሌላ ሦስተኛ ሐገር ያብራራው ነገር የለም።
ዩክሬይን እነዚህን ረዥም ርቀት የሚወነጨፉ ሚሳይሎች ወደ ሩስያ ግዛት ዘልቃ ለማጥቃት ከተጠቀመችባቸው  በአሜሪካና ሩስያ መካከል ግጭት ሊቀሰቅስ እንደሚችል ተንታኞች እያስጠነቀቁ ነው።
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

Äthiopien Alamata City Gondar
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።