1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የካሜሩን ሴቶች የዘንድሮውን የጀርመን አፍሪቃ የሰላም ሽልማት አሸነፉ

ሐሙስ፣ ሰኔ 1 2015

የዘንድሮው የጀርመን አፍሪቃ የሰላም ሽልማት የካሜሩን ሴቶች ለሀገራቸው ሰላም ላደረጉት ያላሰላሰ ጥረት ተሸላሚ ሆነዋል።ሴቶቹ በዋናነት ያሸነፉት በጎርጎሪያኑ ጥር 2021 ዓ/ም የመጀመሪያውን የሴቶች የሰላም ጉባዔ በማዘጋጀታቸው ነው።

https://p.dw.com/p/4SLT4
Kamerun | Preisträger des Deutschen Afrika-Preis 2023
ምስል Elisabeth Asen/DW

የጀርመን አፍሪቃ ሽልማት የ2023 አሸናፊ

ከ30 በላይ አፍሪቃውያን እጩዎች በተወዳደሩበት በዘንድሮዉ የጀርመን አፍሪቃ ሽልማት በካሜሩን የመጀመሪያው ብሔራዊ የሴቶች የሰላም ጉባዔ የ2023 አሸናፊ ሆኗል።
በምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ካሜሩን ሁለት የእንግሊዥና ተናጋሪ ክልሎችን ለመገንጠል በሚታገሉ አማፅያን እና በመንግስት  መካከል በሚካሄደው ግጭት ከጎርጎሪያኑ 2017 ዓ/ም ጀምሮ ሀገሪቱ እየታመሰች ትገኛለች።

Kamerun | Preisträger des Deutschen Afrika-Preis 2023 - Esther Omam
የጀርመን የአፍሪቃ ሽልማት ካሜሩንምስል Elisabeth Asen/DW

በሀገሪቱ  ከሚገኙ 10 ክልሎች ውስጥ  በተለይ በአራቱ ከፍተኛ የፀጥታ ችግር ያስከተለ ሲሆን    ሴቶችን ህፃናትን በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ አድርጓል።የ17 ዓመቷ አዳጊ ሞኩ  ፌቨን የችግሩን ስፋት እንዲህ ስትል ታስረዳለች። «በጠዋት ወደ ትምህርት ቤት በምሄድበት ወቅት በአብዛኛው የሚያሰጋኝ ነገር በድንገት መታፈን እና በጥይት መገደል ነው።ምክንያቱም አሁን ባለው ግጭት ሳቢያ ብዙ ግድያዎች አሉ።ወደ ትምህርት ቤት በምንሄድበት ጊዜ ድንገተኛ አፈናን እና ግድያን መስጋት ግዴታ ነው።»

የ16 ዓመቷ ካሜሩናዊት ሹ ፕሪማም ተመሳሳይ ስጋት አላት።«ወደ ትምህርት ቤት ቦርሳየን ይዤ የትምህርት ቤቴን የደንብ ልብስ ለብሼ ለመሄድ እወዳለሁ።ግን አሁን አልችልም።አሁን ወደ ትምህርት ቤት መፅሀፍትና ወረቀቶች ብቻ  ይዤ  በፍርሃት ነው የምሄደው።በጣም አስቸጋሪ ነው።መንግስት አንድ ነገር ማድረግ አለበት።»
በዘንድሮው የጀርመን አፍሪቃ የሰላም ሽልማት አሸናፊ የሆኑት የካሜሩን ሴቶች ይህንን መሰሉን ስጋት ለመቅረፍ እና በሀገራቸው የሰላም ጥረት አድርገዋል። ለዚህም የሀገሪቱ ሴቶቹ በጥር 2021 ዓ/ም  የመጀመሪያውን የሴቶች የሰላም ጉባዔ  አዘጋጅተዋል። የ80 ድርጅቶች  ጥምረት የሆነዉ ይህ ጉባዔ በካሜሩን የሚገኙትን አስር ክልሎችን ያዳረሰ እና እስከ 25 የሚደርሱ የተለያዩ የሴት ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን የሚወክሉ ማህበራት የተካተቱበት ነዉ። 

Kamerun | Preisträger des Deutschen Afrika-Preis 2023 - Marthe Wandou
የጀርመን የአፍሪቃ ሽልማት ካሜሩንምስል Elisabeth Asen/DW

በካሜሩን ታሪክ  በዓይነቱ ትልቅ በተባለው በዚህ ጉባኤ ከሁሉም ክልሎች  የተውጣጡ ከ1,800 በላይ ሰዎች  ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል። ሴቶቹ በዚህ ጉባኤ ባስቸኳይ የተኩስ አቁም ተደርጎ  በአማፅያኑ እና  በመንግስት  መካከል  ውይይት እንዲጀመር እና በግጭቱ በተጎዱ አካባቢዎች የመልሶ ማቋቋም ማዕከላትን ማጠናከር እና ማቋቋምን እንደሚገባ ጠይቀዋል። በእነዚህ ክልሎችም  ለጦርነት ሰለባዎች የስነ-ልቦናእና ማህበራዊ ድጋፍ ማዕከሎች እንዲገነቡ አሳስበዋል። ይህ የሰላም ጥረታቸውም በዘንድሮው የጀርመን አፍሪቃ የሰለም ሽልማት እውቅና አግኝቷል።

በጎርጎሪያኑ 1993 ዓ/ም የተጀመረው  የጀርመን የአፍሪቃ ሽልማት  ለእርቅ፣ ለሰለም እና ለማህበራዊ እድገት ቁርጠኛ የሆኑ አፍሪቃውያን በየዓመቱ  በመሸለም ለ45 ዓመታት በጀርመን እና በአፍሪካ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ ሆኖ ቆይቷል።  ድርጅቱ ባለፈው ዓመትም የኮቪድ 19 የኦሚክሮንን ዝርያ ላገኙ ሁለት ደቡብ አፍሪቃውያን ተመራማሪዎች ሽልማት ሰጥቷል።

ፀሀይ ጫኔ
ነጋሽ መሀመድ