1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

ዓርብ፣ ሰኔ 2 2015

መንግሥት ሀገርን ከከፋ ቀውስ እና ብጥብጥ እንዲታደግ፣ በከፍተኛ ደረጃ እየተሸረሸረ ነው ያለውን የፖለቲካ ምህዳር እንዲያሰፋ እና የዜጎችን ሕይወት እና መብት እንዲጠብቅ ብልጽግና ፓርቲ አባል የሆነበት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጠየቀ።

https://p.dw.com/p/4SOJ7
Infografik Karte Äthiopien AM

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የሰጡት መግለጫ

መንግሥት ሀገርን ከከፋ ቀውስ እና ብጥብጥ እንዲታደግ፣ በከፍተኛ ደረጃ እየተሸረሸረ ነው ያለውን የፖለቲካ ምህዳር እንዲያሰፋ እና የዜጎችን ሕይወት እና መብት እንዲጠብቅ ብልጽግና ፓርቲ አባል የሆነበት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጠየቀ።
ግጭት እና የፖለቲካ አለመረጋጋቶች ዜጎችን ለሞት ፣ ለአካል መጉደል ፣ መፈናቀል እና የሥነ ልቦና ስብራት እየዳረጉ ነው ያለው የፓርቱዎች የጋራ ምክር ቤት በትግራይ ክልል አንፃራዊ ለውጥ ቢታይም በኦሮሚያ ፣ በአማራ እና በጋቤላ ክልሎች ያለው የሰላም ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ በመሆኑ የፀጥታ እና የደህንነት ተቋማት ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ገለልተኝነት ሕግና ሥርዓትን እንዲያስከብሩ ጠይቋል።
"በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ እየተካሄደ ያለው መስጊዶችን የማፍረስ ተግባር በአፋጣኝ እንዲቆም" ሲል የጠየቀው የጋራ ምክር ቤቱ ከተማውን የማልማቱ እንቅስቃሴ አያሌ ዜጎችን ቤት አልባ ማድረጉን በመግለጽ ተግባሩ የሀገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ ፣ በውይይት እና መተማመን ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ጠይቋል።
መንግሥት እና የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች እንዳይገለሉ በማድረግ ኢትዮጵያን ከዘርፈ ብዙ ችግሮች ለማውጣት ያስችላል ያለው ግልጽ እና አሳታፊ ብሔራዊ ውይይት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ዛሬ ባወጣው  መግለጫ ጠይቋል። 
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ በሰጠው መግለጫ ኢትዮጵያ በዘርፈ ብዙ የጸጥታ ፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ችግሮች ውስጥ መውደቋን መገንዘቡን ዘርዝሯል።

የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ዶክተር መብራቱ ዓለሙ በንባብ ያቀረቡት አቋም ግጭቶች በአፋጣኝ እንዲቆሙ፣ የፀጥታ እና ደህንነት አስከባሪዎች ከመቼውም ጊዜ በተሻለ በገለልተኝነት እንዲንቀሳቀሱ ይጠይቃል።

የጋራ ምክር ቤቱ በትግራይ ክልል ተስተውሏል ያለው አንፃራዊ የሰላም ሁናቴ በተለይ እጅግ አሳሳቢ ሆኗል ያለው በኦሮሚያ ፣ በአማራ እና በጋምቤላ ክልሎች ያለው የፀጥታ መደፍረስ በድርድርና ውይይት እንዲፈታም አሳስቧል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት "አያሌ ዜጎችን ቤት አልባ ያደረገው እና ለከፋ ሰብዓዊ ጉዳት የዳረገ" ያለው የሸገር ከተማ የልማት እንቅስቃሴ "ሕግን  የተከተለ ፣ የሀገሪቱን ተጨባጭ  ሁኔታ ያገናዘበ ፣ በውይይት እና በመተማምን ላይ የተመሰረተ እንዲሆን" ሲል ጠይቋል።

የጋራ ምክር ቤቱ በዜጎች ላይ ይፈፀማል ያለው አፈና እና መሰወር ከፍተኛ ሥጋት መደቀኑን በመግለጽ መንግሥት እና የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች እንዳይገለሉ በማድረግ ኢትዮጵያን ከዘርፈ ብዙ ችግሮች ለማውጣት ያስችላል ያለው ግልጽ እና አሳታፊ ብሔራዊ ውይይት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ጠይቋል።

ሰለሞን ሙጬ

ታምራት ዲንሳ

ነጋሽ መሐመድ