1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአቶ በቀለ ገርባ ከፓርቲ ፖለቲካ መገለልና አሜሪካ ጥገኝነት መጠየቃቸው

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 23 2015

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ ከፓርቲው ኃላፊነታቸው እራሳቸውን በማግለል በየናይትድ ስቴትስ ጥገኝነት መጠየቃቸውን በይፋ ዐስታወቁ ። አቶ በቀለ ገርባ በተለይም ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት፦ በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ፓርቲዎች በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችል አውድ እንደሌለ ገልጸዋል ።

https://p.dw.com/p/4Vicg
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ። ፎቶ ከማኅደር ።
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ ከዓመታት በፊት ትግራይ ክልል መቀሌ ተገኝተው መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ንግግር ሲያሰሙ። ፎቶ ከማኅደር ።ምስል DW/M. Haileselassie

ከፓርቲ ኃላፊነታቸው በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸውን ገልጸዋል

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ ከፓርቲው ኃላፊነታቸው እራሳቸውን በማግለል ላለፉት 15 ወራት በቆዩበት በየናይትድ ስቴትስ ጥገኝነት መጠየቃቸውን በይፋ ዐስታወቁ ። አቶ በቀለ ገርባ በተለይም ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት፦ በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ፓርቲዎች በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችል አውድ እንደሌለ ገልጸዋል ። ከእንግዲህ ወደ አገር ቤት መመለስ ለሕይወቴ፣ ለቤተሰቦቼ እና ለትግል ዓላማዬ ፋይዳው አልታየኝም ያሉት አንጋፋው ፖለቲከኛ ፓርቲያቸው በፈለጋቸው ጊዜ በሚችሉት ለማገልገል እንደሚጥሩም አመልክተዋል ። ስለ አቶ በቀለ ከፓርቲው ኃላፊነት እራሳቸውን ማግለል ላይ ማናቸውንም አስተያየት ለመስጠት እንደ ድርጅት እንደሚወያዩበት ለዶይቼ ቬለ የተናገሩት ደግሞ የፓርቲው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና መሆናቸውም ተዘግቧል ።

አንጋፋውን ፖለቲከኛ አቶ በቀለ ገርባን ለጥገኝነት ጠያቂነት ያበቃቸው ውሳኔ ለረዥም ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ በተለይም በፓርቲያቸው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)ተሳትፎ አንቱታን አትርፈዋል። አቶ በቀለ ገርባ በተለይም ለዶቼ ቬለ በሰጡት ቃለምልልስ “እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ በተለይም ባለፉት 12 ዓመታት የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) የአመራርነት ቆይታዬ የራሴን ድርሻዬ ለማበርከትም ሞክሬያለው” ሲሉም ይገልጻሉ፡፡ 

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ። ፎቶ ከማኅደር ።
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ ከዓመታት በፊት ትግራይ ክልል መቀሌ ተገኝተው መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ንግግር ሲያሰሙ። ፎቶ ከማኅደር ።ምስል DW/M. Haileselassie

አቶ በቀለ ለዶይቼ ቬለ እንዳሉት በነዚህ ጊዜያት ውጣውረዶችን አሳልፈዋል፡፡ በተለይም በፖለቲካ ትግላቸው ሂደት ውስጥ ለተደጋጋሚ እስር መዳረጋቸውን የሚገልጹት ፖለቲከኛ በቀለ ገርባ ቤተሰቦቻቸው ላይመየደረሰው ጫና ቀላል እንዳልነበረ አስገንዝበዋል፡፡ 

“አሁን የመጨረሻ ዙር እስራቴን ጨርሼ ወደ አሜሪካ ስመጣ ለሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ነው” ያሉት አቶ በቀለ፤ አንዱ በአሜሪካ በሚገኝ ስማቸውን ግን ባልጠቀሱት ድርጅት ስለ ኢትዮጵያ አሁናዊ የፖለቲካ ሁናቴ የገባቸውን ያህል ለማስረዳት እና ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ እሳቸውን ጨምሮ የትግል አጋሮቻቸው በእስር ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ደምፅ ሆነውናል ያሏቸውን ለማመስገን መሆኑን አስረድተዋልም፡፡ 

ከአንድ ዓመት ከሦስት ወራት በፊት ወደ አሜሪካን አገር የተጓዙበትን እቅዳቸውን በወቅቱ አከናውነው ወደ አገራቸው የመመለስ ዕቅድ እንደነበራቸውም የገለጹልን አቶ በቀለ ነገር ግን “ከእለት ወደ እለት አገር ውስጥ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እየተረጋገጠ መጥቶ በርካቶች የሚታሰሩበት፣ የሚገደሉበት፣ እንዳውም ከእስር ቤት ፈቱ የተባሉ ሰዎች ሁሉ ለዓመታት በእስር የሚማቅቁበት ሁኔታ እየተፈጠረ የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ከድጡ ወደ ማጡ እየሄደ በመምጣቱ ወደዚያ መመለሱ ምንም አስፈላጊነቱ አልታየኝም” ሲሉም ትችታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ “በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ፍጹም አመቺነት የለውም” ያሉት ፖለቲከኛ በቀለ ገርባ ከዚሁ ተነሳ በሄዱበት በአሜሪካ ለመኖር ጥገኝነት ጠየይቀው ምላሹን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል። የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ በቀለ ከፓርቲያቸው ከመልቀቃቸው በፊት ከፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያይተው ከስምምነት የደረሱበት ነጥብ ካለ፤ ብሎም በአመራርነት የሚገለግሉትን ፓርቲ በይፋዊ ደብዳቤም አስገብተው የመልቀቅ ሂደትም ፈጽመው እንደሆነ የተጠየቁት አቶ በቀለ ውሳኔውን ያሳለፍኩት በግሌ ነው የሚል ምላሽ ለዶቼ ቬለ ሰጥተዋል፡፡ ነገር ግን ለቅርብ አለቃቸው የፓርቲው ሊቀመንበር ለሆኑት ለፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ከኃላፊነት ቦታቸው የመሰናበቻ ጥያቄ ያቀረቡበትን ደብዳቤ በኢሜይል እና በሌላ መንገድ መላካቸውን አስረድተዋል፡፡ 

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ። ፎቶ ከማኅደር
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ ከፓርቲው ስለመልቀቃቸው ለቅርብ አለቃቸው የፓርቲው ሊቀመንበር ለሆኑት ለፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ከኃላፊነት ቦታቸው የመሰናበቻ ጥያቄ ያቀረቡበትን ደብዳቤ በኢሜይል እና በሌላ መንገድ መላካቸውን አስረድተዋል፡ምስል Eshete Bekele Tekele/DW

“ወደዚህ አገር ከመጣሁ በኋላ የነበረኝ የፖለቲካ ተሳትፎ የተገደበ ነበር” ያሉት አቶ በቀለ በውጭ አገር ሆነው ሥልጣኑን ይዘው መቀጠለቸው ጠቃሚ ስላልሆነ እራሳቸውን ከፓርቲው ለማግለል መወሰናቸውንም ተናግረዋል። 

“የፖለቲካ ፓርቲ የሚደራጀው ከህዝብ ጋር በቅርበት አብሮ በመስራት ለስልጣን ተፎካክሮ ያመኑበትን ፖሊሲ ለማስፈጸም ነው፡፡ አሁን ህዝቡን አግኝቶ መምራት የሚያስችል ሁኔታ የለም፡፡ በቅርቡ ሰላማዊ ምርቻም ይደረጋል ተብሎ ሚታሰብበት ሁኔታ አይታይም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢሮዎችም በየቦታው ተዘግተው የፖለቲካ እንቅስቃሴ በቆመበት የፖለቲካ ተሳትፎ ማድረግ አይቻልም፡፡ ስለዚህ እኔ አሁን ወደዚያም ብመለስ ምንም አይነት የፖለቲካ ተሳትፎ ማድረግ ሚያስችል ሁኔታ አለመኖሩን ነው ያስረዳኝ፡፡ ለዚህም መንግስት ያለኝን ተቃውሞ እየገለጽኩ ስለቆየሁ ወደዚያ አገር መመለስ ባለኝ በገገጠመኝ ልምድ በዚያ መንግስት በዝመታ ይታለፋል ተብሎ ስለማታመን ይህ ለግል ሕይወቴም ለቤተሰቤም ሆነ ለምታገልለት ኣላማ ጠቃሚ ነው ብዬ አላመንኩም” ሲሉም ለጥገኝነት ጠያቂነቱ ያበቃቸውን ምክንያትም በዝርዝር አብራርተዋል፡፡ 

አቶ በቀለ ገርባ ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ ተፈጥሮ የነበረውን ሁከት ተከትሎ በቁጥጥር ሥር ውለው ለ18 ወራት በእስር ላይ ቆይተው ከተለቀቁ በኋላ ነበር ወደ አሜሪካ ተጉዘው በዚያው የቆዩት። 

አቶ በቀለ ለኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ)ም ሆነ በዚያ ውስጥ ላሉ አመራሮች ትልቅ አክብሮት እንዳላቸው ገልጸው ፓርቲውም ለመልቀቅ የተገደዱት በውጪ ሆነ በአመራርነት የነቃ ተሳትፎ ማድረግ አዳጋች በመሆኑ ብቻ መሆኑንና ሌሎች እድሉን እንዲያገኙም በማሰብ ጭምር መሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡ 

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ። ፎቶ ከማኅደር ።
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ ከዓመታት በፊት ትግራይ ክልል መቀሌ ተገኝተው መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ንግግር ሲያሰሙ። ፎቶ ከማኅደር ።ምስል DW/M. Haileselassie

አቶ በቀለ ጓዶቻቸውንም “የህዝባቸውን ጥቅም አሳልፈው የማይሰጡ ቆራጥ ታጋዮች መኖራቸውን ነው እኔ የማውቀው እስከ መጨረሻውም በመተማመን አገሪቱን ወደ ፊት መግፋት በሚስችል የመወያየት ፖለቲካ ላይ የሚተማመኑ ሰዎች መሆናቸውን ነው የምረዳው” ብለው አሞካሽተዋቸዋል፡፡ ከፓርቲ ኃላፊነታቸው ግን ከዛሬ ጀምረው በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸውን ያስረዱት ፖለቲከኛ ወደፊት ግን እንዳስፈላጊነቱ ፓርቲያቸው ለትብብር ብጠይቃቸው ለመተባበር ዝግጁ መሆናቸውን አስረድተዋልም፡፡ 

አቶ በቀለ ስለወደፊት የሕይወት ገጽታና ዓላማቸውም ተጠይቀው፤ ሙስናና ስርዓት አልበኝነት ተንሰራፍቶበታል ባሉት አገር ውስጥ የመታገያ ብቸኛው መንገድ ፖለቲካዊ ብቻ መሆን አይገባውም ብለዋል። እናም ከአንድ ፖለቲካ ፓርቲ ገደብ ወጥተው ከሰብኣዊ መብት ተከራካሪ ተቋማት እና በግል በመንቀሳቀስ በየትኛውም ቦታ የሰው ልጆች መብቶች ሲነኩ ለሁሉም እኩል መታገል እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ