1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራና የትግራይ ሕዝቦች ግንኙነት

ዓርብ፣ ጳጉሜን 4 2014

የደሴ ከተማ አስተያየት ሰጪው እንደሚሉት በሁለቱ ህዝቦች መካከል የተፈጠረው ቁርሾ በቀላሉ መፈታት የሚችል ባለመሆኑ ጠንካራ የማግባባትና የማወያየት ስራ ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግስት፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት አመራሮች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት አባቶች ከፍተኛ የማግባባት ስራ ሊሰሩ ይገባል፡፡

https://p.dw.com/p/4Gdvq
Äthiopien | Yilkal Kefale
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ጦርነቱ የአማራና የትግራይ ሕዝብን አቃቅሯል-አስተያየት ሰጪ

                                   
የትግራይ ህዝብ ለአማራ ጎረቤቱ ወንድም  መሆኑንና አብሮ ማድግና አብሮ መኖር የሚፈልግ እንደሆነ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ።ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ የአዲሱን ዓመት ዋዜማ ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት የሁለቱ ሕዝቦች ወድማማችነት እንደሚቀጥል አስታዉቀዋል።የደሴና የደብረማርቆስ  ከተሞች  ነዋሪዎች የርዕሰ መስተዳድሩን አስተያየት በመደገፍና በመቃወም እሁለት የተከፈለ አስተያየት ሰጥተዋል።አንድ የደሴ ከተማ ነዋሪ ጦርነቱ የፈጠረው ቅራኔ በአማራና በትግራይ ህዝቦች መካከል በቀላሉ ሊሽር የማይችል  ጠባሳ አስቀምጠዋል ብለዋል፡፡
“ ይህ ጦርነት በእርግጠኝነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ያለዚያም አንድ ዓመትም ቢጨምር መቋጨቱ አይቀርም፣ ግን በህዝቦች መካከል ጥሎት የሚያልፈው ጠባሳ እንዲሁ በቀላሉ የሚገመት አይደልም፣ ዝም ብሎ የሚወራው ህዝቡና ህዝቡ አይለያይም፣ ህዝቡና ህዝቡ አንድ ነው በተጨባጭ ግን ልጆቻቸውን ያጡ፣ ወንድሞቻቸውን ያጡ፣ ንብረቶቻቸውን የወደመባቸው፣ ራሳቸው የቆሰሉ፣ የተጎዱ በትግራይም፣ በኢትዮጵያም ህዝብ አለ፤ ስለዚህ ይህ ትውልድ እስካለ ድረስ ያ ጠባሳ በቀላሉ ሊድን አይችልም” ነው ያሉት፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ትናንት አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት ግን የትግራይና የአማራ ህዝቦች ወንድማማቾች ናቸው አብረው ማደግ ይፈልጋሉ ብለዋል፡፡
አንድ የደብረማርቆስ ነዋሪም በሁለቱም ህዝቦች ላይ ወንጀል የፈፀሙ አካላት በህግ እስከተጠየቁ ድረስ የትግራይና የአማራ ህዝቦች አይነጣጠሉም፣ በርካታ የትግራይ ተወላጆች  ተፈናቅለውና ወሰን ተሸግረው ወደ አማራ ክልል መግባታቸው ማሳያ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ህዝቡ በጋብቻ፣ በጎረቤትነት፣ በባህል፣ በአኗኗርና በስነልቦና የማይነጣጠል በመሆኑ ለትውልድ የሚሻገር ጥላቻ ሊኖር እንደማይችል አብራርተዋል፡፡ 
የደሴ ከተማ አስተያየት ሰጪው እንደሚሉት በሁለቱ ህዝቦች መካከል የተፈጠረው ቁርሾ በቀላሉ መፈታት የሚችል ባለመሆኑ ጠንካራ የማግባባትና የማወያየት ስራ ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግስት፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት አመራሮች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት አባቶች ከፍተኛ የማግባባት ስራ ሊሰሩ ይገባል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሰሜን ወሎ ዞን አንዳንድ አካባቢዎች ዛሬም ውጊያ እንዳለ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል ፡፡
“ከቆቦ በስተምዓራብ በኩል ተኩለሽ፣ ጊዶ፣ በዚያ ኃይለኛ የሆነ የተኩስ ልውውጥ አለ፣ በአላዉሀ በኩል ደግሞ ትልልቅ የመሳሪያ ድምፅ ነው ይሰማ የነበረው መድፍ ብቻ፤በተኩለሽ በኩል አሁንም ውጊያ አለ ከትናንት ጀምሮ አላረፈም”
ኮቦ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል በህውልናችን ላይ የተቃጣውን ወረራ ለመቀልበስ ውጊያ በተለያዩ አካባቢዎች መቀጠሉን አመልክተዋል፡፡
“ጦርነት የማይፈለግና የማይመረጥ አማራጭ መሆኑን ያወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ህልውናን ለማስጠበቅ ሲባል በተጀመረው ዳግም ወረራ ባሉት ጦርነት የተጀመረውን ጥቃት ከፍተኛ መስዋዕትነት ተከፍሎም ቢሆን የመከላከያ ሰራዊት፣ የአማራና የአፋር ጥምር ኃይሎች አኩሪ ድል እየተጎናፀፉ ነው” ብለዋል ዶ/ር ይልቃል፡፡ የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎችና የህወሓት ተዋጊዎች ላለፉት ሁለት ዓመታት እያካሄዱት ባለው ጦርነት የብዙዎች ህይወት አልፏል፣ በርካቶች ያካል ጉዳት ደርሶባቸዋል በሚሊዮን የሚቆጠሩት ደግሞ ለእንግልትና ለችግር ተዳርገዋል፡፡ 
ዓለምነው መኮንን

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ