1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት መግለጫ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 1 2016

1445ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል ሲከበር ሙስሊሙ ማህበረሰብ የተፈናቀሉ ወገኖችን፣ ወላጆቻቸው የሞቱባቸውንና ደካሞችን በመርዳትና በማገዝ መሆን እንዳለበት የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አስተወቀ፡፡ ሰሞኑን “ማንነታቸው ያልታወቀ” ያላቸው ታጣቂዎች በባሕር ዳር ከተማ የፈፀሙትን ግድያም ምክር ቤቱ አውግዟል፡፡

https://p.dw.com/p/4eZoh
Äthiopien Oberster Rat für Islamische Angelegenheiten der Region Amhara (ARIASC)
1445ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል ሲከበር ሙስሊሙ ማህበረሰብ የተፈናቀሉ ወገኖችን፣ ወላጆቻቸው የሞቱባቸውንና ደካሞችን በመርዳትና በማገዝ መሆን እንዳለበት የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አስተወቀ፡፡ ምስል Alemnew Mekonenen/DW

የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛው ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የሰጠው መግለጫ

1445ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል ሲከበር ሙስሊሙ ማህበረሰብ የተፈናቀሉ ወገኖችን፣ ወላጆቻቸው የሞቱባቸውንና ደካሞችን በመርዳትና በማገዝ መሆን እንዳለበት የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አስተወቀ፡፡ ሰሞኑን “ማንነታቸው ያልታወቀ” ያላቸው ታጣቂዎች በባሕር ዳር ከተማ የፈፀሙትን ግድያም ምክር ቤቱ አውግዟል፡፡

ነገ ረቡዕ የሚከበረውን 1445ኛ ዓመት የኢድ አልፈጥር በዓል አስመልክቶ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ትናንት መግለጫ ሰጥቷል፡፡ የምክር ቤቱ ፕረዚደንት ሸክ ጃዋር መሀመድ ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች “እንኳን አደረሳችሁ” ብሏል፡፡

ጾምና ፈተናው በተፈናቃዮች መጠለያ

የምክር ቤቱ ምክትል ፕረዚደንት ሸክ መሀሙድ አኑዋር በበኩላቸው ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከበር የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብና በማካፈል ሊሆን እንደሚገባ ገልጠዋል፡

“ሙስሊሙ ማህበረሰብ ኢድ አልፈጥር በዓልን በሚያከብርበት ጊዜ የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን፣ ወላጅ የሌላቸው ህፃናትን፣ በችግር በድንኳን ውስጥ ያሉትን ማሰብና በዓሉ የሁሉም ማህበረሰብ እንዲሆን አደራ እንላለን፤ የተለመደውን አብሮነታችንን፣ ከአባቶቻችን ለወረስናት አገራችን የሰላም ድልድይ ሰርተን ለቀጣዩ ትውልድ እስክናስተላልፍ ድርስና ከአባቶቻችን የተረከብነውን ኃላፊነት እስክንወጣ ድረስ ይህ ትውልድ አንድነትንና ሰላምን የሚያስተጋባበት የኢድ አልፈጥር በዓል ይሆናል ብለን እናስባለን፡፡” ብለዋል፡፡

የአማራ ክልልእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ሊያከናውን ያቀደው የልማት ስራዎች ምስል
የአማራ ክልልእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በርካታ የልማት ስራዎች ለማከናወን አቅዷል።ምስል Alemnew Mekonenen/DW

ሸክ ሙሀሙድ በመግለጫቸው በዓሉ ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ የፈጣሪ ኃያልነት የሚገለጽበት እንዲሆንም አሳስበዋል፡፡

ምክር ቤቱ በጽሁፍ ባሰራጨው ሌላ መግለጫ ደግሞ፣ “መጋቢት 29/2016 ዓ ም በባሕር ዳር ከተማ ቀበሌ 14 የመቅሪብ ሶላት ሰግደው ወደ ቤታቸው በሚሄዱ አማኞች ላይ ማንነታቸው ያልታወቁ የታጠቁ ኃይሎች 4 የአንድ ቤተሰብ አባላትንና አንድ ጎረቤታቸውን በመግደል ተሰውረዋል” ብሏል፡፡

ይህን ድርጊት አስመልክተው የምክር ቤቱ ምክትል ፕረዚደንት ሸክ ሙሀሙድ የድርጊቱን ፈፃሚዎች ለህግ ለማቅረብ ሁሉም አካል እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል፡፡በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እየተሰራ ነው ተባለ

“... ወንድሞቻችን ሶላት ሰግደው ሲወጡ ከመስጊድ በር ላይ ግድያ የፈፀመው አካል ከህግ ፊት ቀርቦ እንድናየው፣  መረጃ ያለው  ሁሉ ለክልሉ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትና ለሚመለከተው አካል እንዲጠቁምና ትብብር እንዲያደርግ አንጠይቃልን፣ ሀገራችንን ከመጥፎ ነገር ፈጣሪ ይጠብቅልን፡፡” ነው ያሉት፡፡

ድርጊቱ ከዝርፊያ ጋር የተገናኘ ሳይሆን እንደማይቀር ያመለከተው መግለጫው የማንንም እምነትና ብሔር ግን አይወክልም ብሏል፡፡

ግድያ፣ ዘረፋ፣ መፈናቀልና ወከባ በክልሉ ከተሞች እየሰፋ መምጣቱን ያመለከተው መግለጫው መንግስት፣ ህዝቡ፣ የሁሉም ኃይማኖት አማኞች፣የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባቶችና የሚመለከታቸው አካላት እርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቋል፡፡

ዓለምነው መኮንን

ታምራት ዲንሳ

ሸዋዬ ለገሰ