1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የብዝሃ ሕይወት እና የማኅበረሰብ መብቶች ተሟጋቹ ሲታወሱ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 19 2015

ለአካባቢ ተፈጥሮ ባበረከቱት አስተዋጽኦ ከሀገራቸው አልፈው በዓለም መድረክ ከፍተኛ ተደማጭነትን ያተረፉት፤ ዶክተር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር ባለፈው ሳምንት ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ተሰምቷም።

https://p.dw.com/p/4PKlt
Dr. Tewolde Berhan Gebre Egziabher
ምስል Privat

የብዝሃ ሕይወት እና የማኅበረሰብ መብቶች ተሟጋቹ ሲታወሱ

በ83 ዓመታቸው መጋቢት 12 ቀን 2015 ዓም ከዚህ ዓለም ድካም ያረፉት የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪ፤ በዓለም መድረክም የድሀ ሃገራት የተፈጥሮ ሀብት ተሟጋች የነበሩት ዶክተር ተወልደ ብርሃን ለአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ዘርፈ ብዙ መሆኑ ይነገራል።

አቶ ሰሎሞን ኃይለ ማርያም ዶክተር ተወልደ ብርሃን አስመራ ዩኒቨርሲቲ ይሠሩ በነበረት ጊዜ ከ1981 ዓም ጀምሮ ነው ከቤተሰቡ ጋር አብሮ መኖር የጀመረው። በቤታቸው የኖረ አብሯቸውም ለዓመታት አብሯቸው ሠርቷል። ከአራት ዓመታት በፊት ቀድመዋቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ባለቤታቸው ሱዛን በርኔል ኤድዋርድስ ጋር ይሠራ በነበረው የደን ልማት ሥራ ምክንያት በመጀመሪያ የተዋወቀው አቶ ሰሎሞን ጥንዶቹ በጋራ በጀመሩት በጓሮ የሚሰናዳ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ከመነሻው ተሳትፏል። አቶ ሰሎሞን በቆይታውም ዶክተር ተወልደ ብርሃን ከባለቤታቸው ጋር በመሆን በመኖሪያ ቤታቸው የዘላቂ ልማት መካነ ጥናት ፕሮጀክትን ሲያቋቁሙ አብሮ መሥራቱን ቀጠለ። «የተጀመረው አዲስ አበባ ላይ ነው ቤት ውስጥ ሙከራ ተደረገ ብስባሽ ማዘጋጀት። ዋናው ችግር ማዳበሪ ነው። የአፈር ለምነትን መጠበቅ ነው።»

Susan Edwards Gründerin des Institute for Sustainable Development Ethiopia (ISD)
ዶክተር ተወልደ ብርሃን እና ባለቤታቸው በሚንከባከቡት መስክ ላይምስል ISD

በቤት ውስጥ የተሞከረው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት የማዳበሪያ ግዢ የኑሮ አቅሙን ለሚፈታተነው አርሶ አደር የሚደርስበት መንገድም ተቀየሰ። ለዚህም ትግራይ ክልል ውስጥ የተሠሩ ሥራዎችን በማሳያነት ይጠቅሳል።

ዶክተር ተወልደ ብርሃን አንድ አካባቢን ከሰው እና እንስሳ ንክኪ ከልሎ በማሳረፍ የጠፉ ተክሎች መልሰው እንዲለመልሙ፤ በአፈር እና ውኃ ጥበቃው በኩልም እንዲሁ ለሌሎች አካባቢዎች ምሳሌ የሚሆኑ ሥራዎች እንዲሠሩ ግንባር ቀደሙን ሚና መጫወታቸው ይነገርላቸዋል። በዚህ ረገድ ትግራይ ላይ የታየውን አቶ ሰሎሞን ተአምር ይለዋል።  

በኢትዮጵያ የአረንጓዴ ጀግና ተብለው የተሸለሙት ዶክተር ተወልደ ብርሃን፤ በሀገር ውስጥ ከሠሩት አልፎ በአፍሪቃ ብሎም በዓለም ደረጃ የብዙዎችን ትኩረት ስበው፤ ብዙዎችም ሃሳባቸውን እንዲከተሉ ማድረጉ እንደተሳካላቸው ዶክተር ሚሊየን በላይ የአላያንስ ፉድ ሶቨርኒቲ ኢን አፍሪካ የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ኃላፊ ገልጸውልናል። ድርጅታቸው የተለያዩ 41 የሚሆኑ አፍሪቃ ውስጥ ያሉ የአርሶ አደሮች፤ አርብቶ አደሮች፤ የዓሣ አስጋሪዎች እና ሌሎችም ማኅበራት ስብስብ ሲሆን ዋና ትኩረቱም የአፍሪቃ እርሻ ምርታማ ብቻ ሳይሆን የኅብረተሰቡን ጤና ያማከለ እንዲሆን ለማድረግ የሚሠራ ነው። ዶክተር ሚሊየን የዶክተር ተወልደ ብርሃንን አስተዋጽኦ በሦስት ከፋፍለውታል። «አንደኛ ደረጃ ሲያስተምሩበት በነበሩበት ዩኒቨርሲቲ የባዮሎጂ ዲፓርትመንት ሲመሰረት ከመስራቾቹ አንዱ ናቸው፤ በሁለተኛ ደረጃ ኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን እንዲመሠረት ከማድረግ ጀምሮ የአካባቢ ፖሊሲ እና ስትራቴጂ እንዲኖራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፤ ሌላው ዓለም ደግሞ የሚያውቃቸው በአፍሪቃ ደረጃ አፍሪቃን ወክለው የሠሩት ሥራ ነው።» በዓለም አቀፍ መድረክ ያላቸውን ተቀባይነት በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ ያነሱት ዶክተር ሚሊየን፤ እንዲያም ሆኖ በዓለም አቀፍ መድረክ ድርድርን በተመለከተ የሚያውቁትን ሳይጽፉ በማለፋቸው መቆጨታቸውን አልሸሸጉም።

Susan Edwards Gründerin des Institute for Sustainable Development Ethiopia (ISD)
ጥንዶቹ የአረንጓዴ ጀግኖች ዶክተር ተወልደ ብርሃን እና ባለቤታቸው ሱ ኤድዋርድስምስል ISD

ዶክተር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር «የምድራችን ጀግና»  እና «የኢትዮጵያ ሳይንቲስት» በተሰኙ መጻሕፍት ታሪካቸው ተሰንዷል። እነዚህን ሁለት መጻሕፍት ያዘጋጀው ጋዜጠኛ እና ደራሲ ዘነበ ወላ፤ ስለ ዶክተር ተወልደ ብርሃንን የሚያወሱትን ሥራዎቹን ከማዘጋጀቱ አስቀድሞ ወደ 20 ዓመታት ገደማ በቅርበት እንደተከታተላቸው ለዶቼቬለ ገልጿል። በትግራይ አድዋ ከተማ አቅራቢያ በ1932 ዓ,ም የካቲት 12 ቀን የተወለዱት ዶክተር ተወልደ ብርሃን በቤታቸው ትምህርትን ጀምረው የመጀመሪያ ዲግሪ እስኪያገኙ በሀገር ውስጥ በጥሩ ውጤት ትምህርታቸውን ገፍተዋል። ከዚያም ለሁለተኛ ዲግሪያቸው ወደ እንግሊዝ ሀገር በሄዱበት ዩኒቨርሲቲ ውጤታቸውን ተመልክቶ በቀጥታ የዶክትሬት እንዲጀምሩ በማድረጉ ጥናታቸውን በስነምህዳር ላይ በማድረግ ማጠናቀቃቸውንም አመልክቷል። በወጣትነት ዕድሜና ዩኒቨርሲቲ የመምህርነት ዘመናቸው አስመራ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ብዙዎች ያወሱላቸዋል። በተፈጥሮ ጥበቃ ረገድ ላበረከቱት ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦም በተለያዩ ዓመታት እውቅናና ሽልማቶችን አግኝተዋል።

Dr. Tewolde Berhan Gebre Egziabher
ዶክተር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር ምስል Privat

ጋዜጠኛ እና ደራሲ ዘነበ ስለቤተሰባቸው ሲገልጽ፤ ከአብራካቸው የተከፈሉ ሦስት ልጆች እንዳሏቸው እና የልጅ ልጆችንም ለማየት መታደላቸውን አንስቷል። ከዚህም ሌላ ከ50 በላይ የችግረኛ ቤተሰብ ልጆችን እስከሚፈልጉበት የትምህርት ደረጃ ድረስ ማስተማራቸውን፤ የጤና ችግርም ሆነ የአካል ጉዳት ያላቸውንም ሲረዱ መኖራቸውን ዘርዝሯል። ዶክተር ተወልደ ብርሃን በሀገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ የሚችሉትን ሲያደርጉ ዕድሜያቸውን ገፍተዋል። እንደ እሳቸው ሁሉ የባለቤታቸውም አስተዋጽኦ ዛሬም ይወሳል። በጥቂት ዓመታት ልዩነት ተከታትለው ወደማይቀርበት ዓለም ተሻገሩ። ሥራቸውን ግን ትውልድ ይዘክረዋል። ለቃለ መጠይቁ የተባበሩን እናመሰግናለን።

ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር