1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቤኒሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ ፓርቲ አመራሮች ውዝግብ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 2 2015

ስምምነቱ በሰላም እና ልማት ላይ በጋራ ለመስራት ያለመ መሆኑም ተገልጸዋል፡፡ ሆኖም የቤኒሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ (ቤ.ህ.ነ.ን.) የፓርቲውን ሊቀ መንበር ከኃላፊነት ማንሳቱን ገልጸዋል፡፡ ሊቀመንበሩ ከፓርቲው የታገዱት ሐምሌ ፓርቲው ያልተነጋገረበትና ያላጸደቀውን ስምምነት ከክልሉ መንግስት ጋር ተፈራርመዋል በሚል ነው፡፡

https://p.dw.com/p/4Uu2a
Äthiopien Assosa
ምስል Negassa Dessalegn/DW

«የቤኒሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ ፓርቲ ስምምነቱን አይቀበልም» የፓርቲዉ ም/ሊቀመንበር

ፓርቲው በክልሉ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱት 7 ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ ሲሆን ሐምሌ 26/2015 ዓ.ም ክልሉ መንግስት ጋር በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ ስምምነቱ በሰላም እና ልማት ላይ በጋራ ለመስራት ያለመ መሆኑም ተገልጸዋል፡፡ ሆኖም የቤኒሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ(ቤ.ህ.ነ.ን.) ትናንት ይፋ ባደረገው መረጃ የፓርቲው ሊቀ መንበር የሆኑትን አቶ አብዱልሰላም ሸንግል ከኃላፊነት ማንሳቱን ገልጸዋል፡፡ ሊቀመንበሩ ከፓርቲው የታገዱት ሐምሌ 26/2015 ዓ.ም ፓርቲው ያልተነጋገረበትና ያላጸደቀውን ስምምነት ከክልሉ መንግስት ጋር ተፈራርመዋል በሚል ነው፡፡ አቶ አብዱልሰላም ሸንግል በበኩላቸው በድርጅቱ ደንብ መሰረት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ሊቀመንበሩን መሻር እንደማይችል ገልጸዋል፡፡ በተደረሰው ስምምነት መሰረት በሁለት ወረዳዎች ውስጥ በጉዳዩ ላይ ውይይት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ የቤኒሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ ፖለቲካ ፓርቲ በምርጫ ቦርድ ተመዝግቦ በክልሉ ውስጥ የሚንቀሳቀስ ሲሆን በ2013 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ ላይ ተሳትዋል፡፡

ሐምሌ 26/2015 ዓ.ም በክልሉ በሰላምና ልማት እንዲሁም በልዩ ልዩ ተግባራት ላይ ከመንግስት ጋር ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ ስምምነቱን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን እና የቤኒሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ የፖለቲካ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አብዱልሰላም ሸንግል ተፈራርመዋል፡፡ በስምምነቱ ከክልል እስከ ወረዳ ባሉ የአስተዳደር መዋቅሮች ለፓርቲው አባላት ኃላፊነት እንደሚሰጣቸው ተገልጸዋል፡፡ ሆኖም የቤኒሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ ፓርቲ በምክትል ሊቀመንበሩ ፊርማ በተሰራጨው ደብዳቤ ሊቀመንበሩ ድርጅቱን ለማፍረስ በመስራታቸው ከፓርቲው እንዲነሱ መደረጉንና ስምምነቱን እንደማይቀበሉ አብራርተዋል፡፡ የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መሐመድ እስማኤል የፓርቲው ስራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ ሳያውቀውና ሳይወያይበት የፓርቲው ሊቀመንበር ከድርጅቱ ደንብ ውጭ ከመንግስት ጋር ስምምነት ማድረጉን አመልክተዋል፡፡

ፓርቲውን በመወከል ስምምነቱን የፈረሙት አቶ አብዱሰላም ሸንግል የተደረሰው ስምምነት በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እና ለህዝብ ልማት የጎላ ፍይዳ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ሐምሌ 26/2015 ዓ.ም ከክልሉ መንግስት ጋር የተደረሰው ስምምነትንም አብራርተዋል፡፡ በፓርቲያቸው ስም ከዚህ ቀደም በርካታ አባላት በፖለቲካ አመለካከትና ተሳትፎአቸው ሲታሰሩ መቆየታቸውን ገልጸው በስምምነቱ መሰረት ከስራ የታገዱ ወደ ስራቸውን እንዲመለሱ መስማማታቸውን አክለዋል፡፡ የፓርቲያቸው ስራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ ስምምነቱን አለመቀበሉንና ከሊቀ መንበርነት ማገዱን በተመለከተም በሰጡት ምላሽ የተወሰኑ ሰዎች የተደረሰውን ስምምነት ወዳልተፈለገ አቅጣጫና ግጭት ለማምራት ያደረጉት ሙከራ ነውም ብለዋል፡፡

የክልሉ መንግስትና ፖለቲካ ፓርቲው የደረሱት ስምምነትን በተመለከተና የቤ.ህ.ነ.ን ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስምምነቱን መቃወሙ፤ በስምምነቱ ላይ ተጽህኖ ሊያደርስ ይችል እንደሆነና ተፈጻሚ ስለመሆኑ ከመንግስት በኩል ተጨማሪ መረጃ ለማካተት ከክልሉ ብልጽግና ፓርቲ፣ ፖሊስ ኮሚሽንና ሌሎችም የጸጥታ ዘርፍ ተቋማት መረጃ ለማግኘት ያደረኩት ጥረት አልተሳካም፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚንቀሳቀሱ መካከል ቤ.ህ.ነ.ን ጨምሮ የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ የፖለቲካ ድርጅቶች ከክልሉ መንግስት ጋር ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ በክልሉ ታጥቆ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት ሁለት የታጣቂ ቡድኖች ጋርም በዚህን ዓመት በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረት ወደ ህብረሰተቡ ተቀላቅሏል።

ነጋሳ ደሳለኝ

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ