1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማክሰኞ፤ ግንቦት 6 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የዓለም ዜና

ማክሰኞ፣ ግንቦት 6 2016

አርእስተ-ዜና፦ ሰሜን ሸዋ፥ ቀዎት እና ሞላሌ ወረዳዎች የድሮን ጥቃት፤ ጋምቤላ፥ ኢታንግ የ10 ሰዎች ሕይወት በግጭት ማለፉ ተገለጠ፤ አ.አ፥ ብርቱ የእሳት አደጋ ንብረት አወደመ፤ ራፋ፥ እሥራኤል 76ኛ የነጻነት ቀኗን ባቀረበችበት ቀን ውጊያ በጋዛ፤ ኪዬቭ፥ የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዩክሬንን ድንገት ጎበኙ፤ ሙምባይ፥ ግዙፍ የማስታወቂያ ሠሌዳ ተደርምሶ ቢያንስ 14 ሰዎች ገደለ

https://p.dw.com/p/4fqpJ

*በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በቀዎት ወረዳ እና ሞላሌ ወረዳዎች ውስጥ እሁድ ግንቦት 04 ቀን፣ 2016 ዓ.ም. ተፈጸመ በተባለ የሰው አልባ ጢያራ (ድሮን) ጥቃት ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተነገረ ።

*በጋምቤላ ክልል ኢታንግ ልዩ ወረዳ ውስጥ ትናንት እና ባለፈው እሁድ በተከሰተ ግጭት የፀጥታ ኃይላትን ጨምሮ  የነዋሪዎች  ሕይወት ማለፉ ተገለጠ ። የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ሦስት የፀጥታ ኃይላትን ጨምሮ 9 ሰዎች በግጭቱ መሞታቸውን ተናግሯል ።  

*ድንገት ሳይጠበቁ የዩክሬን መዲና ኪዬቭ ዛሬ የተገኙት የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ሀገራቸው ለዩክሬን ተጨማሪ ወታደራዊ ድጋፍ እንደምታደርግ ቃል ገቡ ። የውጭ ጉዳዩ ሚንስትሩ ጉብኝት እና ድጋፍ የተሰማው ሩስያ ጥቃቷን ዩክሬን ላይ ባጠናከረችበት ወቅት ነው ።

ዜናው በዝርዝር

ሰሜን ሸዋ፥ ቀዎት እና ሞላሌ ወረዳዎች የድሮን ጥቃት

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በቀዎት ወረዳ እና ሞላሌ ወረዳዎች  ውስጥ እሁድ ግንቦት 04 ቀን፣ 2016 ዓ.ም. ተፈጸመ በተባለ የሰው አልባ ጢያራ (ድሮን) ጥቃት ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተነገረ ። አንድ የአከባቢው ነዋሪ የባለፈው እሁድ የቀዎት ወረዳው የድሮን ጥቃት የተነጣጠረው በርግቢ በሚባል አከባቢ ት/ቤት ላይ መሆኑን ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል ።

«በርግቢ ይፍራታ እና ግድሜ አለ አይደለም ይፋት፤ ከአጣዬ በላይ፤ ወደ ሸዋ ሮቢት ሲል ትምሕርት ቤት ነው ። በሚገርምህ ነገር መምህራን ናቸው ያለቁት እኮ ። እንዳለ ነው የመታቸው ። እንዳጋጣሚ ቤተሰቦቼ እዚያ አካባቢ ነበሩ፥ በጣም ነው ያዘኑት ።»

ስለጥቃቱ መፈጸም በመንግስት በኩል የተባለ ነገር የለም ። ዶቼ ቬለ ለሰሜን ሸዋ ዞን ኮሚዩኒኬሽን እንዲሁም ለክልሉ እና ለፌዴራል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ባለስልጣናትም ደውሎ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረትም ለዛሬ አልሰመረም ። መንግስታዊው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን መረጃው እንዳላቸው አረጋግጠው የምርመራ ሂደቱ ግን ገና በጅምር ላይ ነስለመሆኑ መናገራቸውን የአዲስ አበባ ወኪላችን ሥዩም ጌቱ ዘግቧል ።

ጋምቤላ፥ ኢታንግ የ10 ሰዎች ሕይወት በግጭት ማለፉ ተገለጠ

በጋምቤላ ክልል ኢታንግ ልዩ ወረዳ ውስጥ ትናንት እና ባለፈው እሁድ በተከሰተ ግጭት የፀጥታ ኃይላትን ጨምሮ  የነዋሪዎች  ሕይወት ማለፉ ተገለጠ ። የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ሦስት የፀጥታ ኃይላትን ጨምሮ 9 ሰዎች በግጭቱ መሞታቸውን ተናግሯል ።  አንድ የአካባቢው ነዋሪ በበኩላቸው  ኑዌሮች በሚኖሩበት ቀበሌ የ10 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ለዶይቸ ቬለ ገልጠዋል ።

«ኢታንግ ልዩ ወረዳ ሆኖ መኮድ ቀበሌ እና ሌር ቀበሌ ናቸው ። ኑዌር የሚገኙበት ማለት ነው ። በአንዴ አርፒጂ ነው መሰለኝ ዐሥር ሰው ወዲያ ው እንደሞተ ነው መረጃ ያለኝ ። ወደ 17 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል ። ከመካከላቸው አንደናው ሞቷል ። »

በወረዳው አንድ ቀበሌ ውስጥ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ የያዙ የተባሉ አካላት ሰዎች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ ከፀጥታ ኃይላት ጋር ግጭት መከሰቱም ተነግሯል ።  ጥቃቱ ደረሰ የተባለባት የኢታንግ መንደር ከጋምቤላ ከተማ በ46 ኪ.ሜ ርቀት ገደማ ላይ ትገኛለች ። በጋምቤላ ክልል ኢታንግ ልዩ ወረዳ በተለያዩ ወቅቶች በሚከሰቱ ግጭቶች ለበርካታ ሰው ሕይወት ማለፍና ንብረት ውድመት ምክንያት እየሆነ እንደሚገኝ ነዋሪዎች  ገልጠዋል ። የአሦሳ ወኪላችን ነጋሣ ደሳለኝ በዜና መጽሄት ዝርዝር ዘገባ አለው ።

አ.አ፥ ብርቱ የእሳት አደጋ ንብረት አወደመ

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 ወይም ኢንዱስትሪ መንደር ተብሎ በሚታወቀው አከባቢ ትናንት ከሌሊቱ 10 ሰዓት ገደማ ጀምሮ ብርቱ የእሳት አደጋ መከሰቱ ተገለጠ ። የእሳት አደጋው በአንድ ሻማ ፋብሪካ እና ከአጠገቡ በሚገኝ ጋራዥ ላይ ጉዳት ማድረሱን የከተማው እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ንጋቱ ማሞ ተናግረዋል ።

«አክማ የሚባል ሻማ ፋብሪካ አብዛናው ክፍል ወድሟል ። እንደዚሁም አጠገቡ የተሽከርካሪ ጥገና አገልግሎት የሚሰጥ ጋራዥ አለ፥ ለጥገና ገብተው የነበሩ አምስት ተሽከርካሪዎችም ብርቱ ጉዳት ደርሶባቸዋል ።»

በፋብሪካው የነበሩ ጥሬ ዕቃዎችና ተቀጣጣይ ኬሚካሎች ለእሳቱ መባባስ አስተዋጾኦ ማድረጋቸውንም ኃላፊው ለዶቼ ቬለ አክለዋል ።  የደረሰው ውድመት መጠን እና ትክክለኛ የአደጋው መንስኤ በፖሊስ እየተጣራ ነው ብለዋል ። እሳቱ እንዳይስፋፋና ወደ መኖሪያ መንደሮች ብሎም በአቅራቢያው ወዳሉ ፋብሪካዎች ሳይዛመት ለመቆጣጠር መቻሉንም ጠቁመዋል ። የሻማ ፋብሪካው በጥሬ እቃነት የሚጠቀምባቸው ኬሚካሎች ብሎም ነዳጅ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ጭምር የሚገኝበት ጋራጅ አጠገብ ለአጠገብ መሆናቸው ለእሳቱ መስፋፋት አስተዋጽኦ ማድረጉን የሕዝብ ግንኑነት ኃላፊው አመልክተዋል ። በአደጋው የሰው ሕይወት ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ኃላፊው መጠቆማቸውን የአዲስ አበባ ወኪላችን ሥዩም ጌቱ ዘግቧል ።

ራፋ፥ እሥራኤል 76ኛ የነጻነት ቀኗን ባቀረበችበት ቀን ውጊያ በጋዛ

እሥራኤል 76ኛ የነጻነት ቀኗን በምታከብርበት ቀን ወታደሮቿ ጋዛ ሠርጥ ውስጥ ከሐማስ ታጣቂዎች ጋ በበርካታ ቦታዎች ብርቱ ውጊያ ማድረጋቸው ተዘገበ ። በውጊያውም ፍልስጥኤማውያን በገፍ መፈናቀላቸው ተጠቅሷል ።  ደቡባዊ ጋዛ ውስጥ በርካቶች ተጨናንቀው በሚኖሩባት ራፋሕ ከተማ እንዲሁም በሰሜናዊ እና መአከላዊ ጋዛ ጭምር ዛሬ ውጊያ እንደነበር የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት (AFP) ዘገቧል ። ዩናይትድ ስቴትስ የጋዛን የተኩስ አቁም ስምምነት ደጋግማ በማሳሰብ አጋርዋ እስራኤል ጦርነቱን በተመለከተ፦ «ሥልታዊ ፍጻሜ» እንድታዘጋጅ እና ከጦርነት በኋላ ዕቅድም እንድትነድፍ ጠይቃለች ሲሉ የኋይት ሐውስ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጃክ ሱሊቫን ተናግረዋል ።

« እስራኤልን እያነጋገርን ነው የሐማስን ዘላቂ ሽንፈት በሚያረጋግጥ ብሎም ለጋዛ እና ለፍልስጤም ሕዝቦች የተሻለ የወደፊት አማራጭ ሁኔታን በሚያመጣ መልኩ ወታደራዊ ዘመቻዎቻቸውን ወደ ሁሉን አቀፍ  የተቀናጀ ስትራቴጂ እንዴት እንደሚያገናኙ እየተናጋገርን ነው »

እስራኤል፦ ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአዉሮጳ ኅብረት፣ ብሪታንያና ተከታዮቻቸዉ በአሸባሪነት የፈረጁት የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሐማስ ጥቃት ከሰነዘረባት በኋላ የበቀል ጥቃቶችን ስትሰነዝር ከሰባት ወራት በላይ ሆኗል ። ባለፉት 24 ሰአታት ብቻ ቢያንስ 82 ሰዎች መገደላቸውን በሐማስ የሚመራውና ጋዛ የሚገኘው ጤና ሚንስትር ዐስታውቋል ። ከሰሞኑ በነበሩ ውጊያዎች ብቻ 450,000 ፍልስጥኤማውያን ከራፋሕ ተፈናቅለዋል ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዐስታውቋል ። 100, 000 ግድም ደግሞ ከሰሜን ጋዛ መፈናቀላቸውን በመጥቀስ በግዛቲቱ፦ «አንዳችም ቦታ አስተማማኝ አይደለም» ብሏል ።

ኪዬቭ፥ የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዩክሬንን ድንገት ጎበኙ

ድንገት ሳይጠበቁ የዩክሬን መዲና ኪዬቭ ዛሬ የተገኙት የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ሀገራቸው ለዩክሬን ተጨማሪ ወታደራዊ ድጋፍ እንደምታደርግ ቃል ገቡ ። የውጭ ጉዳዩ ሚንስትሩ ጉብኝት እና ድጋፍ የተሰማው ሩስያ ጥቃቷን ዩክሬን ላይ ባጠናከረችበት ወቅት ነው ። አንቶኒ ብሊንከን ኪዬቭ ዛሬ የገቡት ከፖላንድ ሌሊቱን በባቡር ተጉዘው መሆኑም ተዘግቧል ። ሩስያ በሰሜን ምሥራቅ ድንበር በኩል በወሰደችው ፈጣን የማጥቃት ርምጃ ከዩክሬን ግዛት ከ100 እስከ 125 ስኩዌር ኪሎ ሜትሮችን መቆጣጠሯ ተገልጧል ። ሩስያ የተቆጣጠረችው አካባቢ ቢያንስ ሰባት መንደሮች የሚገኙበት ነው ተብሏል ።  ከመንደሮቹ ነዋሪዎች ቀድሞውኑም የተሰደዱ ቢሆንም በሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ጦርነቱን ፍራቻ ከመኖሪያቸው ሸሽተዋል ። የሩስያ የአሁኑ ፈጣን ጥቃት ከሁለት ዓመatት ወዲህ እጅግ ብርቱው ነው ተብሏል ። የዩክሬን ፕሬዚደንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ፦ ሰላማዊ ዜጎችን ከሩስያ ጥቃት ለመታደግ ተጨማሪ የመከላከያ መሣሪያዎች ያስፈልጉኛል ሲሉ ዩናይትድ ስቴትስን ጠይቀዋል። ከሩስያ ወረራ በኋላ ዩክሬንን ለአራተና ጊዜ የጎበኙት ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን በበኩላቸው የዩናይትድ ስቴትስ ድጋፍ « መንገድ ላይ ነው» ማለታቸው ተሰምቷል ።

ሙምባይ፥ ግዙፍ የማስታወቂያ ሠሌዳ ተደርምሶ ቢያንስ 14 ሰዎች ገደለ

የህንድ የፋይናንስ መዲና የሆነችው ሙምባይ ውስጥ ግዙፍ የማስታወቂያ ሠሌዳ ተደርምሶ ቢያንስ 14 ሰዎች ሞቱ ። ከኦሎምፒክ መዋኛ ገንዳን ያህል ግዝፈት ያለው የማስታወቂያ ሠሌዳ ትናንት በመብረቅ ምት ተደርምሶ የወደቀው የነዳጅ ማደያ አጠገብ ነው ተብሏል ። በፍራሹ ውስጥ መውጣት ያልቻሉ ከ100 በላይ ሰዎችን ሕይወት የማዳን ሥራ ትናንት ሌሊት ጀምሮ መቀጠሉን የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናግረዋል ። የሕይወት አድን ሠራተኞች፦ ተሽከርካሪ ከተጨናነቀባት የሙምባይ ከተማ የጋትኮፓር መንደር ውስጥ በተከሰተው አደጋ የቆሰሉ 75 ሰዎችን ከፍርስራሹ ውስጥ ማውጣታቸውንም ገልጠዋል። 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

Äthiopien Alamata City Gondar
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።