1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመንግሥት መግለጫ፣የቀጠለው የቤቶች ፈረሳ ፣የህንጻዎች መደርመስ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 18 2016

«የሽግግር ፍትህ ብቸኛ መፍትሄ አይሆንም ሌሎች አማራጮች ይፈተሹ መፈናቀል ለወረኞች በር ይከፍታል የተባለው ለመፈናቀል ምክንያት የሆኑ ችግሮች በጊዜ መፍትሄ ስላልተሰጣቸው ነው መንግስት ሀገር መምራት ከጀመረባት ቀን አንስቶ የተፈጠሩ አለመግባባቶች በጊዜው በሽግግር ፍትህ መታከም ነበረባቸው አሁን ከመጨረሻ መጀመሩ ይከብዳል።»

https://p.dw.com/p/4fDOe
የኢትዮጵያ የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት
የኢትዮጵያ የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ምስል Office of the PM of Ethiopia

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት


የብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት በወቅታዊ ሀገራዊ የደህንነትና ፀጥታ ጉዳዮች ከትናንት በስተያ ባወጣው የታጠቁ ኃይሎች ትጥቅ ፈተው የተሐድሶ ሂደትን መቀላቀል እንዳለባቸው በማሳሰብ የፖለቲካ ጥያቄዎቻቸውንም በሀገራዊ ምክክር ሂደት በመሳተፍ መፍታት ይችላሉ ብሏል። ለዚህም የተሐድሶ ኮሚሽን መቋቋሙን ያሳወቀው መግለጫው ዓላማውም መሣሪያ ማስፈታት፣ የትጥቅ ቡድኖችን ሰላማዊ ማድረግና ከማኅበረሰቡ ጋር መቀላቀል መሆኑንም ገልጿል።  ግቡ ዘላቂ ሰላም መሆኑን የጠቀሰው ምክር ቤቱ አብረን እንሥራ፣ እንምከር፣ በጋራ ለሀገራችን ጉዳዮች መፍትሔ እንፈልግ ሲልም ዘለግ ባለው መግለጫው ጥሪ አቅርቧል።

በዚህ መግለጫ ላይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከተሰጡ አስተያየቶች የዘሪሁን በዘባህ አንዱ ነው «አማራጭ የሌለው ምርጫ መሆኑን ሁሉም ተገንዝቦ ወደዚህ የተቀደሰ ሀሳብ መምጣት የውዴታ ግዴታ መሆኑን አውቀው የመንግስትን ሀሳብ ይቀበላሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ምክንያቱም መንግስት ነውና።» ይላል ልጅ ባልቻ በሚል የፉስቡክ ስም የሰፈረ አስተያየት ደግሞ በአጭሩ «ጦርነት ሁላችንንም ያከስራል፣ ሰላም ሁላችንንም አትራፊ ያደርጋል!» ሲል ይታረቅ አምባ ደግሞ ትችት አስቀድመዋል «መግለጫ ለምን ይረዝማል አሰልቺ ነው፤ በአጭሩ ይነገር ካሉ በኋላ « መንግስት ከገባበት ማነቆ ለመውጣት የሽግግር ፍትህ ብቸኛ መፍትሄ አይሆንም ሌሎች አማራጮች ይፈተሹ መፈናቀል ለወረኞች በር ይከፍታል የተባለው ለመፈናቀል ምክንያት የሆኑ ችግሮች በጊዜ መፍትሄ ስላልተሰጣቸው ነው መንግስት ሀገር መምራት ከጀመረባት ቀን አንስቶ የተፈጠሩ አለመግባባቶች በጊዜው በሽግግር ፍትህ መታከም ነበረባቸው አሁን ከመጨረሻ መጀመሩ ይከብዳል። ቀድሞ ነበር መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ በማለት ሀሳባቸውን አጠቃለዋል።


የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት መግለጫበልእስቲ ሰውዓለም « ሁሉንም ችግር በኃይል እንፈታለን ብላችሁ፣ሁሉንም አማራጭ ሞክራችኋል፣ግን አልቻላችሁም፣አሁንም ቢሆን ፣በሁሉም ክልል ነፍጥ አንግበው የፖለቲካ ጥያቄ ከያዙ ኃይሎች ጋር ሀቀኛ የፖለቲካ ድርድር በማድረግ ሀገሪቱን ከገባችበት አዘቀት መውጣት ይኖርባታል።»በማለት «ትክክለኛው የመውጫ መንገድ ሁሉን አቀፍ ንግግር (ድርድር )ብቻ እና ብቻ ነው።» ሲሉ የበኩላቸውን ሀሳብ አቅርበዋል። ብሥራት መሰለም  ፣ «መንግስት ተከብሮ ለመከበር መጀመሪያ ሁሉን ብሔር በተለይ ሀይማኖት እኩል ይመልከት!!! የበላይ ነኝ ከማለት ወደ ህዝቡ ቀርቦ ምንድነው ችግሩ ብሎ ይጠይቅ !!!ሲቀጥል በተለይ በአማራ ክልል የሚደረገውን ውጊያ አቁሞ ከታጣቂዎቹ ጋር ለመነጋገር ይሞክር ሀገሩን ሚጠላ የለም !!!» በማለት ለመንግሥት መፍትሄ ያሉትን ሀሳብ  አቅርበዋል።
። አብዛኛው የዚህ አገር የፖለቲካ ችግር ከመብት እና ነፃነት ጋር የተገናኘ አይደለም» በማለት ሀሳባቸውን የጀመሩት ዘነበ ቶሎሳ « የአገሪቱ መሠረታዊ ችግር ድህነትና ሥራ አጥነት ነው።በተለይ የህዝብ ቁጥር በጣም ማደጉና በአንጻሩ ኢኮኖሚው አለማደጉ ከፍተኛ ችግር ነው ። ፖለቲከኛውም ታጣቂውም ተቃዋሚውም ሄዶ ሄዶ የመሬት የዳቦ የልማት... ጉዳይ ነው የሚያነሳው ። ተደራጅቶና ታጥቆ ጫካ መግባት እንደ ሥራ እድል እየታየ ነው።ሰለዚህ ከሌሎች መፍትሄዎች ጎን ለጎን ወገብን ጠበቅ አደርጎ ኢኮኖሚው ላይ መስራት እጅግ አስፈላጊ ነው ሲሉ አሳስበዋል። 

ፍሬሕይወት ሙላቱ  « ለመነጋገር ቁርጠኝነትና ፍላጎት ካለ ደግሞ በአጭር ጊዜ እንኳን ባይሆን ሊሳካ ይችላል ባይ ነኝ ፡፡ ተጠያይቆ ተማምኖ እና ተስማምቶ ትላንትን ለትላንት ትቶ ዛሬን ለነገ ማሻገር ሲቻል ብቻ ነዉ። ይህንን እንድናደርግ ፈጣሪ አይነ ልቦናችንን ያብራልን እላለሁ ።ሰላም ወዳዶች ተስፋችሁ በሀገራችሁ ላይ ብቻ የሆነ ሰዎች ሁላችሁም በየሐይማኖታችሁ ፀልዮ፡፡ በማለት መክረዋል።

በፒያሳ የቤቶች ፈረሳ
በፒያሳ የቤቶች ፈረሳ ምስል Solomon Muchie/DW

በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች «ለልማት» በሚል ቤቶች መፍረሳቸው ነዋሪዎችም መነሳታቸው ቀጥሏል። በተለይ ከፒያሳ አንስቶ እስከ የካ ሾላ አካባቢ ድረስ በሚዘልቀው «የኮሪደር ልማት» በተሰኘው ፕሮጀክት ቤቶቹን የማፍረሱ ስራ መቀጠሉን ነዋሪዎች ለዶቼቬለ ተናግረዋል። ነዋሪዎች እንዳሉት በቀበሌ ቤት የሚኖሩ ፣ቤቶች እየተሰጣቸው ቤቶቹ እየፈረሱ ሲሆን  የግል ቤቶች ግምትና ልዋጭ መሬት ለማዘጋጀት በሚል እስካሁን እንዳልፈረሱ ተናግረዋል። የእነዚህ ነባር ሰፈሮች መፍረስ የነዋሪዎቹን ሕይወት ማኅበራዊ ግንኙነትና መስተጋብር እንደጎዳው የሚናገሩ አሉ በሌላ በኩል ወደፊት ለሁሉም ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል የሚገምቱም አልጠፉም ። በዚህ ጉዳይ ላይ በዶቼቬለ የፌስቡክ ገጽ ላይ ከተሰጡ አስተያየቶች አንዱ የፍሬ ሕይወት አያሌው ማሳሰቢያ ነው። በአዲስ አበባ ፒያሳ አከባቢ በቤቶች ፈረሳ መውደቂያ አጣን ያሉ ነዋሪዎች
«ችኮላው ለእግረኛ መንገድ ብቻ መስፋት ከሆነ ይሔን ሁሉ ውጪና ጥድፊያ ቆም ብሎ ማሰብ ይፈልጋል የሚያመጣው የኢኮኖሚ ገቢም አይታየኝም ቅድሚያ የሚሰጣቸው ብዙ ጉዳዮች አሉን የሥራ እድልም ከተባለ ለአጭር ጊዜ መሆኑ ይታወቃል ሕዝቡም ለግማሹ ጥሩ ቢሆንም በአብዛኛው የገቢ ምንጫቸው የተዘጋባቸው አዝነዋል ፈጣሪ ይርዳቸው ነው የሚባለው» ይላል።
ሻሎም ብርሀን ደግሞ «ወንጀል የሚሆነው ፈርሶ ባይሰራ ነው። ፈርሶ ጥሩ ተደርጎ ከተሰራ ምን ችግር አለው። ሁሉንም አጣጥለን እና ተጠራጥረን እንዴት ይሆናል? በማለት ድርጊቱን የማይቀበሉትን ወቅሰዋል። 

«ከሁሉ ሰው ይቀድማል» ያሉት ወንድሙ ዘኢትዮጵያ «የዜጎችን የመኖርና ያለመኖር መብት ያላከበረ ሰረአተ-መንግስት ህንፃ ብቻ እየገነባ ፣ምን እንደሚያደረገው እግዜር ይወቅ አሁን በዚህ ጊዜ መቅደም ያለበት ህንፃና መንገድ ነው ? ሲሉ በመጠየቅ ሀሳባቸውን ደምድመዋል። ሸምስ መሀመድ ድርጊቱን ከሚተቹት መካከል ናቸው «ከወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ጠቀሜታው አይታየኝም ለምሳሌ እስካሁን የተሰሩ ፓርኮች ቀርተው የእነሱ ወጭ ተፈናቃዮችን ወደየ ቀያቸው መልሱ ማቋቋም ቢቻል ኑሮ አሁን ያሉበትን ስቃይ መቀነስ በተቻለ ነበር ሲሉ መሆን ነበረበት ያሉትን አካፍለዋል።  
ሰይድ መሀመድ ደግሞ «ለእኔ ልማትን የሚጠላ የለም ግን ለህዝባችን ቅድሚያ መኖሪያ ቤት አዘጋጅተው ቢሆን ጥሩ ነበር !! ህዝብን እያማርሩ ልማት የለም ።ሲሉ «ሮም በአንድ ጀንበር አልተገነባችም። ልማት ማንም አይጠላም »ያሉት አህመድ አለማየሁም « ያለቅድመ ማስጠንቀቂያ ሰው ለኪራይ የሚከፍለው አቃ የሚጓግዝበት ሳይኖረው በላዩ ለይ ማፍረስ ግን ግፍ ነው።»ብለዋል።
ደሳለኝ አለማው በተቃራኒው «ማንም ግለሰብም እኮ ቤቱን የሚያድሰው አፍርሶ ነው። ታዲያ ከተማ አስተዳደሩ አፍርሶ መገንባቱ ምኑ ላይ ነው ችግሩ?አዲስ አበባ መንገድ ዳር የነበሩ የንግድ ተቋማት በኮሪደር ልማት ሲነሱ ተጋለጠች። ባጭሩ የክልል ከተሞች ቀድመዋታል። የተነሽዎች መብት ሳይዘነጋ መታደስ አለባት። ሲሉ የበኩላቸውን ሀሳብ አካፍለዋል።  
ማሜ ሁሴንም ሳይፈርስ የሚገነባና የሚለማ ከተማ የሌም ። ያረጁ ቤቶችና ያረጁ አስተሳሰቦች መቀየር አለባቸዉ ብለዋል ።

የቤቶች ፈረሳ በአዲስ አበባ
የቤቶች ፈረሳ በአዲስ አበባ ምስል Solomon Muchie/DW


በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ዋና ከተማ በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ትልልቅ ከተሞች የሚገነቡ ህንጻዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። በሀገሪቱ ለመኖሪያም ሆነ ለተለያዩ ግልጋሎቶች የሚውሉ ህንጻዎች ግንባታ ከምንግዜውም ይልቅ እየጨመረ በመጣበት በዚህ ወቅት ላይ በግንባታ የደኅንነት ችግሮች ሰበብ በሚደርሱ አደጋዎች የሰዎች ሕይወት ያልፋል፤  የንብረት ውድመትም ይደርሳል። ሰሞኑን አዲስ አበባ በግንባታ ላይ የነበረ ህንጻ ተደርምሶ  የሁለት ቤተሰብ አባላት የሆኑ የሰባት ሰዎች ህይወት ጠፍቷል።
በሰሞኑ አደጋ መነሻነት በፌስቡክ የተለያዩ አስተያየቶች ተሰጥተዋል።የቤቶች ፈረሳና እርምጃዉ ያስከተለዉ ጣጣ
ያሳዝናል!! ሲሉ አስተያየታቸውን የጀመሩት አቡ ሬያነ ሀሰን ስጋታቸውን በመግለጽ ለመንግስት ማሳሰቢያ አቅርበዋል። 
ከ30 እስከ 90 ቀን ባለ ጊዜ ተገንብቶ የሚመረቅ ህንፃ በዝቷል ከዚህም በላይ ጉዳት እንዳያደርስ እኔ ያሰጋኛል ። በዚህ ላይ የብረት፣የአሻዋ፣የሲምንቶ እንዲሁ የግንባታ መሐንዲሶች የጥራት ችግር ባለበት ሁኔታ ችግሩ የሚቀጥል ነው የሚመስለው መንግስት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል ።» ሲሉ አሳስበዋል። 
ይድነቃቸው ሻሎም በበኩላቸው 
«ጥራቱን ያልጠበቀና ከደረጃ በታች የሆነ ነገር የብቃት ማነስ የኮንስትራክሽን ባለሞያው ኮንትራቱን የሚወስደው አካል ፈቃድ ሰጭው መሐንዲስ ጉቦ ሙስና ንዝህላልነት እና የመሳሰሉት» የአደጋዎቹ ምንጮች መሆናቸውን ጠቁመው« በዚህ ሁሉ ውስብስብ ሁኔታ ውስጥ ምንም የማያውቁት ምስኪኖች አለፉ ነፍሳቸውን ይማር ብለዋል።
የባለሙያ ተብየዎች የሙያ እጥረት ይመስላል ያሉት ደግሞ ፣እኔ ነኝ ናቸው በፌስቡክ ብዙ አሽዋ ላይ ትንሽ ሲሚንቶ በተን እያረጉ እየሰሩ እንዴት አይደረመስ በዛ ላይ ብረቱ ጥራት የለውም ብለዋል። 
በኮንስትራክሽን ተመርቄ በዘርፉ በኣንድ የመንግስት መስርያ ቤት ተቀጥሬ እየሰራሁ ነው የሚሉት ብርሃኑ አብርሃ ችግሩ በጣም አሳሳቢ መሆኑን ጠቁመው መንስኤ ካሏቸው መካከል   የህንፃ ኣዋጅ ፣ ደንብ እና መመሪያን ኣለመከተል ፣ ከህንፃው ድህንነት ይልቅ ሕጋዊ ያልሆነ ትርፍን ማስቀደም ፣ብቁ  ባለሞያን አለመቅጠር ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን አስረድተዋል። ታምራት ሳህል ደግሞ «የነቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳ ሠንበለጥ።» ብለዋል።
 

ኂሩት መለሰ 

አዜብ ታደሰ