1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሚያዝያ 28 ቀን 2016 ዓ/ም የስፖርት ዝግጅት

ሰኞ፣ ሚያዝያ 28 2016

ትናንት እሁድ በቼክ በተካሔደ 29ኛው የፕራግ የማራቶን ውድድር በሁለቱም ጾታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸነፉ። ሪያል ማድሪድ የ2023/24 የስፔን ላሊጋ ዋንጫን ለ36ኛ ጊዜ አሸናፊ መሆኑ በይፋ ተረጋግጧል። የአውሮጳ ቻምፒየንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ ሁለተኛ ዙር ጫወታዎች ማክሰኞ እና ረቡዕ ተደርገው ለዋንጫ ፍልሚያ ሃላፊ ቡድኖች ይለያሉ ።

https://p.dw.com/p/4fYbn
Spanien | La Liga EA Sports 2023/24 Fußballspiel zwischen Real Madrid und Cadiz CF
ምስል Diego Radames/Anadolu/picture alliance

የአትሌቲክስ ፤ እግር ኳስ እና ሌሎች ስፖርታዊ መረጃዎች የተካተቱበት የስፖርት ዝግጅት

 

ሪያል ማድሪድ የ2023/24 የስፔን ላሊጋ ዋንጫን ለ36ኛ ጊዜ አሸናፊ መሆኑ በይፋ ተረጋግጧል። እንዳጓጉ  በመገባደድ ላይ የሚገኙት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ እና የአውሮጳ ቻምፒየንስ ሊግ በዕለቱ ዝግጅታችን ይዳሰሳሉ፤ በዓለማቀፍ ደረጃ የተከናወኑ የአትሌቲክስ ውድድሮች ዉጤቶችን ጨምሮ  የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን ለፓሪስ ኦሎምፒክ እያደረገ ያለው ዝግጅት ከብዙ በጥቂቱ እንጠይቃለን።

አትሌቲክስ

ትናንት እሁድ በቼክ  በተካሔደ 29ኛው የፕራግ የማራቶን ውድድር በሁለቱም ጾታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸነፉ። በሴቶች በተካሔደው የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊቷ በዳቱ ሒርጳ  2 ሰዓት ከ23 ደቂቃ ከ41 ሰከንድ በማጠናቀቅ አሸናፊ ሆናለች። ኬንያዊቷ ዶርካስ ጄፕቺርቺር ሁለተኛ ስትወጣ ኢትዮጵያውያኑ ሸዋረጌ አለነ እና ጸግነሽ መኮንን ሦስተኛ እና አራተኛ ሆነው ጨርሰዋል። በሴቶች በተካሔደው ውድድር ከሦስት እስከ ሰባት ያለውን ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁት  በሙሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው።

በተመሳሳይ በዕለቱ ወንዶች በተካሔደው ውድድር ለሚ ብርሀኑ በ2 ሰዓት ከ8 ደቂቃ ከ44 ሰከንድ  አሸናፊ ሆኗል። ኬንያውያኑ ኪፕሮሞ ኪፕኬሞይ እና ጆሹዋ ኪፕኬምቦይ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ወጥተዋል። ለሚ ብርሀኑ ባለፈው ጥር ህንድ ሙምባይ ውስጥ በተካሔደ የማራቶን ውድድር አሸናፊ ነበር። 

	የፓሪስ ኦሎምፒክ አርማ
ፓሪስ በምታሰናዳው የኦሎምፒክ ጫወታዎች ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሄራዊ ቡድን ዝግጅት እያደረገ ነውምስል Alkis Konstantinidis/REUTERS

ከአትሌቲክ ዜና ሳንወጣ በ2024 ፓሪስ በምታሰናዳው የኦሎምፒክ ጫወታዎች ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሄራዊ ቡድን የዝግጅት ሁኔታ ምን ይመስል ይሆን ስንል ከአዲስ አበባ እንጠይቃለን። የአዲስ አበባው ተባባሪ ዘጋቢያችን ምስጋናው ታደሰን በስልክ አነጋግሬዋለሁ።

እግር ኳስ

በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ወደ ተከናወኑ ዐበይት የእግር ኳስ ዜናዎች ስንመጣ የስፔይን ላሊጋ የ2023 / 24 የውድድር ዘመን አሸናፊውን ለይቷል። ኃያሉ ሪያል ማድሪድ አራት ጫወታዎች እየቀሩት ሻምፒዮናነቱን አስቀድሞ አረጋግጧል።  

ማድሪድ ዋንጫውን ከፍ ማድረጉን ያረጋገጠው በርቀት ይከተለው የነበረው የምንግዜም ተቀናቃኙ  ባርሴሎና በዤሮና 4 ለ 2 በሆነ ውጤት መሸነፉን ተከትሎ ነው፡፡ ከባርሴሎና ጫወታ አስቀድሞ ከካዲዝ ጋር የነበረውን ጫወታ በ3 ለ0 አሸናፊነት የደመደመው ሪያል ማድሪድ ከተከታዩ የነበረውን የነጥብ ልዩነት ወደ 13 ማሳደግ ችሏል። ሪያል ማድሪድ የላሊጋውን ዋንጫ ሲያነሳ ለ36ኛ ጊዜ ነው።

ፕሪምየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫውን ለ4ኛ ጊዜ በተከታታይ ለማሸነፍ እና ከረዥም ጊዜ በኋላ ዋንጫውን ለማንሳት ትከሻ ለትከሻ እየተጓዙ የሚገኙት የሊጉ መሪ አርሴናል እና ማንችስተር ሲቲ በሳምንቱ መጨረሻ ተጋጣሚዎቻቸውን በሜዳቸው አሸንፈዋል።

የአርሴናል ቡድን
ለፈው ቅዳሜ አስቀድሞ በተደረገ ጫወታ  በኤሜሬትስ በርንማውዝን ያስተናገደው አርሴናል 3 ለ 0 በማሸነፍ መሪነቱን ማጠናከር ችሏል።ምስል Frank Augstein/AP Photo/picture alliance

ባለፈው ቅዳሜ አስቀድሞ በተደረገ ጫወታ  በኤሜሬትስ በርንማውዝን ያስተናገደው አርሴናል 3 ለ 0 በማሸነፍ መሪነቱን ማጠናከር ችሏል። ተከታዩ ማንችስተር ሲቲም በአልኢትሃድ ዎልቨርሃምፕተን ዎንደረርስን አስተናግዶ 5 ለ1 በሆነ ሰፊ የጎል ልዩነት በማሸነፍ የእርሱን ነጥብ መጣል ሲጠብቁ በነበሩ የአርሴናል ደጋፊዎችን ኩምሽሽ አድርጓል። በሊጉ በዋንጫ ፍክክሩ ውስጥ ብርቱ ተጋድሎ ሲያደርግ የነበረው እና ባለፉት ሁለት ጫወታዎች አምስት ነጥብ ጥሎ የዋንጫ ተስፋውን ያመነመነው ሊቨርፑል ትናንት ቶተንሃም ሆትስፐርን በሜዳው አስተናግዶ 4 ለ2 በሆነ ውጤት በማሸነፍ አሁንም አለሁ ብሏል።

የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግና የአውሮጳ ሊግ ፍልሚያዎች

በሊጉ ለዋንጫ የሚደረገውን ፍልሚያ ያህል ላለመውረድ ፣ የሻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊ ለመሆን እንዲሁም ለሎች የአውሮጳ ዋንጫዎች ተሳትፎ ለማረጋገጥ የሚደረጉ ፍልሚያዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል። ባለፉት ሁለት ጫወታዎች መነቃቃት ያሳየው ቼልሲ ትናንም ዌስትሃም ዩናይትድን 5 ለ0 በሆነ የሰፋ ጎል በማሸነፍ ደረጃውን ወደ 7ኛ ማሳደግ የቻለበት ዉጤት ተጠቃሽ ነው። ኖቲንግሃም ፎረስትም መውረዱን ካረጋገጠው ሼፊልድ ዩናይትድ ጋር ያደረገውን ጫወታ ከሜዳው ውጭ 3 ለ 1 በማሸነፍ እና  3 ጣፋጭ ነጥቦች ሰብስቦ በመመለሱ ከወራጅ ቀጠናው በሶስት ነጥብ መራቅ አስችሎታል።

አርሴና ከማንችስተር ሲቲ ብርቱ ተፎካካሪዎች ሆነው ቀጥለዋል
እንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫውን ለ4ኛ ጊዜ በተከታታይ ለማሸነፍ እና ከረዥም ጊዜ በኋላ ዋንጫውን ለማንሳት ትከሻ ለትከሻ እየተጓዙ የሚገኙት የሊጉ መሪ አርሴናል እና ማንችስተር ሲቲ በሳምንቱ መጨረሻ ተጋጣሚዎቻቸውን በሜዳቸው አሸንፈዋል።ምስል Dave Thompson/AP Photo/picture alliance

አስቀድሞ ሻምፒዮናውን የለየው የጀርመኑ ቡንደስሊጋ በዚህም ሳምንት ቀጥሎ የተከናወነ ሲሆን የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎን ለማረጋገጥ እና ላለመውረድ የሚደረጉ ፉክክሮች አሁንም ተጠናክረው ቀጥለዋል። ሻምፒዮናነቱን አስቀድሞ ያረጋገጠው ባየር ሊቨርኩሰን አሁን እያደረገ ባለው ጫወታ ያለመሸነፍ ክብረ ወሰኑን ማስጠበቅ ሆኗል። ትናንት እሁድ ወደ ፍራንክፈርት አቅንቶ አይንትራ ፍራንክፈርትን የገጠው ሊቨርኩሰን 5 ለ1 በሆነ የሰፋ የጎል ልዩነት አሸንፎ መመለስ ችሏል። ለሊቨርኩሰን ዓመቱ በእርግጥ  እጅግ ድንቅ ነው ማለት ይቻላል። አካሄዱ ለአውሮጳ ሊግ ዋንጫ ቅድመ ግምት እንዲሰጠውም አስችሎታል።

የባየር ሊቨርኩሰን ተጫዋቾች ደስታቸውን ሲገልጹ
ሻምፒዮናነቱን አስቀድሞ ያረጋገጠው ባየር ሊቨርኩሰን አሁን እያደረገ ባለው ጫወታ ያለመሸነፍ ክብረ ወሰኑን ማስጠበቅ ሆኗል።ምስል Ciro De Luca/REUTERS

ወደ ሽቱትጋርት አቅንቶ የነበረው የዓመቱ አቋሙ ሲዋዥቅ የቆየው ባየር ሙንሽን በሽቱትጋርት 3 ለ1 ሽንፈት ቀምሶ ተመልሷል። በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙት ኮሎኝ እና ማየንዝ አንድ አቻ በመለያየታቸው ተያይዘው እዚያው ወራጅ ቀጣና ውስጥ ቀርተዋል። አምና ብርቱ የዋንጫ ተፎካካሪ የነበረው ዶርትሙንድ ወደ ላይፕሲች ተጉዞ ያደረገው ጫወታ የ4ለ1 ብርቱ ሽንፈት አከናንቦታል።  በዘንድሮው የአውሮጳ ሻምፒየንስ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ መድረስ የቻለው ዶርቱሙንድ ለቀጣዩ ዓመት ተሳትፎውን ለማረጋገጥ ብርቱ ፈተና ተደቅኖበታል። በሊጉ ባየርሙንሽን ፣ ሽቱትጋርት እና ላይፕሲች ከ2 እስከ 4 ያለውን ደረጃ ሲይዙ በአንጻሩ  ዳርምሽታት ፣ኮሎኝ እና ማየንዝ በወራጅ ቀጣና ውስጥ ይገኛሉ።

ባየር ሙንሽን በጫወታ ላይ
ወደ ሽቱትጋርት አቅንቶ የነበረው የዓመቱ አቋሙ ሲዋዥቅ የቆየው ባየር ሙንሽን በሽቱትጋርት 3 ለ1 ሽንፈት ቀምሶ ተመልሷል።ምስል FILIP SINGER/EPA

ሻምፒየንስ ሊግ

የአውሮጳ ቻምፒየንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ ሁለተኛ ዙር ጫወታዎች ነገ ማክሰኞ እና ተነገ ወዲያ ረቡዕ ተደርገው ለዋንጫ ፍልሚያ ሃላፊ ቡድኖች ይለያሉ ።ሪያል ማድሪድ ወይንስ ባዬርን ሙይንሽን?

ነገ ረቡዕ  በፈረንሳዩ ፓሪሰን ዤርሜ እና ጀርመኑ ቦሩሽያ ዶርትሙንድ መካከል የሚደረገው ፍልሚያ ፓሪስ ውስጥ ይከናወናል።  በመጀመሪያው ዙር ወደ ጀርመን ተጉዞ ዶርቱምንድን የገጠመው ፒ ኤስ ጂ 1 ለ 0 ተሸንፎ የተመለሰ ሲሆን በነገ ምሽቱ ጫወታ ይህንኑ ውጤት ለመቀልበስ ሜዳ ይገባል።

የዶርትሙንድ ተጫዋቾች ደስታቸውን ሲገልጹ
ገ ረቡዕ  በፈረንሳዩ ፓሪሰን ዤርሜ እና ጀርመኑ ቦሩሽያ ዶርትሙንድ መካከል የሚደረገው ፍልሚያ ፓሪስ ውስጥ ይከናወናል።ምስል Horst Mauelshagen/pepphoto/picture alliance

 

ተነገ ወዲያ ረቡዕ በስፔኑ ሪያል ማድሪስ እና በጀርመኑ ባየር ሙንሽን መካከል የሚደረገው ጫወታም እንዲሁ ተጠባቂ ነው። ባለፈው ሳምንት  ሙኒክ ላይ የተደረገው የመጀመሪያው ዙር ጫወታ 2 አቻ መጠናቀቁ ይታወሳል። ምንም እንኳ ባለሜዳው ሪያል ማድሪድ የበርካታ ጊዜ የዋንጫው አሸናፊ መሆኑ እና ጫወታውን በሜዳው ማድረጉ የተሻለ ግምት እንዲያገኝ ቢያስችለውም ቀላል እንደማይሆን ግን በርካታ ተንታኞች አስተያየታቸውን እየሰጡ ነው። በእርግጥ ማን አሸንፎ ወደ ዌምብሊይ ያቀና ይሆን ? የነገ ማክሰኞ እና የተነገወዲያ ረቡዕ ጫወታዎች ይለያሉ።  

ሪያል ማድሪድ ከባየር ሙንሽን በጫወታ ላይ
ባለፈው ሳምንት  ሙኒክ ላይ የተደረገው የመጀመሪያው ዙር ጫወታ 2 አቻ ተጠናቋልምስል Ulmer/Teamfoto/IMAGO

 

ዜና እረፍት

በባርሴሎና ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን በማራቶን  የወከለው አትሌት ጠና ነገሪ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽ አስታወቀ ። ፌዴሬሽኑ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባጋራው መረጃ የአትሌቱን ህልፈት አርድቷል። አትሌት ጠና ነገሪ ከባርሴሎና ኦሎምፒክ በተጨማሪ በበርካታ ዓለማቀፍ ውድድሮች ኢትዮጵያን በመወከል ተሳትፏል። የቀብር ሰነስረአቱን ዛሬ ከሰዓት በኃል አዲስ አበባ  በሰዓሊተ ምህረት ቅድስት ማርያም ቤተክርስትያን መፈጸሙን ፌዴሬሽኑ ገልጿል።

 

ታምራት ዲንሳ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር