1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢድ አልፈጥር በአል በስልጤ ማኅበረሰብ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 3 2016

የስልጤ ህዝብ መጠሪያውን ያገኘው ከቀደምት የእስላማዊ ሱልጣኔቶች አመሰራረት ሲወርድ በመጣው ሂደት እንደሆነ ይነገርለታል። በተለይ ደግሞ ሀጂ አሊዬ ለልጃቸው ሌላ ሱልጣን (ሱልጣኔት) (ገዢ) የሚል ስም መስጠታቸውን ተከትሎ ስልጤ ለመጠሪያነት መዋሉን የስልጤ ዞን የባህል ጽ/ቤት ከድርሳናት ያገኘውን መረጃ አጋርቶናል።

https://p.dw.com/p/4eea8
Äthiopien Werabe | Eid Al-Fitr Feier in Silte
ምስል Silte zone culture office

የኢድ አልፈጥር በዓል ኃያማኖታዊ እና ባህላዊ አከባበር በስልጤ

ኢድ አልፈጥር በአል በስልጤ ማኅበረሰብ

ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለ1445ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ እንላለን አድማጮች ፤ የዕለቱ የባህል መድረክ ዝግጅታችን ወደ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ይወስደናል፤ ወደ ስልጤ ዞን። በኢድ አልፈጥር እና የሸዋል ዒድ የስልጤዎች ሃያማኖታዊ እና ባህላዊ ስርዓት ከብዙ በጥቂቱ ልንዳስስ ወደድን ፤

ዒድን በስልጤ

የስልጤ ህዝብ መጠሪያውን ያገኘው ከቀደምት የእስላማዊ ሱልጣኔቶች አመሰራረት ሲወርድ በመጣው ሂደት እንደሆነ ይነገርለታል። በተለይ ደግሞ ሀጂ አሊዬ ለልጃቸው ሌላ ሱልጣን (ሱልጣኔት)  (ገዢ) የሚል ስም መስጠታቸውን ተከትሎ ስልጤ ለመጠሪያነት መዋሉን የስልጤ ዞን የባህል ጽ/ቤት ከድርሳናት ያገኘውን መረጃ አጋርቶናል። የስልጤ ዞን መዲና ዋራቤ ትሰኛለች። ከአዲስ አበባ በስተደቡብ ሲጓዙ በቡታጅራ እና ሆሳዕና ከተሞች መካከል ረባዳ ስፍራ ላይ ትገኛለች። ገና በማደግ ላይ ያለች ከተማ ነች።

የስልጤ ህዝብ በርካታ ሃይማኖታዊ፤ ባህላዊ እና ታሪካዊ ቅርሶች ያሉት እንደመሆኑ ወቅቱ የዒድ ሰሞን ነውና ስልጤዎች ዒድ አልፈጥርን እንዴት ይሆን የሚያከብሩት ስንል እንጠይቃለን ።

የሸዋል ኢድ በዓል በዩኔስኮ መመዝገቡ ሀረሪዎችን አስደስቷል

የዒድ አልፈጥር በዓል ከመድረሱ በፊት ለስልጤዎች በዓልን በዓል የሚያደርግላቸው የአብሮነት እና ለሌለው የማካፈል ሃይማኖታዊም ባህላዊም ትውፊታቸው ነው ። በዓሉ አንድ እና ሁለት ቀናት ሲቀረው የተቸገሩ ይጎበኙበታል። 

የኢድ አከባበር አንድምታ በሀገር ሽማግሌ ሲገለጽ 

ሼህ አብዱራህማን ሼ ሃጆ በስልጤ ዞን ዳሎቻ ወረዳ ነዋሪ ናቸው ፤ የሃይማኖት አባት እና የሀገር ሽማግሌም ናቸው ። 

«መጀመሪያ የምንጀምረው ፊጢር በመባል የሚታወቅ በነፍስ ወከፍ ለያንዳንዱ ሰው በሚሰጥ እህል ነው። በጣም ትልቅ ነው ፤ ረመዳን ከተያዘ በኋላ አንድ ሰው በነፍስ ወከፍ ዛሬ በተወለደም ልጅ ኢድ ፊጢር ይወጣል፤ ሁለት ኪሎ ተኩል እህል ተሰብስቦ ለደሃዎች እኛም ስንበላ እብረው እንዲበሉ ፤ ልጆቻቸው ልብስ እንዲገዙ ይሰጣል።»

በስልጤ የኢድ አልፈጥር በዓል ባህላዊ እና ኃይማኖታዊ አከባበር
በስልጤ ከኢድ አልፈጥር ቀጥሎ ያሉ ሰባት ቀናት ከተጾሙ በኋላ የሚከበረው የሸዋል ዒድ ትልቅ ትርጉም አለው። በዋናው ኢድ የሚከናወኑ እንዲሁም በትንሹ ዒድ የሚደረጉ ተግባራት ተለይተው ይታወቃሉ ።ምስል Silte zone culture office

የኢድ አልፈጥር ዕለት ሃይማኖታዊውን ስርዓት ተከትሎ በስልጤም በተክቢራ እንደሚጀመር ሼህ አብዱራህማን ይናገራሉ። ነገር ግን የበዓሉ ድባብ ጎልቶ እንደመታየቱ የስልጤዎች ባህላዊ ትውፊትም በዚሁ ውስጥ ይቃኛል። ለዚህ ደግሞ ትልቁ ኃላፊነት በሴቶች ላይ መጣሉን ነው የሀገር ሽማግሌው የነገሩን። እነርሱ የሚያደርጉት ዝግጅት የበዓሉን ድባብ ይወስናልና።

ዒድ አልፈጥር በዓል አከባበር በአዲስ አበባ

የኢድ በዓል እና የሴቶች ሚና 

« ስልጤን ልዩ የሚያደርገው በረመዳን ወር በፍጡር ሰዓት ከደሃዎቹ አብሮ ነው የሚበላው ስልጤ ደሃ ካለበት ለጎረቤትም ይወስዳል፤ በኢድ ቀን ደግሞ በጥዋቱ ሰው ይዘያየራል፤ አብሮ ነው የሚበላው ፤ የተዘጋጀውን ምግብ ለብቻው አይበላም።  እናቶችም ለበዓሉ በጣም ዝግጅት ያደርጋሉ፤ በስልጤ የጾም ፍቺ ሴቶች አይቤ ያዘጋጃሉ፤ የጎመን ክትፎ በቅቤ ይሠራሉ፤  ስሙ ጉጋ ይባላል፤ ጠዋት ለመብላት ያዘጋጃሉ። »

በእርግጥ ነው ስለባህላዊ ምግብ ሲነሳ ስለ ዝግጅቱ አብሮ ማንሳቱ የግድ ነው። ለዚህ ደግሞ በሀገራችን የሴቶች ሚና ትልቁን ስፍራ ይይዛል። ሴቶች ምግብ ለማዘጋጀት ለበዓል በማለት ብቻ ቅቤን ጨምሮ ለአንዳንድ ወጭዎች ዕቁብ እስከመግባትም ይደርሳሉ። ወ/ሮ ሙናጃ ዑመር የወራቤ ከተማ ነዋሪ ናቸው የዒድ በዓላት ሲመጡ በሴቶች ላይ ጫና ይዘው እንደሚመጡ ይናገራሉ።

ዒድ አልፈጥር አከባበር በመቐለ

ወ/ሮ ሙናጃ እንዳሉት ገና ስማቸው ሲጠራ ጣዕማቸው ወደ አዕምሮ የሚመጣ ምግቦችን ለማዘጋጀት ምን ያህል አድካሚ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም። እነዚህን ሁሉ ምግቦች ለማዘጋጀት በዓል ከመድረሱ ሁለት ሳምንት አስቀድሞ በሚደረጉ ዝግጅቶች መጀመርም የግድ ይላል ።

ስልጤዎች በበዓላትም ሆነ በዘወትር ቀናት በማዘጋጀት የሚታወቁባቸው በርካታ ባህላዊ ምግቦች አሉ። ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል አተካኖ ፣ ሱልሶ ፣ ሎሎሃድ፣ የበሰር ኪልፋን፣ ፊንታፊንቶ/ጨራጨረ ፣ ጎሳ ጎሰ ፣ የቆሊ /ያቆቀሲ በሰር..፣ የጄሪ አንገብሶ..፣ ዪንጫቆ በሰር የዶሮ ስጋ ፣ የቁኜ ዪንጫቆ በሰር ። ከስልጤ የባህል ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ከሰላሳ በላይ የምግብ አይነቶች እንዳሉ ነው።

የስልጤ ወንዶች በባህላዊ አልባሳት
የዒድ ዕለት ዚያራ ወይም ቤተዘመድ ጥየቃ ሲኬድ እንዲሁ በባዶ እጅ አይኬድም። አምሪያ እንደምትለው ሁሉም የየአቅሙን ይዞ ይሄዳል፤ ከተዘያሪውም አጸፋ ይኖራል።ምስል Silte zone culture office

ስልጤዎች በሚታወቁበት የንግድ ሥራ በበርካታ የሀገሪቱ ከተሞች ተበታትነው ይኖራሉ። ለዒድ ወደ ሀገር ቤት ከመግባት የሚያግዳቸው ነገር ማጣት እና ህመም ብቻ ነውም ይባልላቸዋል። በተለይ በሸዋል ዒድ እና አረፋ፤ ወላጆች ልጆቻቸውን ያገኙበታል ፤ ለዚህም ነው ሃይማኖታዊ ክብረ በዓሉ ፤ ባህሉን ጨምሮ የመጠያየቅ እና የመገናኘት በዓል የሚሆንላቸው ፤ ለስልጤዎች ።

የኢድ በዓል እና ወጣቶች በስልጤ

አምሪያ ነብዪ የወራቤ ከተማ ነዋሪ ወጣት ናት። በበዓል ዝግጅት ወቅትም ሆነ ከቤተሰቦቻቸው ርቀው የነበሩ ወጣቶች ለጥየቃ ቤተሰቦቻቸውጋ እንደሚመጡ ትናገራለች። ዕለቱንም በሃይማኖታዊ ስርዓት ካሳለፉ በኋላ ባህላዊው ይከተላል።

የዒድ አከባበር በድሬ ደዋ ከተማ

የዒድ ዕለት ዚያራ ወይም ቤተዘመድ ጥየቃ ሲኬድ እንዲሁ በባዶ እጅ አይኬድም። አምሪያ እንደምትለው ሁሉም የየአቅሙን ይዞ ይሄዳል፤ ከተዘያሪውም አጸፋ ይኖራል።

በስልጤ ከኢድ አልፈጥር ቀጥሎ ያሉ ሰባት ቀናት ከተጾሙ በኋላ የሚከበረው የሸዋል ዒድ ትልቅ ትርጉም አለው። በዋናው ኢድ የሚከናወኑ እንዲሁም በትንሹ ዒድ የሚደረጉ ተግባራት ተለይተው ይታወቃሉ ።

በትምህርት አልያም በሥራ ከዘመድ አዝማድ ርቀው የሚኖሩ ወጣት ስልጤዎች በዓልን ጠብቀው ወደቤተዘመድ መመለሳቸው ሳይታለም የተፈታ ነው። እርግጥ ነው ወደ ቤተዘመድ መምጫው በአረፋ ቢሆንም የኢድ አልፈጥር እና ሸዋል በዓላትም በርከት ያሉ ስልጤዎች ወደ ትውልድ መንደራቸው ይመጣሉ።

የስልጤዎች ኃይማኖታዊ ቆብ
ለስልጤዎች ሁሉም በዓል እንደአመጣጡ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ስርአቱን ጠብቆ በአግባቡ ይከበራል።ምስል Silte zone culture office

ኢድ አልፈጥር በሀዋሳ

ለስልጤዎች ሁሉም በዓል እንደአመጣጡ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ስርአቱን ጠብቆ በአግባቡ ይከበራል። ትናንት ረቡዕ በድምቀት ከተከበረው የኢድ አልፈጥር በዓል በተጨማሪ ሳምንት ሸዋል በድምቀት ሊከበር ዝግጅት እየተደረገበት ነው።

ከእነዚህ በዓላት በተጨማሪም በስልጤዎች  ዘንድ የሚታወቁ እና ከፍተኛ ዝግጅት ተደርጎባቸው የሚከበሩ በዓላት በርካቶች ናቸው። አንዳች አረፋ(የሴቶች አረፋ)፣ አረፋ፣ ቀሊ ፍቼ(ትንሹ ኢድ)፣ መዉሊድ እና የስልጤ ዘመን መለወጫ (መሰሮ) ተጠቃሾች ናቸው።

በመጨረሻም በዓል የተድላ እና የደስታ ስሜት እንደመያዙ ሀገሪቱ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ መዘንጋት እንደማይገባ ስልጤዎች ያምናሉ ። 

ዩኔስኮ ለመዘገባቸዉ የኢትዮጵያ ቅርሶች ጥበቃ ያደርጋል?

 ከብዙ በጥቂቱ በስልጤ የዒድ አልፈጥር በዓል አከባበር ላይ ያተኮረው የዕለቱ የባህል መድረክ ዝግጅታችንም የእስካሁንን ይመስል ነበር። ለቃለ ምልልሱ  እንዲሁም መረጃዎችን በመስጠት የተባበሩንን ለስልጤ ዞን ባህል ጽ/ቤት ኃላፊ ምስጋናችንን እያቀረብን በዚሁ እንሰነባበት ።

ታምራት ዲንሳ

ሸዋዬ ለገሠ