1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ በመጪዎቹ ወራት የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ እንደሚደረግ ትጠብቃለች

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ መጋቢት 20 2015

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ አበዳሪዎች በመጪዎቹ ወራት የአከፋፈል ሽግሽግ ያደርጋሉ የሚል ተስፋ ሰንቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተስፋቸውን የገለጹት የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች ወደ አዲስ አበባ ባቀኑበት ወቅት ነው። ዐቢይ እንዳሉት ባለፈው ዓመት ብቻ የኢትዮጵያ መንግሥት 1.7 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ከፍሏል።

https://p.dw.com/p/4PSFC
Äthiopien | Premierminister Abiy Ahmed Ali
ምስል Office of the Prime Minister Ethiopia/UPI Photo/Newscom/picture alliance

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ ኢትዮጵያ በመጪዎቹ ወራት የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ እንደሚደረግ ትጠብቃለች

የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ዕዳ፣ የዋጋ ንረት፣ የመሠረተ-ልማት ክፍተት እንዲሁም በፍላጎት እና አቅርቦት መካከል ያለው አለመጣጣም ኹነኛ ፈተናዎች እንደሆኑበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ትላንት ማክሰኞ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የኢትዮጵያ ዕዳ ከአገሪቱ አጠቃላይ የምርት መጠን (GDP) 52 በመቶ ድርሻ አለው።

በተለይ የኢትዮጵያን የመክፈል አቅም የሚፈታተነው የውጭ ዕዳ ባለፉት አምስት ዓመታት ከ30.6 በመቶ ወደ 24.4 በመቶ ዝቅ ማለቱን ተናግረዋል። ዐቢይ እንዳሉት ባለፈው ዓመት ብቻ የኢትዮጵያ መንግሥት 1.7 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ከፍሏል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት ቢቆጠቡም "በሚቀጥሉት ስድስት ሰባት ወራት ተስፋ የምናደርጋቸው መሸጋሸጎች አሉ። በዚያ እየቀነስን እንደምንሔድ ተስፋ ይደረጋል" ሲሉ ተደምጠዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ እንዲደረግለት በቡድን 20 አገራት የጋራ ማዕቀፍ በኩል ጥያቄ ያቀረበው በሐምሌ 2013 ቢሆንም እስካሁን ድርድሩ ፈቅ አላለም።  ዐቢይ እና የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴን ጨምሮ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ለኢትዮጵያ የተቋቋመውን የአበዳሪዎች ኮሚቴ በተባባሪ ሊቀ-መንበርነት ወደ ሚመሩት ፈረንሳይ እና ቻይና ባለፉት ወራት በተከታታይ ባደረጓቸው ጉብኝቶች የመነጋገሪያ አጀንዳ ከነበሩ መካከል ይኸው የአከፋፈል ሽግሽግ ጉዳይ ይገኝበታል።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዓርማ
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች ለኢትዮጵያ በሚበጅ አዲስ መርሐ ግብር ላይ ለመነጋገር ወደ አዲስ አበባ አቅንተዋል። ድርጅቱ የሚያበጀው የብድር መርሐ ግብር ለኢትዮጵያ የዕዳ ሽግሽግ አስፈላጊ ነው። ምስል Yuri Gripas/REUTERS

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመጪዎቹ ወራት በኢትዮጵያ የዕዳ አከፋፈል ላይ ሽግሽግ ሊደረግ እንደሚችል ጥቆማ የሰጡት የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች ወደ አዲስ አበባ ባቀኑ በቀናት ልዩነት ነው። የድርጅቱ የኮምዩንኬሽን ዳይሬክተር ጁሊ ኮዛክ ባለፈው ሣምንት ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ "ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ግጭትን ለማቆም በተፈረመው ሥምምነት መሠረት ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋትን ለመመለስ የሚደረገውን ጠንካራ እርምጃ በበጎ ይመለከተዋል። የሰብዓዊ እርዳታ እና የተቋረጡ አገልግሎቶች ወደነበሩበት መመለስን ጨምሮ የሥምምነቱ አተገባበር በጥሩ ሁኔታ እየቀጠለ ነው" ብለው ነበር።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በኢትዮጵያ ምጣኔ-ሐብታዊ "ማሻሻያ እቅዶች እና ሰብዓዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚያደርጉትን ጥረት እንዴት መደገፍ እንደምንችል ከባለስልጣናት ጋር ቀጣይነት ያለው ውይይት እያደረጉ ነው" ያሉት ጁሊ ኮዛክ "የገንዘብ ድጋፍ ጥያቄ የቀረበልን ሲሆን ለኢትዮጵያ ሊሰጥ ለሚችል ፕሮግራም ላይ ለመወያየት የቴክኒክ ስራ እያከናወንን ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለኢትዮጵያ የሚያበጀው አዲስ መርሐ-ግብር የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ከአገሪቱ አበዳሪዎች ጋር ለጀመረው የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ አስፈላጊ ነው። ለአስር ቀናት ወደ አዲስ አበባ ያቀኑት የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች ኢትዮጵያ የገጠሟትን ሰብዓዊ እና ኤኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች ለመፍታት በሚያስፈልገው ድጋፍ ላይ እንደሚወያዩ ብሎምበርግ ዘግቧል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጥቅም ላይ የዋለ ታንክ
የትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎችን ያዳረሰው ጦርነት ካስከተለው ብርቱ ሰብዓዊ ቀውስ ባሻገር የኢትዮጵያን ኤኮኖሚ አዳሽቆታል። በጦርነቱ ምክንያት ምዕራባውያን ለኢትዮጵያ የሚሰጡትን ብድር እና እርዳታ ከልክለዋል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ያቀረበው የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ጥያቄንም አዘግይቷል። ምስል Baz Ratner/REUTERS

የኢትዮጵያ መንግሥት የተሟጠጠውን የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለማጠናከር እና በጦርነት የወደመውን መልሶ ለመገንባት ጠቀም ያለ ገንዘብ ያስፈልገዋል። የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የኮምዩንኬሽን ዳይሬክተር ጁሊ ኮዛክ ለስድስት ተከታታይ ወቅቶች ዝናብ ሳይጥል በመቅረቱ የተከሰተው ድርቅ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ ግጭት እንዲሁም የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ላይ ብርቱ ተጽዕኖ እንዳሳደሩ ባለፈው ሣምንት በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል። የምግብ ዋስትና እጦት፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት፣ የዋጋ ንረት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ጨምሮ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች "ብርቱ" መሆናቸውን ጁሊ ኮዛክ አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም መጋቢት 19 ቀን 2015 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ የገጠሙት ተግዳሮቶች ብርቱ መሆናቸውን አልሸሸጉም። በኢትዮጵያ ላለፉት 20 ዓመታት ያለማቋረጥ ሲያድግ የቆየ የዋጋ ንረት በአምራቾች እና ሸማቾች መካከል ባለው የአቅርቦት ሰንሰለት ችግር እንደተባባሰ ዐቢይ ተናግረዋል። ከዓለም ገበያ ወደ ኢትዮጵያ የሚዛመተው የዋጋ ንረት በጦርነት፣ በድርቅ መበርታቱን የገለጹት ዐቢይ አገሪቱ በእርዳታ የምታገኘው ገንዘብ "በእጅጉ" መቀነስም አስተዋጽዖ እንዳበረከተ ጠቅሰዋል። ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰት እና ምርት መደበቅ ሌሎች ዐቢይ የጠቀሷቸው ተጨማሪ ችግሮች ናቸው።

የኢትዮጵያ መንግሥት በ2015 በግብር የሰበሰበው "የተጣራ ታክስ 210 ቢሊዮን ብር ነው ። ይኼ በአሐዝ ደረጃ በ28 በመቶ አድጓል። ነገር ግን ታክስ ከአጠቃላይ አገራዊ የምርት መጠን ጋር ባለው ምጣኔ አሁንም በጣም በጣም ዝቅተኛ ነው" ሲሉ ዐቢይ ተናግረዋል።  "የሰባት ወራት ወጪያችን ግን 376 ቢሊዮን ብር ነው። ከገቢያችን ብዙ ይበልጣል። ከገቢያችን ብቻ ሳይሆን ወጪ ብቻውን 31 በመቶ አድጓል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግሥት ወጪ በሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች መባባሱን አስረድተዋል። "በብድር፣ በእርዳታ ካልተሞላ በስተቀረ በገቢ ካስገባንው ባሻገር ያለ ፍላጎት እንደ መንግሥት ለማሟላት ያስቸግራል። ወጪ እና ገቢያችን ተጨማሪ ስራ የሚጠይቅ እንደሆነ ገቢ ማሳደግ እንዳለብም ያመላክታል" ሲሉ ተደምጠዋል።

ጫት ገበያ በአዎዳይ
የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ በ2015 ስምንት ወራት የነበረው አፈጻጸም ከመንግሥታቸው እቅድ ያነሰ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናግረዋል። ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ወርቅ እና ጫትን የመሰሉ ሸቀጦች በሕገ-ወጥ ንግድ ወደ ውጪ አገራት መላካቸው አንዱ ምክንያት ነው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና ፌድራል ፖሊስ ሕገ-ወጥ ንግዱን እንዲቆጣጠሩ መሰማራታቸውን ዐቢይ ተናግረዋል። ምስል DW/M. Gerth Niculescu

ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ወራት ለዓለም ገበያ ካቀረበቻቸው ሸቀጦች እና አገልግሎቶች ያገኘችው ገቢ ካለፈው ዓመት አኳያ በ25 በመቶ ዕድገት እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ከውጭ ቀጥተኛ መዋዕለ-ንዋይ (FDI) በስምንት ወራት "ከአምናው በጣም ከፍ ያለ" 2.2 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን የጠቀሱት ዐቢይ ከ90 በላይ ፕሮጀክቶች የተግባር ሥራ ውስጥ እንደገቡ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ የገባበት ቅርቃር

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንዳሉት ኢትዮጵያ በተያዘው ዓመት ለዓለም ገበያ ያቀረበችው ምርት ከመንግሥት እቅድ አንጻር "ትንሽ ዝቅ ያለ ነው።" ለዚህም ኢትዮጵያ ወደ ውጪ የላከችው ወርቅ እና ጫት በሕገ-ወጥ ንግድ ምክንያት መቀነሱን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሆኗል ያሉትን በማሳየነት አንስተዋል።

"አሶሳ አምና ወደ ማዕከላዊ ገበያ 20 ኩንታል ወርቅ ያቀረበ ሲሆን ዘንድሮ ግን 3 ኩንታል ወርቅ ነው ያቀረበው። አብዛኛው ወደ ጎረቤት አገር ሔዷል። ወርቅ እያመረትን ወደ ማዕከላዊ ገበያ ከማምጣት ይልቅ በአሻጥር እና ኮንትሮባንድ ወደ ጎረቤት አገራት በስፋት ይሔዳሉ።" ሲሉ ለምክር ቤቱ አባላት አስረድተዋል። "ታንታለም ጉጂ ይመረታል። ኢትዮጵያ ኤክስፖርት ከምታደርገው በላይ ግን የማያመርቱ ጎረቤት አገሮች ኤክስፖርት ያደርጋሉ" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥታቸው ሕገ-ወጥ ንግዱን የመቆጣጠር ኃላፊነት ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና ለፌድራል ፖሊስ እንደሰጠ ጠቁመዋል።

"ይኸንን ኮንትሮባንድ ለመከላከል፤ እያጋጠመ ያለውን ፈተና ለመከላከል አብዛኛው ኃይላችን ሀብት ያለባቸው አካባቢዎች እና ሽፍታ የበዛባቸው አካባቢዎች እንዲሰፍር ተደርጓል። የአገር መከላከያ ሚኒስቴር፤ የፌድራል ፖሊስ ቀዳሚ ተግባር ኮንትሮ ባንድን መዋጋት፤ በኮንትሮባንድ የሚመዘበረውን የኢትዮጵያን ሀብት መከላከል በየአካባቢው ታጥቆ ለዘረፋ የተሰማራን ኃይል ሕግ ማስከበር በሚል ስራ ተስጥቷቸዋል። ቦታ ቦታቸውን እየያዙ ነው። በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ እንጠብቃለን" ብለዋል።

የመንገድ ግንባታ በአዲስ አበባ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "ከ22 ሺሕ ኪሎ ሜትር በላይ አስፓልት ኮንክሪት ኢትዮጵያ ውስጥ ይሰራል። ዛሬ በእጃችን ያሉ ፕሮጀክቶችን ብቻ ለማስጨረስ አንድ ትሪሊዮን ብር ያስፈልገናል" ሲሉ ተናግረዋል። ምስል Imago/Xinhua Afrika

ዐቢይ እንዳሉት ኢትዮጵያ ከዓለም ገበያ ለምትሸምታቸው ሸቀጦች ያወጣችው ገንዘብ በስምንት ወራት ብቻ ከ9 ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል። ከዚህ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ነዳጅ ሲሆን መንግሥት ለድጎማ በስምንቱ ወራት ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ እንዲያወጣ አስገድዶታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ለአፈር ማዳበሪያ ግዢ ድጎማ የወጣው ወጪ 21 ቢሊዮን ብር ደርሷል። ዘይት እና ስኳር የመሳሰሉ በፍራንኮ ቫሉታ ወደ ኢትዮጵያ በገቡ ሸቀጦች መንግሥትን ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ አሳጥተዋል።

በርካታ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በተደጋጋሚ ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል የመንገድ ግንባታ አንዱ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጥያቄዎቹ በሰጡት ምላሽ በ2015 በጀት ዓመት ብቻ ለመንገድ ግንባታ የተጠየቀው የካሳ ክፍያ 20 ቢሊዮን ብር መድረሱን ገልጸው በመንግሥታቸው ወጪ ላይ ያስከተለውን ጫና ጠቆም አድርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ወረዳዎች ገና መንገድ ይሰራል ሲባል ጌሾ እያስተከሉ፤ ተመን እያስፋፉ ልማት እንዳይሰራ እያደረጉ ነው" ሲሉ ነቅፈዋል። የተጀመሩትን 320 የመንገድ ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅ የሚያስፈልገው ገንዘብ ሌላው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቀሱት ፈተና ነው። "ከ22 ሺሕ ኪሎ ሜትር በላይ አስፓልት ኮንክሪት ኢትዮጵያ ውስጥ ይሰራል። ዛሬ በእጃችን ያሉ ፕሮጀክቶችን ብቻ ለማስጨረስ አንድ ትሪሊዮን ብር ያስፈልገናል" ሲሉ ተናግረዋል።  

እሸቴ በቀለ

ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር