1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አንጋፋው የስፖርት ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 1 2015

በኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኝነት ታሪክ ፈር ቀዳጅ ተብለው ከሚጠቀሱት አንዱ የሆነው አንጋፋው ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ፍቅሩ ኪዳኔ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ በተለያዩ ቋንቋዎች በስፖርት ጋዜጠኝነት ፣ በካፍ እና በኦሎምፒክ ኮሚቴ አመራርነት፣ በስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር መስራችነት እና አመራርነትም አገልግሏል።

https://p.dw.com/p/4I2zC
ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ
አንጋፋ የስፖርት ጋዜጠኛ የነበረው ፍቅሩ ኪዳኔምስል Haimanot Tiruneh/DW

አንጋፋው የስፖርት ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ አረፈ

በኢትዮጵያ  የስፖርት ጋዜጠኝነት ታሪክ ፈር ቀዳጅ ተብለው ከሚጠቀሱት አንዱ የሆነው አንጋፋው ጋዜጠኛ ጋሽ ፍቅሩ ኪዳኔ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ጋሽ ፍቅሩ ኪዳኔ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ በተለያዩ ቋንቋዎች በስፖርት ጋዜጠኝነት ከማገልገሉም ባሻገር በካፍ እና በኦሎምፒክ ኮሚቴ አመራርነት፣ በስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር መስራችነት እና አመራርነትም አገልግሏል። አንጋፋው የስፖርት ጋዜጠኛ፣ ፍቅሩ የቀድሞው የዓለም አቀፍ የኦሎምፒክ ኮሚቴና የአፍሪቃ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ባልደረባ  ነበር።  ታዋቂው ጋዜጠኛ ፍቅሩ በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ዛሬ ማለዳ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን ቤተሰቦቹ አስታዉቀዋል። በ1943 በሱዳን እና ኢትዮጵያ መካከል የተደረገውን የእግር ኳስ ጨዋታ በኢትዮጵያ ራድዮ ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጥታ ስርጭት የዘገበው ፍቅሩ  በሀገር ውስጥ ለተለያዩ የሕትመት ውጤቶችም ይሰራ ነበር። ከ1969 አንስቶ ኑሮውን ፓሪስ ፈረንሳይ ያደረገው ፍቅሩ የዶቼቬለ (የጀርመን ድምጽ) በኋላም የአሜሪካ ድምጽ ዘጋቢም ነበር። ፍቅሩ የኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ኮሚቴን በዋና ጸሐፊነት፣ የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ሆኖም አገልግሏል። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የቀድሞ ፕሬዝደንት አማካሪም ነበር። «የፒያሳ ልጅ»ና «የስፖርት ጨዋነት ምንጮች» ፍቅሩ ለአንባብያን ያቀረባቸው ሁለት መጻሕፍቱ ናቸው። የአንድ ልጅ አባትና የሁለት የልጅ ልጆች አያት ነበር። ፍቅሩ ያረፈው በ88 ዓመቱ ነው።

ኃይማኖት ጥሩነህ 

ታምራት ዲንሳ 

ነጋሽ መሐመድ