የደቡብ አፍሪቃ ሃገራት በገዳይ የኮሌራ ወረርሺኝ ተመቱ
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 12 2016የኮሌራ ወረርሺኝ የደቡብ አፍሪቃ ሃገራትን ከዐሥር ዓመት ወዲህ በብርቱ መምታቱ ተዘግቧል ። የዶይቸ ቬለዋ ኬት ሐሪሰን ዘገባ አላት ። በዛሬው የትኩረት በአፍሪቃ መሰናዶዋችን ቀዳሚው አድርገነዋል ። ካለፉት አራት ወራት ወዲህ በደቡባዊ የአፍሪቃ ሃገራት ከ1,000 በላይ ሰዎች በኮሌራ ሕይወታቸውን አጥተዋል ። በዐሥር ሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ በብርቱው ገዳይ የኮሌራ ወረርሽኝ ተጠቅተዋል ። በረረሺኙ እጅግ የተጎዱት ሃገራት፦ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ከበደቡብ አፍሪካቃ ሃገራት ሞዛምቢክ፣ ዚምባብዌ እና ዛምቢያ ናቸው ። ወደ ሰሜን ሲል ደግሞ ኮሌራ በኢትዮጵያም ጉዳት አድርሷል ።
በከፍተኛ ሁኔታ ተላላፊ ከሆነው የኮሌራ በሽታ ባክቴሪያ ጋ ንክኪ ሲፈጠር በሰዓታት ውስጥ ከባድ ተቅማጥ እና የሰውነት ድርቀት ይከተላል ። ባክቴሪያው አግኝቷቸው በፍጥነት ከታከሙ ሰዎች መካከል ለሞት የሚዳረጉት ከአንድ ከመቶ በታች ናቸው። ። ነገር ግን ከዓለም ድሃ ሃገራት መካከል አንዷ በሆነችው ዛምቢያ የሟቾች ቁጥር ከ3 ከመቶ በላይ ነው ። ሰዎች በጎስቋላ መንደሮች ተፋፍገው በድህነት ከሚኖሩባቸው ሃገራት አንዷ በሆነችው ዛምቢያ ከአምስት ወራት በፊት ወቅታዊ ዝናብ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ740 በላይ በኮሌራ ወረርሺኝ የተነሳ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ተመዝግቧል ።
«ኮሌራን በተመለከ እጅግ አሳሳቢው ገጉዳይ በሽታው ሰዎችን በያዘ በሰአታት ውስጥ ሊገድል መቻሉ ነው ። ሰዎች ካልታከሙ እና እንክብካቤ ካላገኙ ከ3 እስከ 4 ቢበዛ 24 ሰአት ውስጥ ሊሞቱ ይችላሉ ። በሁለተኛ ደረጃ፦ የኮሌራ ወረርሺኝ ሥርጭት በከተሞች በተለይ ደካማ የንፅሕና አጠባበቅ እና የውኃ አቅርቦት ባለባቸው አካባቢዎች እጅግ ፈጣን ነው ። »
ኮሌራ እንዴት ነው የሚዛመተው?
ኮሌራ በአብዛኛው የሚስፋፋው በተፈጥሮ አደጋ በተጎዱ አካባቢዎች ነው ። በማአከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ የባንጉዊ የአርብቶ አደሮች ተቋማ ኃላፊ እና የተላላፊ በሽታዎች አጥኚ ያፕ ቦም በተፋፈጉ ጎስቋላ መንደሮች ውስጥ መኖር ለወረርሺኙ መስፋፋት ዋነኛ ሰበብ መሆኑንም አክለዋል ።
«መጸዳጃ ቤቱ ከመጠጥ ውኃ ጉድጓዱ እጅግ ቅርብ የሆነ አንድ መኖሪያ ቤትን እስኪ በምናባችሁ ሳሉ ። በመጸዳጃ ቤቶቹ እና በመጠጥ ውኃ አቅርቦቱ ላይ በቀላሉ የባክቴሪያው ንክኪ ይኖራል ። ያ እንዳውም የተለመደው ነው ። በርካታ ሰዎች ተፋፍገው ወደሚኖሩባቸው የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች አለያም በጎርፍ አደጋ ወደተሰጠኩ አባቢዎች ብትሄዱ የመጠጥ ውኃው በኮሌራ በሽታ አማጩ የቪቢሮ ባክቴሪያ እጅግ የተበከለ ነው ። »
በአፍሪቃ የኮሌራ ወረርሺኝ መስፋፋትን የሚያባብሱት ምንድን ናቸው?
በብዙ የአፍሪቃ ሃገራት የኮሌራ ወረርሺን በፍጥነት እንዲዛመት የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች አሉም ይላሉ የጤና ባለሞያው ።
«ኮሌራ በአብዛኛው ለግጭት፣ ለፀጥታ እጦት እና ለድህነት በተጋለጡ ሃገራት የፍትሐዊነት እጦት ምልክት ነው ። ምክንያቱም ኮሌራ በተመሳሳይ መልኩ ምእራባውያን ሃገራት ላይ ቢከሰት ከፍተኛ ክትባት አላቸው ። ጉዳዩ እዚህ እጅግ ተለየ ነው ።»
የጤና ባለሞያው የዘረዘሯቸው ምክንያቶች በአሁኑ ጊዜ ከኮሌራ ወረርሺኝ ጋ ግብግብ በገጠሙት በእያንዳንዱ የአፍሪቃ ሃገራት ውስጥ ይገኛሉ ።
ሌላኛው ምክንያት ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥ ነው ።
በደቡብ አፍሪቃ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት አንያ ዱ ፕሌሲስ በዶይቸ ቬለ ተጠይቀው፦ «ከአየር ንብረት ለውጥ ጋ በተገናኘ በየጊዜው የሚጨምረው የከፋ የጎርፍ መጥለቅለቅ [በኮሌራ ወረርሽኞች ላይ] ተጽእኖ አለው» ሲሉ ጽፈዋል። ቀጣናው በአሁኑ ወቅት እያጋጠመው ባለው የዝናብ ወቅት የተነሳ ኮሌራ በብዛት ይከሰታልም ሲሉ በጽሑፍ ምላሽ ሰጥተዋል ።
የኮሌራ ክትባትን በተመለከተስ?
ነገሩን የበለጠ የከፋ የሚያደርገው ደግሞ የኮሌራ ወረርሺኝን ለመከላከል የሚያግዙ ክትባቶች መሟጠጣቸው ነው ። ደቡብ ኮሪያ ውስጥ የሚገኝ አንድ የመድኃኒት ፈብራኪ ኩባንያ በአፍ የሚሰጥ የኮሌራ መከላከያ ክትባትን በአሁኑ ወቅት በብቸኝነት ያመርታል ። ኩባንያው በሳምንት 700,000 ብልቃጥ ክትባቶችን ለገበያ ያቀርባል ። የመድኃኒት ፍላጎቱ ግን ከኩባንያው አቅም በላይ አራት እጥፍ መድረሱን ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን መረጃ (MSF)ይጠቁማል ።
በሕጻንነት ወቅት ከሚሰጠው የተለመደ የጸረ ኮሌራ ክትባት በተለየ መልኩ ወረርሺኙ ሲከሰት የሚመረተው በልዩ ትእዛዝ ነው ። የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች መድኃኒቶች በተፈለጉ ቁጥር ወዲያው ያመርታሉ ማለት አይደለም ። በዚያ ላይ የአምራቾቹ ፍላጎት ከአንዱ የሌላኛው የተለያየ ነው ። በደቡብ አፍሪቃ ኬፕ ታውን ዩኒቨርሲቲ ለአፍሪቃ ክትባት ተቋም የክትባት ባለሞያዋ ኤዲና አምፖንሻ የራስን አቅም የማጎልበት ወሳኝነትንያሰምሩበታል ።
«በሽታዎች በሁሉም የዓለም ክፍሎች በተመሳሳይ መልኩ ቅድሚያ አይሰጣቸውም ። የማምረት አቅምህን በተለይ የኮሌራ በሽታ ወረርሺኝ በከፋ ሁኔታ በተከሰተባቸው የዓለማችን ክፍሎች ብታጎለብት፤ ያ ማለት ሃገራት የባለቤትነት ኃላፊነቱን በመውሰድ በራሳቸው አቅም በመመስረት የጤና መርኃ-ግብራቸውን በተሻለ ሁኔታ መደገፍ ይችላሉ ማለት ነው ።»
ለመሆኑ ግን ኮሌራ ወረርሺኝን ለመከላከል ክትባት ብቻ ነው መፍትኄው?
የኮሌራ መከላከያ ክትባት ምርት ባለፉት ዐሥር ዓመታት እጅግ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል ።
እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2013 ዓ.ም ሁለት ሚሊዮን ብልቃጥ የነበረው የክትባት ምርት በ2022 ወደ 36 ሚሊዮን ብልቃጦች ግድም ክምችት ከፍ ብሏል ። እንዲያም ሆኖ ይህ መጠን አሁን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቁጥሩ ከፍ ያለውን የኮሌራ ወረርሺኝለመከታተል በቂ አይደለም ። ኤዲና አምፖንሻ ያክላሉ ።
«የኮሌራ መከላከያ ክትባቶችን የምንጠቀመው ወረርሺኙ ሲከሰት በሽታው እንዳይዛመት ለመጠነ ሰፊ የመከላከል ዘመቻ ነው ። ያ ማለት የምናመርተው ለተወሰኑ ሃገራት የተወሰነ መጠን ነው ።»
ክትባት በሽታን ለመዋጋት ከሚረዱ በርካታ መሣሪያዎች ውስጥ አንዱ ብቻ መሆኑንም ባለሞያዎቹ ይጠቁማሉ ። ይልቁንም ከክትባት ባሻገር ሃገራት እንደ የማኅበረሰብ ጤና ነክ የሆኑ ሌሎች የወረርሺኙ መከላከያዎች ጉዳዮች ላይ ቢያተኩሩም ይመክራሉ ። ኅብረተሰቡ የመጠጥ ውኃን አፍልቶ እንዲጠቀም፤ ጥሩ የንጽሕና አጠባበቅ እንዲኖረው ትምህርት መስጠቱ ላይ ሊተኮርም ይገባል ይላሉ ። ቀላል የሚመስሉ ግን እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ልማዶችን ማለትም፦ እጅን መታጠብ፣ ንጹሕ እና አስተማማኝ የውኃሃ ምንጮች አቅርቦቶችን ማሳደግ፤ እንዲሁም የውኃ ጥራት ምርመራ እና ክትትልን ማጎልበት ልብ ሊባልበት እንደሚገባም ጠቁመዋል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ/ኬት ሐሪሰን
ኂሩት መለሠ