1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አል-ነጃሺ የቱሪስት መንደር

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 30 2016

በትግራይ ክልል የሚገኘው እና በጦርነት ወቅት የተጎዳው የአል ነጃሺ መስጂድ መልሶ ለመገንባት ያቀደ መርሐ ግብር ይፋ ተደረገ። የኢትዮጵያ እና የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት እና አል ነጃሺ መልሶ ግንባታ እና ልማት በጋራ የጀመሩት ዕቅድ በታሪካዊው ቦታ ለገብኚዎች የሚሆን መንደር መገንባትን የሚጨምር ነው።

https://p.dw.com/p/4fdnI
BG Tigray | Negash
ምስል Maria Gerth-Niculescu/DW

አል-ነጃሺ የቱሪስት መንደር

ትናንት ምሽት አዲስ አበባ ውስጥ መርሃግብሩ በተካሄደበት ወቅት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼኽ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ የጥንታዊ ታሪክ ባለቤት የሆነውን አል-ነጃሺ መስጂድ እና በዙሪያው የሚገኘውን መካነ መቃብር በማልማት ዓለም አቀፍ የእስልምና መካነ ቅርስ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

መካነ ቅርሱ ለሀገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ መጎልበት ያለውን የላቀ ፋይዳ በመገንዘብ መንግሥትም ለመካነ ቅርሱ መልማት ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጥ ተጠይቋል።

አልነጃሺን የማልማት ውጥን

በታካዊው ስፍራው የመንደር ግንባታ ውጥኑን በተመለከተና በትናንትናው እለት የፌዴራል እና ትግራይ ክልል እስልምና ጠቅላይ ምክር ቤቶች በጋራ ያስተባበሩትን መርሃ ግብር በማስመልከት አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የአልነጃሺ መልሶ ግንባታ እና ልማት ኢኒሼቲቭ ስራ አስከያጅ ሀሰን መሃመድ ሳለህ፤ የመርሃግብሩ ዋና ዓለማ የንጉስ ነጃሺ ታሪካዊ ስፍራን ለዓለም ቱሪዝም መስዕብ ማድረግ ነው ይላሉ፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ዋና ጽህፈት ቤት
በጦርነት የተጎዳው አል ነጃሺ መስጂድ ተመልሶ የሚገነባው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት እና አል ነጃሺ መልሶ ግንባታ እና ልማት በጋራ በጀመሩት ጥረት መሆኑ ተገልጿል። ምስል EIASC

አልነጃሺ በአፍሪቃ የመጀመርያዉ መስጊድ 

“የዚህ ንቅናቄ ዋና ዓለማው የንጉስ ነጃሺ ታሪካዊ ስፍራን ለቱሪዝም እና ሌሎች አገለግሎቶች ዝግጁ ማድረግ ነው፡፡ ቅርሱ የዓለማ ቅርስ ነው፡፡ የትኛውም ስፍራ የሚኖር ሙስሊም ስለ ንጉሱ በጎ መግብር ያውቀዋልና መጎብነት ይፈልጋሉ፡፡ ግን ደግሞ ለቱሪስት የሚሆን በቂ መሰረተ ልማት የለም፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ጀምሮ እስከ ትልልቅ ሆቴሎች በስፍራው እዲገነቡ ነው የታቀደው፡፡ ንጉስ ነጃሺ በዚህ ስፍራ እስላሞች ከሀገራቸው በግፍ ስሰደዱ ከለላ ሰጥተዋል፡፡ ይህን ቦታ ለማልማት ነው ትናንት የማብሰሪያ መርሃግብር የተጀመረው”

ቦታውን ለማልማት የአገራት ፍላጎት

በትናንት ምሽት መርሃግብሩ ኮሚቴን የማዋቀር ስራ መሰራቱ የተነገረም ሲሆን፤ የኮሚቴው ሚና ጥናት አከናውኖ ወደ ተግባር ስራ መግባት ነው ተብሏልም፡፡ ተጠሪነታቸው ለኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት እና ለትግራይ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ይሆናል የተባለው አስራ 11 ዐቢይ ኮሚቴ መዋቀሩም በዚሁ ተነገግሯል፡፡

ሁለቱ መጅሎሰች (የፌዴራል እና የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤቶች) ይመሩታል የተባለውን ይህን ፕሮጀጀክት ብዙ ሀገራት ለመደገፍ ፍላጎት ስለማሳየታቸውም ተነግሯል፡፡ “ይህን ቦታ ለማልማት ብዙ የዓለማቀፍ ተቋማት እና ሀገራ የማልማት ፍላጎት አላቸው፡፡ በትናንት መርሃገብሩ የተሳተፉ ኤምባሲዎችም ህንኑን ያረጋገጡ ብዙ ናቸው” ያሉት ሀሰን በቀጣይ ወደ ስራው ተገብቶ የፋይናንስ ጥያቄዎች እንዲቀርቡ የጠየቁም መኖራቸው አስረድተዋል፡፡

 የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት
ተጠሪነታቸው ለኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት እና ለትግራይ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ይሆናል የተባለው 11 ዐቢይ ኮሚቴ መዋቀሩም በዚሁ ተነገግሯል፡፡ምስል Million Hailesilassie/DW

አልነጃሺ ከሁለት ዓመታት በፊት በተካሄደው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ወቅት የደረሰበት ጉዳትም በዚሁ እንደሚጠገን ተብራርቷል፡፡ “በጦርነቱ ወቅት በተለይም በመስጊድ ላይ የደረሰው ጉዳትም በዚሁ ፕሮጀክት ስር ለመጠገን ነው የታሰበው” ተብሏል፡፡

በሙስሊሞች ፈታኝ ወቅት ከለላ በመስጠት የመኪታወቁት ንጉስ አል-ነጃሺ የሚዘከሩበት የቱሪስት መንደሩ ደረጃውን የጠበቀ ሙዚየም፣ ሀላል ሆቴሎችና ሎጆች፣ ቤተ እምነት፣ የጥናትና ምርምር ተቋም፣ ዩኒቨርሲቲ፣ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ፣ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት፣ ደረጃውን የጠበቀ የጤና ተቋም፣ ለህዝብ አገልገሎት የሚውል የስፖርት ማዘውተሪያ፣ መሰብሰቢያ አዳራሽ እና ሌሎች አገልግሎቶችን እንደሚያካትት ተጠቁሟል።

ሥዩም ጌቱ 
እሸቴ በቀለ
ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር