1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኔልሰን ማንዴላ፣ የነጻነት ተምሳሌት

ረቡዕ፣ የካቲት 21 2010

ኔልሰን ማንዴላ ከአፍሪቃ ዋነኛ የነጻናት ተምሳሌቶች እና ተወዳጅ የነጻነት ታጋዮች አንዱ ናቸው። የነጭ አገዛዝን እምቢኝ በማለታቸው ለሦስት ዐሥርት ዓመታት ያኽል እስር ቤት ቅቀዋል።

https://p.dw.com/p/33Slj
John Adams Nelson Mandela
ምስል picture-alliance/dpa/B. Curtis

ያም ኾኖ ግን ሠላም፣ ዲሞክራሲ እና ነጻነት ለሁሉም ሲሉ ሰብከዋል። ሀገራቸውም ከዘር መድልዎ አገዛዝ እንድትላቀቅ በመርዳት የደቡብ አፍሪቃ የመጀመሪያው ጥቊር ፕሬዚዳንት ኾነዋል። አንደበተ-ርቱእ፣ ትሁት እና ሆደ-ቡቡ በመኾናቸውም ይታወሳሉ።
"እዚህ ከፊታችሁ የቆምኩት እንደ ነቢይ አይደለም፤ እንደ ትሁት የሕዝብ አገልጋይ እንጂ። ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትሉ በጀግንነት መስዋዕት መኾናችሁ ዛሬ እዚህ እፊታችሁ እንድቆም አስችሎኛል። እኔ ደግሞ በበኩሌ ቀሪ ሕይወቴን ለእናንተ እሰጣለሁ።"

ኔልሰን ማንዴላ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1990 ከእስር መለቀቃቸው ለደቡብ አፍሪቃ ወሳኝ ምዕራፍ ነበር። የእሳቸው መፈታት የዘር መድልዎ አገዛዝ የማክተሙ፣ የነጭ የበላይነት አስተዳደር መመናመኑም ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል። እንደ ፖለቲከኛ ለ27 ዓመታት እስር ቤት ተወርውረው እንኳን ማንዴላ ለሀገራቸው ሕልም ነበራቸው፦ ደቡብ አፍሪቃውያንን አንድ በማድረግ እርቀ-ሠላም ፈጥሮ ኅብረተሰቡን በዘር ከፍሎ የነበረው መሪር የዘር መድልዎ አገዛዝ እንዲያከትም ማስቻል። «ሕብረ-ብሔራዊ ሀገር» የመፍጠር ሕልማቸውንም ለማሳካት ተግተዋል። የቆዳ ቀለሙ ምንም ይሁን ምን የሁሉም ዜጎች ሰብአዊ መብቶች የሚከበሩባት፤ ነጻ ትምሕርት የሚሰጥባት ብሎም አቅመ-ደካሞች መጠለያ የሚያገኙባት ደቡብ አፍሪቃን ለመፍጠር ታትረዋል።  እውን ያ ሕልማቸው ግን ሙሉ ለሙሉ ተሳክቷል? በርካቶች ይጠራጠራሉ።

ከእስር ከተፈቱ ከአራት ዓመታት በኋላ በተደረገው የመጀመሪያው ኹሉን ዘር ያሳተፈ ምርጫ የማንዴላ ፓርቲ «የአፍሪቃ ብሔራዊ ምክር ቤት» በሰፋ ልዩነት ድል ተቀዳጀ። ኔልሰን ማንዴላም የመጀመሪያው የሀገሪቱ ጥቊር ፕሬዚዳንት ኾኑ። 

Tribut für Nelson Mandela
ምስል picture-alliance/dpa

ደቡብ አፍሪቃውያን ከኔልሰን ማንዴላ ተምሳሌቶች ብዙ ሊማሩ ይችላሉ ይላሉ የደቡብ አፍሪቃው የኔልሰን ማንዴላ ተቋም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሴሎ ሐታንግ። ማንዴላ ራሳቸውን መስዋዕት ማድረጋቸው እና ለሕዝባቸው መቆርቆራቸው የሚደነቅ ነው፤ ግን በዚያ ብቻ የሚወሰን አይደለም ሲሉ ያክላሉ ሴሎ ሐታንግ።   

“ምንም እንኳን በአራት ግድግዳዎች ተወስነው በእስር ቢማቅቊም ከአራቱ ግድግዳዎች ባሻገር የነበረው የዓለም እይታቸው ግን በኾነ አንዳች አይነት እስር ቤት ለምንገኝ፣ በድህነት ወህኒ ለተወረወርን፣ በኢ-ፍትኃዊነት ማነቆ ለተያዝን ለእኛ ትምህርት ነው።”

በብዙ የሀገሬው ሰው ማዲባ በሚል ስያሜ የሚቆላመጡት ኔልሰን ማንዴላ በደቡብ አፍሪቃ እና በዓለም ዙሪያ የበርካቶች አብነት ለመኾን ጊዜ አልወሰደባቸውም። ማንዴላ ከበርካታ የአፍሪቃ ርእሳነ-ብሔራት በተለየ መልኩ በመንበረ-ሥልጣን ከአንድ ጊዜ በላይ ላለመቆየት በመሰናቸውም ይታወቃሉ። 

ያም ኾኖ ግን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2013 ማንዴላ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ወጣት ደቡብ አፍሪቃውያን የማንዴላ ሕልም ዕውን ስለመኾኑ ማጠየቅ ይዘዋል። የሃያ ሦስት ዓመቷ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዋ ራቲድዞ ሞኮምቤ አንዷ ናት። 

“ደቡብ አፍሪቃውያንን ሽጧቸዋል፤ ምክንያቱም ጭራሽ ዕውን የማይኾን ሕልም ነው ያስታቀፋቸው። የነበረው ርእዮተ-ዓለም ድንቅ ነው፤ ግን ተግባራዊ ኾኗል? በጭራሽ! ስለዚህ ደቡብ አፍሪቃውያንን ሕልም አስታቅፎ ሸጧቸዋል፤ እናም ዛሬም ያኔ ስንታገል እንደነበርነው በተመሳሳዩ እየታገልን ነው።”

Johannesburg Kinder in Alexandra Township mandela Wandbild
ምስል Getty Images/J. Mitchell

ብዙኃኑ ደቡብ አፍሪቃዊ አሁንም ድረስ በድህነት አረንቋ እና በሥራ አጥነት ይማቅቃል። የከፋው ደግሞ ከደቡብ አፍሪቃ የዘር መድልዎ አገዛዝ ወዲህ የነዋሪው ገቢ የሰማይና የምድር ያኽል መራራቊ ነው። ምንም እንኳን የኔልሰን ማንዴላን ሕልም ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ለመተግበር ቢያዳግትም ቅሉ ለማንዴላ ተቋም ባልደረባው ሴላ ሐታንግ ግን የማዲባ መርኆዎች ጠንካራ የሞራል ልዕልና ይሰጣቸዋል። ማንኛውም ደቡብ አፍሪቃዊ ማዲባ በማድርገው ይኮራብኛል? ሲል ሊጠይቅ ይገባልም ይላሉ።   

“ማዲባ ሕልመኛ ግን ደግሞ የተግባር ሰው ስለነበር ሕልሙን የምጠቀምበት መንገድ እሱን ያኮራው ይኾን ብሎ መጠየቅ ያሻል። እናም ምን ያኽል ሕልመኛ እንደሆንክ ራስህን መጠየቅ ያሻል። ስለዚህ  'የተበላሸውን ነገር ፈር ለማስያዝ፤ በሀገራችንም በተሳሳተ መንገድ የሚነጉደውን ነገር ለማስቆም የቻልኩትን ያኽል እየሠራሁ ነው ወይ ማለት ያስፈልጋል።'”

ቪክቶርያ አቨሪል/ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሀመድ

 ይህ ዘገባ አፍሪካዊ ሥረ-መሠረት በሚል ከጌርዳ ሔንክል ተቋም ጋር በመተባበር የሚቀርብ ልዩ ዝግጅት አንድ አካል ነው።

This report is part of African Roots, a project realized in cooperation with the Gerda Henkel foundation.