1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተደራዳሪዎች ሳይስማሙ ቢለያዩም ተስፋ አያስቆርጥም ፤ አስተያየት ሰጭዎች

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 25 2015

ላለፉት ዘጠኝ ቀናት በታንዛንያዋ ደሴት ዛንዚባር በኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስት እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል ሲካሄድ የቆየው ድርድር ዛሬ መጠናቀቁን ሁለቱም ተደራዳሪዎች በየፊናቸው ገልጸዋል። የመንግስት ኮሙኒኬሽን «ውይይቱ በአብዛኛው በአዎንታዊ መልኩ የተከናወነ» ነገር ግን በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት አለመደረሱን ዐስታውቋል ።

https://p.dw.com/p/4QrF9
Karte Sodo Ethiopia ENG

የፌደራል መንግስት ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጋር ያደረገው የሰላም ንግግር አንድምታ

ላለፉት ዘጠኝ ቀናት በታንዛንያዋ ደሴት ዛንዚባር በኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስት እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል ሲካሄድ የቆየው ድርድር ዛሬ መጠናቀቁን ሁለቱም ተደራዳሪዎች በየፊናቸው ገልጸዋል። የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚንስቴር «የመጀመሪያ ምዕራፍ መጠናቀቁን» ባመለከተበት የዛሬ መግለጫው «ውይይቱ በአብዛኛው በአዎንታዊ መልኩ የተከናወነ»  ነገር ግን በዚህኛው ምዕራፍ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት መድረስ  እንዳልተቻለ ዐስታውቋል። የኦሮሞ ነጻነት ጦር በበኩሉ « በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ደርሰናል፤ በአንዳንዶች ግን ገና ከስምምነት አልደረስንም» ብሏል። ውይይቱ በሌላ ምዕራፍ እንደሚቀጥል ከስምምነት መደረሱን  ባወጣው መግለጫ ገልጿል።

በሁለቱ ወገኖች መካከል ሲደረግ ቆይቶ ዛሬ የተጠናቀቀው ንግግሩ በበርካቶች ዘንድ ሲጠበቅ ቆይቷል። ነዋሪነታቸውን በስዊዲን ያደረጉት አቶ ያያ በሽር  በኦሮሞ ነጻነት ግንባር ቃል አቃባይ የነበሩ ናቸው። በማሊሞ ዩኒቨርሲቲ ከሚሰሩት የጥናት ስራቸው ጎን ለጎን አሁንም ድረስ  በኦሮሞ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ የነቃ  ተሳትፎ እንዳላቸው ይናገራሉ። በሁለቱ ወገኖች መካከል ሲደረግ የነበረውን ድርድር ከመጀመሪያው በቀላሉ ከስምምነት እንደማይደረስ ይጠብቁ እንደነበር ይናገራሉ።

« በኦሮሚያ ክልል የነበረው አለመግባባት ከሰሜኑ ጦርነትም ይለያል ። ምክንያቱም ከተመሳሳይ ማህበራዊ አካባቢ የወጡ የፖለቲካ ምሁራን ናቸው በስልጣን ላይም ያሉ በትጥቅ ትግሉ ውስጥም ያሉ ፤ ስለዚህ ይሄንን ነገር ለማግባባት ቀላል ሊመስል ይችላል፤ ነገርግን ወደ ዝርዝር ነገር ሲገባ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል  እገምት ነበር።»

በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች መካከል ሲደረግ ከነበረው ደም አፋሳሽ ጦርነት አንጻር የመጀመሪያውን ዙር ድርድር እንዳልተሳካ መቁጠር አይገባም የሚሉት አቶ ያያ ነገር ግን ተቀራርበው መነጋገራቸውን በራሱ ተስፋ ሰጭ መሆኑን ነው የሚገልጹት ።

«እኔ በተስፋ ነው ያየሁት ፤ምክንያቱም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል ብዬ በጣም የምሰጋቸው ነገሮች ስለነበሩ »

የወሊሶ ከተማ ነዋሪው አቶ ብርሃኑም የዚሁ ሃሳብ ተጋሪ ናቸው ። ሁለቱ ወገኖች በጠረጴዛ ዙሪያ ለመነጋገር መቀመጣቸውን አበረታች ነው ሲሉ ነው የሚገልጹት ።

«እንግዲህ ሙሉ በሙሉ በአንድ ቀን  ወደ መስማማት ደረጃ ይደረሳል ተብሎም አይጠበቅም ግን እንደቅድመ ሁኔታ አንዳንድ የሚስተካከሉ ነገሮች ይሊኖሩ ይችላሉ ፤ ስለዚህ ቀርበው አንድ ላይ በጠረጴዛ ዙሪያ ቁች ብለው መወያየታቸው ራሱ አንድ እርምጃ ነው።»

ዘርትሁን ተሾመ ትውልዷ በነቀምቴ ከተማ ነው ። በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የነቃ ተሳትፎ ታደርጋለች። ተደራዳሪዎች ወደ ድርድር እንዲሄዱ ብርቱ ግፊት ሲያደርጉ ከነበሩ ሰዎች አንዷ መሆኗን በመጥቀስ በአንድ ምሽት የሚመጣ ትልቅ ውጤት የለም ባይ ናት።

« ይህን የሰላም ንግግር ሁላችንም ስንታገልለት እና ጫና ስንፈጥርበት ነበረ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እና ወደዚህ ሲመጣ በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ በአንዴ ስምምነት ላይመጣ ይችላል ፤ በሂደት ነው የሚመጣው»

በፌዴራል መንግስት እና በኦሮሞ ነጻነት ጦር መካከል የተጀመረው የሰላም ንግግር ቀጣይነት እንዲኖረው ከህዝቡም ከዓለማቀፉ ማህበረሰብም ጫናው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የሚጠይቁት አቶ ያያ በሽር ናቸው።

ዘርትሁን እንደምትለው ተደራዳሪዎቹ በቀጣይ የድርድር ምዕራፍ የህዝብን ጥቅም ማስቀደም ተቀዳሚ ዓላማቸው ማድረግ እንዳለባቸው ነው የምታሳስበው።

አቶ ብርሃኑ በበኩላቸው በድርድሩ ሌሎች ተጨማሪ ሶስተኛ ወገን አደራዳሪዎችን አካቶ መቀጠል እንዳለበት ነው ያሳሰቡት  ።

ታምራት ዲንሳ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሄር