1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ባሕላዊ የግጭት አፈታት በሱሪና በሸኮ ብሔረሰቦች

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 27 2015

በተለይ የተፈጸመው ወንጀል የግድያ ከሆነ በዳይና ተበዳይ በደም ለማስተሳሰር ከገዳይ ቤተሰብ ለሟች ቤተሰብ ልጃገረድ ተድራለት በደም እንዲጋመዱ በማድረግ ጥሉ እስከወድያኛው እንዲሸኝ ይደረጋል።

https://p.dw.com/p/4LjLg
South West Ethiopia People Region Emblem
ምስል South West Ethiopia People Region government Communication Affairs Bureau

ባሕላዊ የግጭት አፈታት በሱሪና በሸኮ ብሔረሰቦች

በመላ ሐገሪቱ እዚህም እዚያም ግጭት፣ ሞት፣ ማፈናቀል መፈናቀል እለታዊ ወሬ ከሆነ ውሎ አድሯል። በግጭቶች አፈታት አገር በቀል ዘዴዎች በየአካባቢው ቢለያዩም አብዛኞቹ ግጭትና ጠብን ለማብረድ ጠቃሚ ናቸዉ። በዛሬዉ የባሕል መድረክ ዝግጅታችን  ቀደም ሲል «ሱርማ» እየተባለ ይጠራ በነበረው የሱሪና የሸኮ ብሔረሰቦች ባሕላዊ የግጭት አፈታት ስርዓቶችና ተያያዥ  ባሕላዊ እሴቶችን እንመለከታለን። 
                                      
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በሱሪ ወረዳና በአጎራባች ቤሮ ወረዳ የሚገኘው የሱሪ ብሔረሰብ ተዝቀው ከማያልቁ ባሕላዊ ክንውኖች መካከል የግጭት አፈታቱ በአስተማሪነቱ የሚጠቀስ ነው። በግለሰብ ደረጃ፣ ባልና ሚስት አልያም በጎሳ መካከል ግጭት ሲፈጠር አጥፊ ወይም ተበዳይ የሚጠለሉበት እራሱን የቻለ ቦታ አለ። ወንዶች የሚጠለሉበት ``ቦሎይ`` ሲባል ሴቶች የሚጠለሉበት ቦታ ደግሞ ``ራታ`` ይባላል። በአጥር የተከለለ ቦታ ነው። በግጭት ወቅት ሸሽቶ የመጣ ሰው እዚያ ይጠለላል። የሐገር ሽማግሌዎች  ያነጋግሩታል። ጉዳዬ በእርቅ እስኪፈጸም ድረስ ማሕበረሰቡ የሚያስፈልገውን ቀለብ እያቀረበ የሚቆይበት ቦታ ነው። የሴቶች ራታ ደግሞ የተቸገሩ የሚረዱበት ማሕበራዊ ስራዎቻቸውን የሚከውኑበት፣ የሚመካከሩበት ቦታ ነው ራታ። ከባሏ የተጋጨችም ታርቃ ወደ መደበኛ ቤትዋ እስክትገባ የምትቆይበት  ነው።`
ጋዜጠኛ፣ ደራሲና የፊልም ዳይሬክተር ዋሲሁን አራጌ በአካባቢው ሲኖር የሰነደውን «የጊዜ ሚዛን» በሚል ርእስ ባሳተመው መጽሐፍ  ለተደራስያን አብቅቶታል። ዋሲሁን ስለ ቦሎይና ራታ እንዲህ አወጋን።
 ``ራታ ሴቶች ብቻ የሚሰበሰቡበት ሲሆን፣ ቦሎይ ደግሞ የወንዶች ቦታ ነው። በአጥር የከለለ ቦታ ነው። አሁን ከትዳርህ ጋ ብትጣላ ሸሽተህ የምትሄደው እዛ ነው። የአገር ሽማግሌዎች መጥተው የደረሰብህን ነገር ይጠይቁሃል፣ ታስረዳለህ። በተለያዩ ግጭቶች የተሳተፉ ሰዎችም ወዛው ይሄዳሉ። ዛ የሐገር ሽማግሌዎች መጥው ካነጋገሩህ ቦኋላ ወደ እርቅ ስነስርአት ይኬዳል ማለት ነው።``
ራታና ቦሎይ  የተጋጩት ብቻ ሳይሆኑ የተቸገሩ ሰዎችም ይጠለሉባቸዋል። ማሕበረ ሰቡ እዚያ የተጠለለ ሰው ካየ በምን ሁኔታ እንደተጠለለ ካረጋገጠ ቦኋላ ለተቸገረው የዕለት ጉርስ እያዋጣ ይቀልበዋል ። በዘላቂነት ለማቋቋም  ደግሞ የሃገር ሽማግሌዎች ተመካክረው ወርቅ ተቆፍሮም ይሁን ሐብት ተሰባስቦ እንዲሰጣቸው በማድረግ እንዲቋቋሙ እንደሚደረግ ዋሲሁን አራጌ አጫውቶናል።
ቦሎይና ራታ ሌላ  ከዚሕም በተጨማሪ የተበደለ ብቻ ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ ይሁን በማሕበረሰብ ደራጃ ከቀላላል እስከ ከባድ ወንጀል የፈጸመ ሰውም ይጠለልበታል። የሐገር ሽማግሌዎች መጥተው ሲያናግሩት የፈጸመውን በደል በዝርዝር አስረድቶ እንዲያስታርቁት ይማጸናል።
ጋዜጠኛና ደራሲ ዋሲሁን አራጌ በመጽሀፉ ከዳሰሳቸው ጉዳዮች በተመሳሳይ የሸኮ ብሔረሰብ ባሕላዊ የግጭት አፈታት ስርዓት ነው። በዳይና ተበዳይ በይቅርታ ተሸማግለው ሰላም የሚያወርዱበት ድንቅ ባሕላዊ ሐብት አላቸው። በተለይ የተፈጸመው ወንጀል የግድያ ከሆነ በዳይና ተበዳይ በደም ለማስተሳሰር ከገዳይ ቤተሰብ ለሟች ቤተሰብ ልጃገረድ ተድራለት በደም እንዲጋመዱ በማድረግ ጥሉ እስከወድያኛው እንዲሸኝ ይደረጋል።

`` ባሕላዊ የሸኮዎች የዕርቅ ስነስርዓትም በጣም የሚገርም ነው። የተጋጩ ሰዎችን ለማስታረቅ ኮባ ይቆረጣል፣ በግ ይታረድና አንጀቱን የሐገር ሽማግሌዎች ይይዙና የተጣሉ ሰዎች በዚያ ሥር ሾልከው እንዲያልፉ ይደረጋል። ይህ ማለት ድጋሚ ብንጋጭ አንጀታችን እንደዚህ ይበጣጠስ የሚል ትርጉም አለው። የተፈጸመው ወንጀል የነፍስ ግድያ ከሆነ ከሟችና ከገዳይ ቤተሰቦች ሴትና ወንድ  ወጣቶች ተመርጠዉ እንዲጋቡ ይደረጋል። ጸቡ ድጋሚ እንዳያገረሽ በዚሁ መልኩ በጋብቻ እንዲተሳሰሩ ያደርጋሉ። 

ሌላው ሱሪዎችን የሚያደርጋቸው ለሴቶች የሚሰጡት አክብሮት ነው። ማንኛውም የሱሪ ወጣት ሴት ልጅ ዕቃ ተሸክማ ስትሄድ ካያት ከሚሄድበት ጉዳይ አቋርጦ ወደገበያም ሆነ ወደቤቷ ዕቃውን ተሸክሞ የማድረስ ግዴታ አለበት። በአንድ ወቅት የዓፋሮች ባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓትን በተመለከተ ቃለምልልስ ባደረግንበት ወቅት አንድ የዓፋር ሽማግሌ `` በአሁኑ ወቅት ሽማግሌ እየተከበረ አደለም። የአገር ሽማግሌ የሚጠራው ችግሩ የታጠቁ የመንግስት ሃይሎች ገብተውበት የባሰ ግድያ ተፈጽሞ ውስብስብ ካለ ቦኋላ ነው። ለያውም ባሕላዊ እሴቱን ጠባቆ ሳይሆን የሰላም ኮንፈረንስ በሚል ጊዚያዊ መፍትሄ ያመጣል፣ ችግሩ ግን በነጋታው በተመሳሳይ ይፈጸማል`` ሲሉ ገልጸውልን ነበር። ዋሲሁን አራጌም በአይኑ ከተመለከተው ልምድ ተነስቶ ሐሳቡን ይጋራል። አሁን በሚታዩ ግጭቶች በመፍታት የሐገር ሽማግሌዎችና ባሕላዊ የግጭት አፈታቶች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ በማሳሰብ።
በዚህ ጉዳይ ላይ የተደረጉ ጥናቶች ካሉ፣ ባሕላዊ የግጭት አፈታቱ አሁን ካለው የአገሪቱ ችግር አንጻር ምን ያህል ሥራ ላይ እየዋለ ነው ብለን በደቡብ ምዕራብ ክልል የባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የታሪክና ቅርስ ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘን ስናበቃ ስልካቸዉን ስላላነሱ ሓሳባቸውን ማካካተት አልቻልንም። የፌደራል ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴርም መስሪያቤታቸው ከክልሎች ጥያቄ ሲቀርብ በባሕላዊ ጉዳዮች ላይ ጥናቶች እንደሚያካሂድ በመግለጽ በዚህ ጉዳይ ላይ ግን ምንም አይነት ጥናት እንዳልተደረገ ተነግሮናል።
ለዛሬ ያዘጋጀነውን  በዚሁ አበቃ።  እስከ ሳምንት በሰላም ቆዩ።

Wasihun Arage Äthiopien Künstler
ጋዜጠኛና ደራሲ ዋሲሁን አራጌምስል privat

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ነጋሽ መሐመድ