1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአዲስ አበባ የጁመዓ ጸሎት በሰላም ተከናውኗል

ዓርብ፣ ሰኔ 2 2015

ባለፉት ተከታታይ ሁለት ሳምንታት አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው በታላቁ አኑዋር መስጊድ አጋጥሞ የነበረው የፀጥታ መደፍረስ ስጋት ዛሬ በተረጋጋ ሁኔታ አልፏል። ይሁንና ያለፉት ሁለት ሳምንታት ክስተቶች ባጫሩት ስጋት ምክንያት ለወትሮ በሰው እና ተሽከርካሪዎች የሚጨናነቀው መርካቶ ዛሬ እጅጉን ተቀዛቅዞ መዋሉን የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ተመልክቷል፡፡

https://p.dw.com/p/4SOQX
Äthiopien Addis Ababa | Proteste | Anwar Moschee
ምስል Seyoum Getu/DW

አዲስ አበባ መርካቶ አካባቢ ዕለቱ ተቀዛቀዘ ሁኔታ አልፏል

ባለፉት ተከታታይ ሁለት ሳምንታት አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው በታላቁ አኑዋር መስጊድ አጋጥሞ የነበረው የፀጥታ መደፍረስ ስጋት ዛሬ በተረጋጋ ሁኔታ አልፏል። 

ይሁንና ያለፉት ሁለት ሳምንታት ክስተቶች ባጫሩት ስጋት ምክንያት ለወትሮ በሰው እና ተሽከርካሪዎች የሚጨናነቀው መርካቶ ዛሬ እጅጉን ተቀዛቅዞ መዋሉን የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ተመልክቷል፡፡በተለም ከእኩለ ቀን 6፡00 እስከ 9፡00 ሰዓት በአከባቢው ቅኝት ያደረገው ዘጋቢችን ከውስን ሱቆች በስተቀር አብዛኞቹ ዝግ መሆናቸውን  ተመልክቷል፡፡

ባለፉት ሁለት ተከታታይ የጁመዓ ሶላት መርሃ ግብር የከፋ የፀጥታ ስጋት ያጋጠመው አዲስ አበባ መርካቶ አከባቢ የሚገኘው ታላቁ የአንዋር መስጊድ አከባቢ ዛሬ እጅጉን በተቀዛቀዘ ድባብ ነው ያለፈው፡፡ በመስጊዱ ዙሪያ የሚገኙ በርካታ የጅምላ እና ችርቻሮ ሱቆች ግን ተዘግተው ውለዋል፡፡ መስጊዱ የሚገኝበት በተለምዶ ጎጃም በረንዳ ተብሎ የሚታወቀው አከባቢ እና መላው መርካቶም እጅግ በተቀዛቀዘ ድባብ ነው ቀኑን ያሳለፈው፡፡ ወትሮም በሰውና ተሸከርካሪዎች የሚጨናነቀው ይህ አከባቢ፤ በርካታ ሱቆች በመዘጋታቸውም እለቱ የበዓል እንጂ የአዘቦት ቀንም አይመስልም፡፡ በዚህ የሚያልፉ ተሽከርካሪዎች ብዛትም እጅግ ውስን ሆነው ተስተውለዋል፡፡

በመስጊዱ ዙሪያም ሆነ በአከባቢው እንደባለፉት ሁለት ሳምንታት ግን የፀጥታ ኃይሎች ዝውውር ጎልቶ አልተስተዋለም፡፡ በአንዋር መስጊድ የጁመዓ ሶላትን ሰግደው ሲወጡ ያነጋገርኳቸው አንድ የአከባቢው ነዋሪ የዛሬው ሶላት ፍጹም ሰላማዊ መሆኑን ገልጸው፤ የፀጥታ ሃይሎች ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከመጠን በላይ በዝተው መስጊዱን መክበባቸው ለግጭት መፈጠር ምክኒያት ነበር የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ “ዛሬ እንደምታየው በመስጊዳችን ሶላት ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ነው የተጠናቀቀው፡፡ በተለየውም መስጊድ ውስጥ እንደወትሮው ሰው ሞልተው ነው የሰገድነው፡፡ ባለፉት ሁለት ሳምንታትም ለጥበቃ የተሰማሩ የፖሊስ ኃይሎች በመብዛታቸው ነው ከአማኙ ጋር ግጭት የፈጠሩት፡፡ ፈጣሪ ይመስገን ዛሬ እንዳየሄው ምንም አይነት ፖሊስም በመስጊድ ዙሪያ የለም በሰላምም ነው ሶላታችን የተጠናቀቀው፡፡”

ታላቁ አኑዋር መስጊድ የሚገንበት ቦታ፤ አዲስ አበባ
ታላቁ አኑዋር መስጊድ የሚገንበት ቦታ፤ አዲስ አበባምስል Seyoum Getu/DW

በሸገር ከተማ የከተማዋን ፕላን የሚጣረዙና ህጋዊነትን ባልተከተለ መንገድ ተገንብተዋል የተባሉ መስጊዶች መፍረሳቸውን በመቃወም ባለፉት ሁለት ተከታታይ የጁመዓ ሶላት  ፖሊስ ከምዕመናን ጋር ግጭት ውስጥ መግባቱን ተከትሎ ቢያንስ የአምስት ሰዎች ህይወት ማለፉ እና እስካሁንም በውል ያልተገለጸ በርካታ ሰዎች መጎዳታቸው አይዘነጋም፡፡ ይህንኑን ተከትሎ ከትናንት በስቲያ ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና ከሌሎች ባለስልጣናት ጋር ተወያይቶ ትናንት መግለጫ የሰጠው የኢትዮጵያ እስልማን ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ልዩነቶችን በመነጋገር ለመፍታት ከስምምነት ተደርሷል በማለት የሚደረገው ተቃውሞ እንዲረግብ መጠየቁም ይታወሳል፡፡

በአዲስ አበባ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ እስልማና ጉዳዮች ምክር ቤት ስራ አስፈጻሚ ሐጂ ባህሩ ተማም አብደላ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩትም፤ መሪ ተቋሙ ያስተላለፈው መልእክት ለዛሬው ሶላት ወደ ሰላማዊ ስርዓቱ መመለስ ጉልህ ድርሻ አለው፡፡ “ባለፉት ጊዜያት የተፈጠረውን አለመረጋጋት ተከትሎ ከሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት ጋር በመነጋገር የተደረሰው መፍትሄ ፈጣሪ ይመስገን ሰላማችንን መልሶልናል፡፡ ዛሬ የእራሳችን በጎ ፈቃደኞች አሰማራን እንጂ ፖሊስም በአከባቢው አልነበረም፡፡ በርግጥ ዛሬ ስጋቶች ስለነበሩ አከባቢው ተቀዛቅዟል፡፡ ይሁንና መሪው ተቋማችን በሰጠው አቅጣጫ በመመራት እና በመደማመጥ ህዝቡ ወደ ነበረው መረጋጋት መመለስ አለበት፡፡”

ባለፈው ሳምንት ከአዲስ አበባ ውጪም በውስን ከተሞች ከጁማ ሶላት በኋላ በተወሰኑ አከባቢዎች ተቃውሞዎች ተሰምተው አለመረጋጋቶች ተስተውለው ነበር፡፡ በዛሬው እለት ግን የተላለፈውን ጥሪ በመቀበል፡ በሁሉም አከባቢዎች ሶላቱ በሰላም መጠናቀቁን አንድ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የስራ ሃላፊ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ “እስካሁን ችግር ተፈጥሮበታል በሚል የቀረበልን ዘገባ የለም፡፡ ሁሉም ቦታ በሰላም ነው የተጠናቀቀው፡፡ መስጂዱ ሁሉ ሶላቱን በሰላም ነው ያሳለፉት፡፡ ሰው ሁሉ ሰግደው በሰላም ወደየበሄታቸው ተመልሰዋል፡፡”  

ሥዩም ጌቱ

ታምራት ዲንሳ

ነጋሽ መሐመድ