1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የነባር ዳኞች ስራ መልቀቅ

ሐሙስ፣ መጋቢት 21 2015

የአማራ ክልል ዳኞች ማኅበር እንደተናገረው ዳኞች በሚፈጠርባቸው ጫናዎች ስራቸውን እየለቀቁ ነው፡፡ባለፉት 6 ወራት ብቻ 103 ዳኞች ከስራቸው በራሳቸው ፈቃድ ለቅቀዋል።ይህም ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ዳኞችን አሳጥቷል ይላል ማኅበሩ። ፍርድ ቤቶች የአዳዲስ ዳኞች መለማመጃ ሆነዋልም ነው የሚለው፡፡ይህም የፍርድ ሂደቱን በከፍተኛ ሁኔታ ይጎዳዋል ብሏል፡፡

https://p.dw.com/p/4PVkQ
Äthiopien Anwaltsvereinigung
ምስል Alemnew Mekonen/DW

በአማራ ክልል አሳሳቢው የነባር ዳኞች ስራ መልቀቅ

በአማራ ክልል የነባር ዳኞች ስራ መልቀቅ በፍርድ ሂደቱ ላይ ጫና እፈጠረ እንደሆነ የአማራ ክልል የዳኞች ማህበር አስታወቀ፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በበኩሉ በውስጣዊና ውጫዊ ገፊ ምክንያቶች አንዳንድ ዳኞች ስራ መልቀቃቸውን ተናግሯል፡፡በአማራ ክልል 2000 ያህል ደኞች እንዳሉ የክልሉ ዳኞች ማህበር መረጃ ያመለክታል፣ ይህ ቁጥር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን የማህበሩ ፕረዚደንት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ፕረዚደንቱ አቶ አበባው ታደሰ እንደተናገሩት ዳኞች በሚፈጠርባቸው ጫናዎች ስራቸውን እየለቀቁ ነው፡፡ ባለፉት 6 ወራት ብቻ 103 ዳኞች ከስራቸው በራሳቸው ፈቃድ ለቅቀዋል፤ ይህም ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ዳኞችን አሳጥቷል የሚሉት አቶ አበባው ፍርድ ቤቶች የአዳዲስ ዳኞች መለማመጃ ሆነዋል ነው ያሉት፡፡ይህም የፍርድ ሂደቱን በከፍተኛ ሁኔታ ይጎዳዋል ብለዋል፡፡
በቅርቡ ከአቃቤ ህግነት ስራቸው በራሳቸው ፈቃድ የለቀቁትና በጠበቃነት ሥራ የተሰማሩት አቶ አደራው አዲሱም ዳኞች የተሻለ ክፍያ አላቸው ቢባልም ምቹ የስራ ሁኔታ ባለመኖሩ የዳኞችና የአቃቤያነ ህግ ፍልሰቱ በርክቷል ብለዋል፡፡ ባለፉት 6 ወራት 96 ዳኞች ከስራቸው መልቀቃቸውን የሚናገሩት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ታዘባቸው ጣሴ በበኩላቸው ከስራቸው ጋር በተያያዘ ከሌላው አካል የሚደርስባቸው ጫና ዳኞች ስራቸውን ለመልቀቅ አንዱ ምክንያት እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
መንግስት ሁኔታዎች እንዲሻሻሉ እያደረገ ቢሆንም ምቹ የስራ ቦታ አለመኖር ዳኞች ደስተኛ ሆነው እንዳይሰሩ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡
በምክትል ቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የአማራ ክልል ፍትህ ባለሙያዎች ማሰልጠኛና የህግ ምርምር ተቋም የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ ዘመንሽ አዱኛው ተቋማቸው በየዓመቱ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸውን 300 ባለሙያዎች የዳኝነትና የአቃቤ ህግ የቅድመ ሥራ ስልጠና በመስጠት ለዳኝነትና አቃቤ ሕግ እንደሚያበቃ ተናግረዋል፡፡ ማነኛውም ከዩኒቨርሲቲ የወጣ ተማሪ በተቋማቸው በኩል አስፈላጊው ስልጠና ሳይሰጠው ወደ ዳኝነትና አቃቤ ህግ ስራ እንደማይሰማራ አመልክተዋል፡፡
በዓመት ከ600 በላይ የህግ ባለሙያዎችን ለማሰልጠን ፍላጎት ቢኖርም በግብዓት፣ በባለሙያና በበጀት እጥረት ምክንት ግማሽ ያህሉን ብቻ ለ9 ወራት የተግባርና የንድፈ ሀሳብ ስልጠና እንደሚሰጥ ወ/ሮ ዘመንሽ ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡
ዓለምነው መኮንን

Äthiopien Anwaltsvereinigung/Abebaw Tadese
አቶ አበባው ታደሰ የአማራ ክልል ዳኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ምስል Alemnew Mekonen/DW

ኂሩት መለሰ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር