1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሸገር ከተማ የቤቶች እና የእምነት ተቋማት ፈረሳ ቆሞ ሕጋዊነቱ እንዲፈተሽ ኦፌኮ ጥሪ አቀረበ

ሐሙስ፣ ግንቦት 24 2015

የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ የሸገር ከተማ አስተዳደር እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የግል ቤቶችን እና የእምነት ተቋማት የማፍረስ ተግባራቸውን በአፋጣኝ አቁመው የእርምጃው ሕጋዊነት እና አተገባበር እንዲፈተሽ ጥሪ አቀረበ። ፓርቲው እርምጃውን "ህጋዊነትን ያልተከተለ እና በተሳሳተ ፖሊሲ ላይ የተመሰረተ" ሲል ተችቷል።

https://p.dw.com/p/4S4mK
Äthiopien Oromo Federalist Congress
ምስል Seyoum Getu/DW

በሸገር ከተማ የቤቶች እና የእምነት ተቋማት ፈረሳ ቆሞ ሕጋዊነቱ እንዲፈተሽ ኦፌኮ ጥሪ አቀረበ

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) "ህገ-ወጥ አሰራርን ተከትሎ ህግን ማስከበር አይቻልም" በሚል ርዕስ ባወጣው ወቅታዊ መግለጫ ከጥቂት ወራት ወዲህ በኦሮሚያ ክልል የሸገር ከተማ መቋቋምን ተከትሎ በስፋት እየተካሄደ ነው ያለው የግለሰቦች የመኖሪያ ቤትና የእምነት ተቋማት ቤቶች የማፍረስ ተግባርን ኮንኗል።  ፓርቲው በአቋም መግለጫው በቤቶቹ ፈረሳ ምክንያት ሺህዎች ቤት አልባ ሆነው በመፈናቀላቸው ጎዳና ላይ እንዲወድቁ ተደርጓልም ብሏል። ቁጥራቸው የተለያየ ቢሆንም ብዛት ያላቸው መስጂዶች፣ ቤተ ክርስቲያናት እና የፕሮቴስታንት ቤተ እምነቶች የአማኞችን ክብር በሚነካ መንገድ በአፍራሽ ግብረ ኃይል በግዳጅ እንዲፈርሱ ተደርገዋልም ነው ያለው።

የፓርቲው ዋና ፀሓፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ በዚሁ ላይ ለዶይቼ ቬለ ባከሉት አስተያየታቸው፤ “በአዲስ አበባ እና ዙሪያ በተለይም ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ ነዋሪዎችን በማፈናቀል ወደ መሬት ንግድ በመግባት ኢኮኖሚውን ያዛቡት በድርጊቱ የመንግስት ባለስልጣናት እጅ በመርዘሙ ነው” ነው ብለዋል፡፡ ኃላፊው አሁን እየፈረሱ ያሉ የግለሰቦች ቤቶች እና የእምነት ተቋማት ለዓመታት የቆዩና ከመንግስት ተቋማት አገልግሎት ሲያገኙ የነበሩ እንዲሁም ከመንግስት የመኒጠበቅባቸውን ኃላፊነትን ሲወጡ የነበሩ ይበዛሉ ሲሉም አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡ ህገወጥ የመሬት ወረራ መኖሩንም ግን እናውቃለን ያሉት የፓርቲው አመራር "ህገ-ወጥነትን በህገወት መንገድ መከላከል አይቻልም" ብለዋልም፡፡

በሸገር ከተማ እየተከናወነ ያለው ይህ የቤትና የእምነት ተቋማት ማፍረስ ተግባር በመሬት ወረራ እና ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የተገነቡ እንዲሁም የከተማዋን ማስተር ፕላን የሚጣረሱ ላይ ብቻ እንደሚያተኩር ባለስልጣናት በተደጋጋሚ መግለጻቸው ይታወቃል፡፡ የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃሉ አዱኛ ትናንት በሰጡት ይፋዊ መግለጫም ይህንኑን አስተያየት አጠናክረዋል፡፡ “አሁን እየተካሄደ ያለው አሉባልታና ማደናገሪያ ዓላመው ፖለቲካዊ ነው፡፡ መንግስት አተኩሮ በአንድ እምነት ላይ ጥቃት እያደረሰ ነው የሚሉ ካለው እውነታ የራቀ ነው፡፡ መንግስት መስጊድም ሆነ የትኛውም እምነት ላይ አተኩሮ ሳይሆን ህጋዊነትን መዓከል አድርጎ እንደሚሰራ ህዝቡ እንድረዳው እንፈልጋለን” ብለዋል፡፡

Äthiopien Vertriebene Menschen bei Legetafo
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በሸገር ከተማ የሚካሔደ የመኖሪያ ቤቶች እና የቤተ እምነቶች ፈረሳ ሕጋዊ ነው ሲል ይሞግታል። በእርምጃው በበርካታ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ቤት አልባ ሆነዋል። ምስል DW/Solomon Muchie

ኦፌኮ ግን ከነዋሪዎች ቅሬታ፣ ጉዳዩን በቅርበት ከተከታተሉና ምርመራ ካከናወኑ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ሪፖርት እንዲሁም ፓርቲው በራሱ ከወሰደው ግምገማ የቤትና የእምነት ተቋማት ቤቶች የማፍረስ ተግባር ህጋዊነትን ያልተከተለ፣ በተሳሳተ ፖሊሲ ላይ የተመሰረተ፣ ወቅታዊነትን ያላገናዘበ፣ አማራጭ መፍትሄዎችን ያላማከለ አድሏዊ ስራ በመሆኑ ዜጎችን ለማህራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አጋልጧል ሲል ወቅሷል።

የኦፌኮ ዋና ፀሓፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ አክለውም ድርጊቱ የተፈጸመው ህብረተሰብን ማወያየት ሳይቀድምና ህጋዊነትን ባልተከተለ ለሙስናም ተጋላጭ በሆነ ሂደት ነው ሲሉ አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡ “አሁን ከምንገኝበት አገራዊ ቀውስ አንጻር ይህ ድርጊት ከመንግስት ቁጥጥርም ውጪ እንዳይሆን እንሰጋለን፡፡ ህገወጥነትን መቆጣጠር አስፈላጊ አይደለም የሚል እምነት የለንም፡፡ ግን የመንግስት ባለስልጣናት ይህን እንደ ንግድ ነው የሚጠቀሙበት የሚል ስጋት አለን፡፡ አፍራሾች የሰውን ንብረት መውሰዳቸው ህገወጥነት ነው ብለንም እናምናለን፡፡” 

ለወራት በሸገር ከተማ ሲከናወን የነበረው የቤቶች ፈረሳ በርካታ ነዋሪዎችን አፈናቅሎ ቅሬታም እንዲያሰሙ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ አሁን ደግሞ በቅርቡ ቤተእመነቶች ላይ ያነጣጠረ የቤቶች ፈረሳ ይከናወናል በሚል ተቃውሞ ባለፈው ሳምንት የሰዎች ህይወትም እንዲቀጠፍ ያደረገ ተቃውሞ በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወሳል፡፡ 

Äthiopien Addis Abeba
በሸገር ከተማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤቶች እና ቤተ እምነቶች ፈረሳ ብርቱ ተቃውሞ ገጥሞታል። ምስል Seyoum Getu/DW

የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ግን ህገወጥ ያሏቸው ቤቶች ፈረሳው ጥንቃቄ በተሞላ መንገድ የሚከወን ነው፡፡ “በህገወጥ ግንባታ ላይ እየተከናወነ ያለው የማፍረስ ተግባር በጥንቃቄ ነው እየተከናወነ ያለው፡፡ ቅድሚያ ህገወጦቹ ንብረታቸውን እንዲያነሱ ነው እድል የምንሰጣቸው፡፡ የሚመለከተውን ህብረተሰብ ሳናማክር የተከናወነ ፈረሳ እንደሌለም ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡”

ኦፌኮ ባስቀመጠው የመፍትሄ አቅጣጫም፤ የሸገር ከተማ አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልል መንግስት የግል ቤቶችንና የእምነት ተቋማት ቤቶች የማፍረሱን ተግባርን በአፋጣኝ አቁሞ በህጋዊነቱና አተገባበሩ  ዙሪያ እየተስተዋሉ ያሉ ክፍተቶችን እንደገና እንዲፈትሽ ጠይቋል፡፡ ሁኔታዎች ሳይወሳሰቡና የባሰ አደጋ ሳያስከትሉ ከህዝቡና የሃይማኖት ተቋማት ኃላፊዎች ጋርም ብወያይ ብሏል። ከተማ አስተዳደሩ የህዝቡን የመኖሪያ ቤት የማግኘት መብትና የሃይማኖት ተቋማትን የማደራጀት መብት ባገናዘበ መልኩ ፍትሃዊነትን እንዲሰፍንም ጠይቋል። በአንዋር መስጂድ የተደረገውን ተቃውሞ ተከትሎ የተፈፀመው ግድያን በተመለከተም የፀጥታ ኃይሎች ተመጣጣን እርምጃ ወስደው እንደሆነ በገለልተኛ አካል ተጣርቶ መንግስት ለህግ እንዲያቀርባቸውና ስለሁኔታው ለህዝቡ ግልፅ ማብራሪያ እንዲሰጥም ተጠይቋል። ህዝቡም ከፋፋይ ለተባለ ፕሮፓጋንዳ ሳይጋለጥ ተከባብሮ አንድነቱን እንዲያጠናክር በመግለጫው ተጠይቋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ)ም ትናንት ባወጣው መግለጫ በሸገር ከ19 በላይ መስጊዶች መፈረሳቸውን ከኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት መረዳቱን አሳውቆ፤

በግንቦት 18 ቀን፣ 2015 ዓ.ም በአንዋር መስጊድ ተቃውሞ ባሰሙ ሙስሊሞች ላይ “የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የፈጸሙ“ የመንግስት የጸጥታ አካላት መንግስት ተገቢውን ማጣራት በማድረግ በሕግ ተጠያቂ እንዲያደርግ ሲል አሳስቧል።

ሥዩም ጌቱ
እሸቴ በቀለ 
ማንተጋፍቶት ስለሺ