1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሰላም እና የሲቪክ ድርጅቶች አስተዋጽዖ

ማክሰኞ፣ ጥር 14 2016

ኢትዮጵያ ውስጥ ጠባብ የፖለቲካ ምህዳር ቢኖርም ዘላቂ ሰላምን ፣ ተስማምቶ መኖርን እና አብሮነትን ለማጠናከር እና በሰላም ግንባታ ላይ ለመሥራት መቋቋሙን ስርየት ለሁሉም የተባለ ሲቪክ ድርጅት ገለፀ። ሲቪክ ድርጅቱ በማህበረሰብ ውይይት ፣ በትምህርት እና በምርምር ነፃ እና ገለልተኛ ሆኖ ለማገዝ እንደሚንቀሳቀስ ገልጿል።

https://p.dw.com/p/4baa2
አዲስ አበባ ከተማ
አዲስ አበባ ከተማ ምስል Seyoum Getu/DW

ስርየት የተባለው ሀገር በቀል የሲቪክ ድርጅት ኢትዮጵያ "የሰላም እጦት ችግር ያለባት ሀገር" መሆኗ በሰላም መሻት ላይ እንዲሰሩ መነሻ እንደሆነዉ ይገልፃል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ጠባብ የፖለቲካ ምህዳር ቢኖርም ዘላቂ ሰላምን ፣ ተስማምቶ መኖርን እና አብሮነትን ለማጠናከር እና በሰላም ግንባታ ላይ ለመሥራት መቋቋሙን ስርየት ለሁሉም የተባለ ሲቪክ ድርጅት ገለፀ። በማህበረሰብ ውይይት ፣ በትምህርት እና በምርምር ነፃ እና ገለልተኛ ሆኖ ለማገዝ እንደሚንቀሳቀስ የገለፀው ይሄው ድርጅት ያም ሆኖ ግን የሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር መጥበብ ፈተና ሊሆንበት እንደሚችል ገልጿል።

በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ የሰላም ሚኒስትር የወሰን፣ የማንነት፣ የራስ አስተዳደር፣ ፍትኃዊ የሀብት እና የሥልጣን ክፍፍል ጥያቄዎች ኢትዮጵያን ቀውስ ውስጥ ያስገቡ መሆናቸውን ገልፀው፣ በተለይም "ከተፈጠረው ለውጥ" ጋር ተያይዘው የመጡ፣ "ከፖለቲካ ባሕል ችግር የሚነሱ እና ከታሪክ እና ትርክርት የሚመነጩ" ያሏቸው ችግሮች" ኢትዮጵያን ሰላም እንዳሳጡ ገልፀው ነበር። 

በሰላም ላይ የሚሠሩ ተቋማት ጥረት

ስርየት ለሁሉም የተባለውና ከተመሠረተ ስድስት ወራት ሆኖታል የተባለው ሀገር በቀል የሲቪክ ድርጅት ኢትዮጵያ "የሰላም እጦት ችግር ያለባት ሀገር" መሆኗ በሰላም መሻት ላይ እንዲሰሩ መነሻ እንደሆናቸው የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ክንዳለም ዳምጤ ( ዶ/ር ) ተናግረዋል።

በሀገሪቱ የሠላም ፣ የፍትሕ እንዲሁም የልማት ጉዳዮች ያገባናል ባዮች መመሥረቱ የተነገረለት ይህ ተቋም ውይይት እና ትምህርትን የሰላም ሥራ ስልቶቹ እንደሆኑ ዛሬ አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ስለ ሰላም የሚወተውቱ፣ የሚሰብኩ ተቋማት ብዙ ናቸው። በሀገሪቱ አሁንም ከመንግሥት ጋር የትጥቅ ግጭት ውስጥ የገቡ ታጣቂ ኃይሎች አሉ። መንግሥት ጉዳዩ "በሠላማዊ ድርድር እና ውይይት መፈታት አለበት" የሚል አቋም አሁንም መኖሩን የሰላም ሚኒስትሩ ተናገሩት በቅርቡ ነው። የፌዴራል መንግሥቱ በተለይ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ያለውን የትጥቅ ግጭት ለምን ማስቆም እንዳልተቻለ እና ለምን ኢትዮጵያን ከእርስ በርስ ጦርነት እና ግጭት ማውጣት አልተቻለም በሚል ለሰላም ሚኒስቴር ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከሳምንታት በፊት ጥያቄ ቀርቦ ነበር።

የአዲስ አበባ ከተማከፊል ገጽታ
የአዲስ አበባ ከተማከፊል ገጽታምስል Seyoum Getu/DW

ይህ ነባራዊ ሁኔታ ባለበት ሰላም ለማምጣት ከሌሎች መሰል ተቋማት ምን የተለየ ተጨባጭ መፍትሔ ይዘው እንደሆን ዶክተር ክንዳለምን ጠይቀናቸዋል። ገለልተኛ እና ነፃ ሆነው የሚሠሩ መሆኑን ለዚህ ምላሽ ሰጥተዋል።

የሰላም መታጣት ችግሮች ምንድን ናቸው?

የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በቅርቡ በሰጡት ማብራሪያ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት "ኢትዮጵያን ቀውስ እና ብጥብጥ ውስጥ አስገብቷታል" ብለው ነበር።
በዚህ ሁሉ መሃል ሰላምን ለመገንባት በሚል የተቋቋመው ስርየት ለሁሉም የተባለው ድርጅት ምን ችግር ሊገጥማቸው እንደሚችል ትንትነው እንደሆን ተጠይቆ የፖለቲካ ምህዳር መጥበብ ችግርን ጠቅሰዋል። የሰላም ሚኒስቴር የወሰን፣ የማንነት፣ የራስ አስተዳደር፣ ፍትኃዊ የሀብት እና የሥልጣን ክፍፍል ጥያቄዎች ኢትዮጵያን ቀውስ ውስጥ ያስገቡ ጉዳዮች መሆናቸውን ለይቷል።

 

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ 

ነጋሽ መሐመድ