1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

”ሰላም ኢትዮጵያ” የአፍሪቃ ሃገራት ለኪነጥበብ እንዲበጅቱ ጠየቀ

ሐሙስ፣ ሰኔ 1 2015

አፍሪቃ በተለያዩ ባህሎች ዘርፍ ግዙፍ እና እምቅ ኃብት ያላት ግን እስካሁን እንብዛም ያልተጠቀመችበት እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ። ከአፍሪቃ ህብረት ጋር የጀመርነዉ ፕሮጀክት አዲስ የሚያደርገዉ የአፍሪቃ ሃገራት ከብሔራዊ ገቢያቸዉ 1% ን የኪነጥበብ እንዲያዉሉ መጠየቁ ነዉ። ህብረቱም አፍሪቃዉያቱ ሃገራት ይህን እንዲያደርጉ ወስኗል።

https://p.dw.com/p/4SKQA
Selam Ethiopia | gemeinnützige Organisation
”ሰላም ኢትዮጵያ” ድርጅት የአፍሪቃ ሃገራት ለኪነጥበብ እንዲበጅቱ ጠየቀምስል Selam Ethiopia

ሰላም ኢትዮጵያ የአፍሪቃ መንግሥታት ከብሔራዊ በጀታቸዉ ቢያንስ 1% ለኪነ-ጥበብ፤ ባህልና፤ ቅርስ ዘርፎች እንዲመድቡ ጠየቀ

«ብዙ የአፍሪቃ ሃገራት ተወካዮች ይህ ነገር ጥሩ ነዉ ብለዋል። ዉሳኔ ላይ ተደርሷል። ሃገራቱ እንዲተባበሩም ተጠይቋል።»

ተሾመ ወንድሙ ይባላሉ። የዛሬ 25 ዓመት ያቋቋሙት “ሰላም ኢትዮጵያ” የተባለዉ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት አዲስ አበባ ላይ ባለፈዉ ሰሞን የአፍሪቃ ህብረት 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እያከበረ በነበረበት ሰሞን  17 የአፍሪቃ አገራት ተወካዮችን፤ አዲስ አበባ ላይ በማሰባሰብ፤ የአፍሪቃ መንግሥታት ከብሔራዊ በጀታቸዉ ቢያንስ 1% ለኪነ-ጥበብ፤ ባህልና፤ ቅርስ ዘርፎች እንዲመድቡ የማግባብያ እና የግንዛቤ መፍጠር ስብሰባና ዝግጅት አካሂዷል።

Selam Ethiopia | gemeinnützige Organisation | Teshome Wendemu
ተሾመ ወንድሙ፤ የ ”ሰላም ኢትዮጵያ” ድርጅት መስራች እና ዋና ዳሬክተርምስል Selam Ethiopia

በስዊድን መንግሥት የሚደገፈዉ እና በሰላም ኢትዮጵያ የሚመራዉ «Connect for Culture Afica» የተባለዉ እንቅስቃሴ ወይም ፕሮጀክት፤ በቀጠናዊ እና ብሔራዊ ደረጃ ያሉ የቅስቀሳ ጥረቶችን፤ የባህል ተሟጋቾችን፤ በርካታ  ባለድርሻ አካላትን በሚደግፉ ቀጠናዊ ትስስሮች አማካኝነት በጋራ የሚያጣምር ነዉ። ፕሮጀክቱ ዶሞክራሲን፤ አካታችነትን፤ ሰላም እና ዘላቂ የሆነ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማምጣት ባህል ላይ መዋዕለ ንዋይን ማዋል እንደሚያስፈልግ ግንዛቤ ይፈጥራል ተብሏል። “ሰላም ኢትዮጵያ” የተባለዉ ድርጅት መስራች እና ዋና ዳሬክተር ተሾመ ወንድሙ፤ የሙዚቃ ባለሞያ ናቸዉ።  ሰሞኑን የአፍሪቃ ሃገራት የባህል ትስስር የሚፈጥሩበትን ፕሮጀክት አስጀምረዋል። 

«እንግዲህ ሰላም ኢትዮጵያ የተባለዉ ድርጅት ላለፉት 25 ዓመታት በኢትዮጵያ ዉስጥ እና በሌሎች አፍሪቃ ሃገራት በተለይ በባህል ጉዳዮች ላይ ሰፊ ስራን ሲሰራ የቆየ ፤ በአፍሪቃ ሃገራት ያለዉን የባህል እንቅስቃሴ ሲደግፍ የኖረ ድርጅት ነዉ። ድርጅቱ ከዚህ ሌላ በአፍሪቃ የባህል እንቅስቃሴ ሊደገፍ ይገባል የሚል እምነትም አለዉ።  «Connect for Culture Afica» የተባለዉ የሰላም ኢትዮጵያ ፤ አዲስ ፕሮጀክት የአፍሪቃ ሃገሮች የባህል ዘርፉን በበጀት እንዲደግፉና ለዘርፉ በጀት እንዲመድቡ በማሳመን እና በማግባባት፤ ከጎርጎረሳዉያኑ 2030 ዓ.ም ጀምሮ እያንዳንዱ የአፍሪቃ ሃገር ለባህል ዘርፉ ከዓመታዊ በጀቱ 1% ን እንዲመድብ የሚል አላማ ይዞ የተነሳ ነዉ። ይህን ፕሮጀክት ነዉ አሁን ያስጀመርነዉ።»    

“ሰላም ኢትዮጵያ” የዛሬ 25 ዓመት ገደማ በስዊድን ስቶክሆልም፣ ላይ በኢትዮጵያዊው የሙዚቃ ባለሙያ ተሾመ ወንድሙ፣ ሲቋቋም  አላማ አድርጎ የተነሳዉ እና የሚንቀሳቀሰዉ፣ የመላውን ዓለም ሙዚቃ፣ ባህልና እሴት ለስዊድን ማስተዋወቅ ነዉ።  በ25 ዓመት ጉዞውም የምዕራቡን ዓለም፣ የአፍሪቃንና የካሪቢያንን ሙዚቃና ባህል ለስዊድን ሲያስተዋውቅ መቆየቱ ተዘግቧል። የዓለም ታላላቅ ሙዚቀኞች ስዊድን ስቶክሆልም ውስጥ በሚገኘውና የኖቤል ሽልማት ሥነ-ስርዓት በሚካሄድበት ‹‹ኮንሰርት ሀውስ›› የተባለ ታላቅ  አዳራሽ ውስጥ በሰላም ኢትዮጵያ አማካኝነት ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡ ከሀገራችን አንጋፋ ሙዚቀኞች መካከል ደግሞ አንጋፋዋ ድምጻዊት አስቴር አወቀ፣ የኢትዮ-ጃዝ አባት ሙላቱ አስታጥቄ፣ ዝነኛው አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) እና ሌሎችም በዚህ መድረክ ሙዚቃቸውን ማቅረባቸውን ነው የተገለፀዉ፡፡ ሰላም ኢትዮጵያ ከዚህ በተጨማሪም፣ ‹‹ሙዚቃዊ›› የተሰኘ የሙዚቃ አሳታሚ ድርጅት  ከፍቶ የተለያዩ ወጣትና አንጋፋ አርቲስቶችን የሙዚቃ ሥራዎች እያሳተመ ይገኛል፡፡  አቶ ተሾመ ባለፈዉ ሰሞን ከአፍሪቃ ሃገራት የባህል ጉዳይ ምሁራን እና ተማሪዎች ጋር ያስጀመሩት ፕሮጀክት ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን መላ አፍሪቃን የሚያጠቃልል ነዉ። 

Selam Ethiopia | gemeinnützige Organisation
”ሰላም ኢትዮጵያ” ድርጅት የአፍሪቃ ሃገራት ለኪነጥበብ እንዲበጅቱ ጠየቀምስል Selam Ethiopia

«ይህ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን መላ አፍሪቃ ሃገራት ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ ነዉ። አፍሪቃ ዉስጥ የባህል ዘርፉ ቅድምያ ያልተሰጠዉ ዘርፍ ነዉ። በሌላ በኩል አፍሪቃ ዉስጥ የባህል ዘርፉ ግዙፍ እና ትልቅ ገቢ ማስገኛ ነዉ ብለን እናምናለን። ስለዚህም ዘርፉ በኢኮኖሚ ከተደገፈ የተለያዩ ማሰልጠኛ ማዕከሎች ከተከፈተለት፤ ሰፊ የስራ እድል የሚ,ጥር፤ ለሃገሪቱም ከፍተኛ የገንዘብ ማግኛ ምንጭ ይሆናል ብለን እናምናለን። በአንድ ሃገር ዉስጥ የህክምና፤ የመከላከያ ፤ ብሎም የንግድ ዘርፉ በኢኮኖሚ ድጋፍ እንደሚደረግለት ሁሉ፤ የባህል ዘርፉም ድጋን ሊያገኝ ይገባል የሚል እምነት አለን። መንግሥት የባህል ዘርፉን ለመርዳት ገንዘብ ፈቃድ ሲሰጥ፤ የተለያዩ የማሰልጠኛ ናዕከሎች፤ የፊልም እና የትያትር አዳራሾች፤ የሙዚቃ ማሳተምያ ማዕከሎች መክፈትና ብሎም ሰፊ የስራ እድሎችን መፍጠር ይቻላል።    »

ሰላም ኢትዮጵያ ፕሮጀክት የክልል ፕሮግራም ስራ አስኪያጅ ኬንያዊትዋ ሉሲ ኢላዶ እንደምትለዉ ድርጅቱ ሁለት ክልላዊ ፕሮጀክቶችን ጀምሯል። የኪነጥበብ ባለሞያዎችን የሚያገናኝ መድረክ የመጀመርያዉ ነዉ።

«አሁን በአህጉሪቱ ላይ ተግባራዊ የምናደርጋቸው ሁለት ክልላዊ ፕሮጀክቶች አሉን። የመጀመርያው የፓን አፍሪቃ ኔትወርክ ለኪነ-ጥበብ ነፃነት የሚባል ሲሆን  የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችና ሌሎች በባህል ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎችን በማገናኘት የበለጠ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ሥራቸውን ለማጠናከር እና ወደ ገበያ ለማቅረብ የሚሞክር ነዉ። በሌላ በኩል ህዝቡ የአርቲስቱን ስራ እንዲገዛም ለማድረግ ጥረት እናደርጋለን። እንደሚታወቀዉ በአህጉሪቱ የዴሞክራሲ ምህዳር የጠበበ ነዉ። በዚህም ምክንያት አሁን ከመቼውም ጊዜ በላይ አርቲስቶች ክህሎታቸውን ብሎም ከሌሎች አርቲስቶች ጋር የሚገናኙበትን መስመር አጠናክረዉ  እና ተጽኖአቸውን ተጠቅመው ለተሻለ፣ አስተዳደር እና ህዝቡ የተሻለ ህይወትን እንዲያገኝ  መታገል ይኖርባቸዋል።  ብዙ የኪነ-ጥበብ ሰዎች ፣ ስለ ዴሞክራሲ፣ ሰብአዊ መብቶች፣ መልካም አስተዳደር፣ እና ሌሎች ህብረተሰባዊ ጉዳዮች ላይ ዉይይት ማድረግን እንደሚፈሩ እናዉቃለን።  አብዛኛዎቹ አርቲስቶች እራሳቸውን ሳንሱር ያደርጋሉም። እኛ ይህ እንዲደረግ አንፈልግም። ስለዚህ በዚህ ኔትዎርክ ድጋፍን ያገኛሉ ብለን እናምናለን። በአሁኑ ጊዜ እየሆነ ያለው በማህበራዊ ግንዛቤ ውስጥ የሚገኝ አርቲስት እውነትን ስለሚናገር ከጥቂት ጊዜ በኋላ  ይህ ሰዉ  እስር ቤት ዉስጥ ይገኛል።  ስለዚህ እኛ የምንፈልገው ብዙም ሳይሆን የትብብር  ኔትዎርክ በጣም ስለፈላጊ መሆኑን ማሳየት ነዉ።  ከፖሊስም ሆነ ከባለስልጣናት የሚደርስን ጭካኔ በዚህ መንገድ መቀነስ እንደሚቻል አይተናል።»

የሰላም ኢትዮጵያ የክልል ፕሮግራም ስራ አስኪያጅ ኬንያዊትዋ ሉሲ ኢላዶ  የድርጅቱ ሁለተኛ ፕሮግራም ለባህል ዘርፉ የመንግሥትን የገንዘብ ድጋፍ የሚጠይቅ መሆኑን አስረድታለች።

Selam Ethiopia | gemeinnützige Organisation | Lucy Ilado
ኬንያዊትዋ ሉሲ ኢላዶ: የሰላም ኢትዮጵያ የክልል ፕሮግራም ስራ አስኪያጅምስል Privat

«ሁለተኛው ፕሮጀክት አፍሪቃን በባህል ማገናኘት የተባለዉ እና ኢትዮጵያ አዲስ አበባ ላይ  ግንቦት 17  የተጀመረዉ ስራ ነው። በአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽን ከባህል ክፍል ጋር በመተባበር ተግባራዊ በማድረግ ላይ ያለነው ፕሮጀክት ነው። የዚህ ፕሮጀክት ዋና አላማ ለበለጠ የህዝብ ድጋፍ  እና ለገንዘብ ድጋፍ ማግባባት ነው። ይህን ስል የመንግስትን የገንዘብ ድጋፍ ማለቴ ነው። የባህል ዘርፉ፣ በእርግጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ድጋፍ ይቀበላል፣ ነገር ግን አብዛኛው የገንዘብ ድጋፍ የሚገኘዉ ከአውሮጻ  እና ከአሜሪካ ነው። እርግጥ ነው መንግሥት ኃላፊነቱን ቢወስድ እና የባህል ዘርፉን ቢደግፍ ደስ ይለናል። ምክንያቱም በብዙ የአፍሪቃ አገሮች የፈጠራ ኢኮኖሚ፣ የባህልና የቅርስ ዘርፍ፤ ለእድገት አስተዋጽኦ ማድረጋቸዉን አናዉቅም። ለዚህ ተጨባጭ መረጃ የለንም።  ስለዚህ መንግስት ከአገራዊ በጀቱ ቢያንስ 1% ለባህል ዘርፉ እንዲመድብ እንጠይቃለን።»

ባህል በውስጡ ቋንቋን፣ አለባበስን፣ አኗኗር ዘይቤን፣ ፋሽንን፣ በአጠቃላይ የጥበብ ዘርፎችን፣ አስተሳሰብን፣ የሥነ ምግባር ደንቦችን፣ እምነትን፣ ተስፋን ጭምር የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ ሰላም ኢትዮጵያ ከአፍሪቃ ህብረት ባህል እና የስፖርት ክፍል ጋር በመተባበር የአፍሪቃን የባህል ዘርፍ ለማገዝ የጀመረዉ ፕሮጀክት የአፍሪቃ ድርጅት ምስረታን በማስመልከት የተጠነሰሰ እንዳልሆን አቶ ተሾመ ወንድሙ ተናግረዋል።

«ቀደም ሲል እንደተናገርኩት ሰላም በባህል ላይ መስራት ከጀመረ ወደ 25 ዓመት ሆኖታል። በተያዩ የአፍሪቃ ሃገራት የተለያዩ የባህል እንቅስቃሴዎችን የሚረዳ ፕሮጀክቶች አሉት። የገንዘብ ድጋፍን የምናገኘዉ ከስዊድን መንግሥት ነዉ። እናም ፕሮጀክቱ ከድሮ የቀጠለ እንጂ አዲስ አይደለም። ግን አሁን ይህ ከአፍሪቃ ህብረት ጋር የጀመርነዉ ፕሮጀክት አዲስ የሚያደርገዉ የአፍሪቃ ሃገራት ከብሔራዊ ገቢያቸዉ 1% ን የኪነጥበብ እንዲያዉሉ መጠየቁ ነዉ። ህብረቱም አፍሪቃዉያቱ ሃገራት ይህን እንዲያደርጉ ወስኗል። እኛም ይህ በወሪ ብቻ ሳይሆን በተግባር እንዲፈፀም ከስዊድን መንግሥት ባገኘነዉ ገንዘብ ፕሮጀክት ቀርፀን ነዉ ነገሩ ተፈፃሚነት እንዲያገኝ እንቅስቃሴን የጀመርነዉ።

አዲስ አበባ ላይ መቀመጫዉን ያደረገዉ  የሰላም ኢትዮጵያ ፤ ዳይሬክተር  ሳሙኤል ሙሉጌታ፤ እንደነገሩን ድርጅቱ ኢትዮጵያ ዉስጥ በተለያዩ ዘርፎች ሲሰራ 18 ዓመታት ገደማ ሆኖታል። ድርጅቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሙዚቃዉን ዘርፍ ለማነቃቃት ሙዚቃዊ የሚል ድርጅት አቋቁሞ ሙዚቃን እያሳተመ ነዉ ።

Selam Ethiopia | gemeinnützige Organisation
”ሰላም ኢትዮጵያ” ድርጅት የአፍሪቃ ሃገራት ለኪነጥበብ እንዲበጅቱ ጠየቀምስል Selam Ethiopia

የአፍሪቃን የባህል ዘርፍ ለማገዝ የተነሳዉ ሰላም ኢትዮጵያ የተባለዉ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት፤ አፍሪቃዉያን መንግሥታት ካላቸዉ ገቢ አንድ በመቶዉን ለባህል ዘርፉ ሰተዉ አፍሪቃ ትጠቀማለች የሚል እምነትን ሰንቀናል ያሉት የሰላም ኢትዮጵያ ድርጅት መስራች ተሾመ ወንድሙ፤ ለአፍሪቃዉያን መንግስታት የአህጉሪቱን የባህልና የኪነጥበብ ዘርፍ እንዲደግፉ ጥሪን አስተላልፈዋል። 

አፍሪቃ በተለያዩ ባህሎች ዘርፍ ግዙፍ እና እምቅ ኃብት ያላት ግን እስካሁን እንብዛም ያልተጠቀመችበት እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ። ሰላም ኢትዮጵያ የተባለዉ ድርጅት ዘንድሮ 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ካከበረዉ ከአፍሪቃ ህብረት ጋር በመሆን የጀመረዉ ፕሮጀክት በርግጥም የአፍሪቃ መንግስታት ለባህሉ ዘርፍ እጃቸዉ በጥቂቱም የሚፈታበት ይሆናል የሚል እምነት አለን።

ሰላም ኢትዮጵያ የተባለዉን መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ለሰጠን ቃለ-ምልልስ በዶቼ ቬለ ስም በማመስገን ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን!

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ