1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

“ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ምላሽ አግኝቷል” - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 30 2016

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ምላሽ አግኝቷል፤ ለዚህ አንታገልም” ሲሉ ተናገሩ። ዐቢይ ይኸን ያሉት ዛሬ በነቀምቴ ከተማ ከአራቱም የወለጋ ዞኖች ለተውጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ባደረጉት ንግግር ነው። ጠቅላይ ሚስትሩ ወደ ነቀምቴ ከመድረሳቸው አስቀድሞ በከተማ የድጋፍ ሰልፍ መደረጉ ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/4fdlk
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በነቀምቴ ስታዲየም ከአራቱም የወለጋ ዞኖች የተውጣጡ ታዳሚን በተገኙበት ባደረጉት ንግግር “ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ምላሽ አግኝቷል፤ ለዚህ አንታገልም” ሲሉ ተደምጠዋል። ምስል Fana Broadcasting Corporate S.C.

“ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ምላሽ አግኝቷል” - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ  በሠላም፣ በህዝብ አንድነት እና ኢኮኖሚ ላይ ትኩረት ባደረገው ንግግራቸው ህብረተሰቡ አንድነቱን በመጠቀም አካባቢውን ማልማት እንዳለበት ተናግረዋል።

ዛሬ በነቀምቴ በመገኘት ባሰሙት ንግግር  በሚስተዋለው የሰላም እጦት ምክንያት ወለጋ በቂ ልማት ሳያገኝ መቆየቱንም የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አህመድ ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ መፈታት እንዳለባቸውና በርካታ የኦሮሞ ህዝብ ጥቄዎችም ምላሽ ማግኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በመጀመርያም  የኦሮሞ ህዝብ ራሱን በራሱ የማተስዳደር ጥያቄውን ምላሽ ያገኘ አጀንዳ ነው ብለዋል። 

“ዛሬ ኦሮሞ በቋንቋው መጠቀም ጥያቄው አይደለም። አዲሱ ጥያቄው ቋንቋው የቴክኖሎጂ ይሁን፣ የልማት ይሁን፣ በዓለም ላይ የሚታወቅ ቋንቋ ይሁን ማለት ነው እንጂ፤ በቋንቋዬ ልጠቀም የሚለውን ጥያቄን አልፈነዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

 ግድያ፣ እገታ፣ ቤት መቃጠል እና ዘረፋ - በኦሮሚያ ክልል

“የባለቤት ጥያቄ እና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ዛሬ ኦሮሞ የለውም። በከፈለው መስዋዕትነት ይሄ ጥያቄም ተመልሰዋል። ለዚህ ጥያቄ አንታገልም” ያሉት ዐቢይ “ይሁን እንጂ ራስን በራስ ማስተዳደር በቂ ባለመሆኑ መልማት አለብን የሚል ጥያቄ አለን” ብለዋል።

“ፍትሐዊና ሐቀኛ የሆነ አገልግሎት ለህዝቡ ተደራሽ መሆን እንዳለበት” አንስተዋል። በተጨማሪም “የሀሳብ ልዩነቶችን በመነጋገር መፍታት እንዳለበትም” ጠቁመዋል፡፡ 
“አንድነት ያስፈልገናል ስንል ለልማትም የተለያዩ ሀሳቦችን ለማፍለቅ አንድነት ያስፈልገናል። አንድነት ማለት በሁሉም ነገር አንድ ቋንቋ መናገር ማለት አይደለም። የተለያዩ ሀሳቦች ሊነሱ ይችላሉ። ልዩነትን በመነጋገር የተሻለውን ሀሳብ ለይቶ መውሰድ እንጂ ለመገዳደል ሊዳርግ አይገባም” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። 

ለማ መገርሳ እና ዐቢይ አሕመድ በነቀምቴ
ዐቢይ ከቀድሞ አጋራቸው ለማ መገርሳ ጋር ከዓመታት በፊት ነቀምቴን ጎብኝተዋል። ምስል Ahmed Kassa

በነቀምቴ ስታዲዩም በነበረው ሰልፍ ላይ ከተሳተፉት መካከል ሀሳባቸውን የሰጡን የከተማው ነዋሪም “ህዝቡ ወደ ልማት መሸጋገር አለበት ሰላም መስፍን አለበት” የሚል ሀሳቦች መነሳታቸውን ተናግረዋል፡፡

 ቄሌም ወለጋ በፀጥታ ችግር የሰዎች ሕይወት እየጠፋ ነው

ዛሬ በነቀምቴ ከተማ ከአራቱም የወለጋ ዞኖች የተወጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች መገኘታቸውም ተዘግቧል። ጠቅላይ ሚስትሩ ወደ ነቀምቴ ከመድረሳቸው አስቀድሞ በከተማ የድጋፍ ሰልፍ መደረጉ ተገልጿል። ጠቅላይ ሚስቴር አብይ አህመድ ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወር ሚያዚያ 2015 ዓ.ም እንደዚሁ  በነቀምቴ ከተማ በመገኘት ህብረተሰቡን አወያይቷል። 

ነጋሳ ደሳለኝ
እሸቴ በቀለ
ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር