1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ምርጫ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል

ዓርብ፣ ሚያዝያ 18 2016

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛው ዙር ቀሪና ድጋሚ ምርጫ በሚካሄድባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች ሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም ምርጫ እንደሚካሄድ አስታወቀ። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ አፋር፣ ሶማሌና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ በሚገኙ ምርጫ ክልሎች የምርጫ ማስፈጸሚያ ጊዜ ሴለዳ ቦርዱ ይፋ አድርጓል።

https://p.dw.com/p/4fEhM
አሶሳ ከተማ
አሶሳ ከተማ ምስል Negassa Dessalegn/DW

ምርጫ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል

 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛው ዙር ቀሪና ድጋሚ ምርጫ በሚካሄድባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች ሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም ምርጫ እንደሚካሄድ አስታወቀ። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ አፋር፣ ሶማሌና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ በሚገኙ ምርጫ ክልሎች የምርጫ ማስፈጸሚያ ጊዜ ሴለዳ ቦርዱ ይፋ አድርጓል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አብዛኛው አካባቢዎች ምርጫ ሳይካሄድ የቆየ ሲሆን ዘንድሮ በሚካሄደው ምርጫ ስምንት የፖለቲካ ፓርቲዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በክልሉ ሰኔ 9 ቀን 2016 . ጠቅላላ ምርጫ ይካሄዳል

 

ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ካልተካሄደባቸው ክልሎች መካከል የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አንዱ ሲሆን በክልሉ ሁለት ዞኖች ሙሉ በመሉ ምርጫ ሳይካሄድ ቀይቷል። ምርጫ ቦርድ ባወጣው መርሀ ግብር ከሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የመራጮች ምዝገባ ይጀመራል። በክልሉ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱት ፓርቲዎች መካከል አንዱ የቦሮ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ አንዱ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ምርጫ ለማካሄድ የሚቻልበት የሰላም ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል። የፓርቲው የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ተሰማ ፓርቲው በክልሉ ውስጥ በሚገኙ ሦስት ዞኖች ውስጥ እንደሚሳተፍ ገልጸው ከዚህ ቀደም በጸጥታ ችግር ምክንያት ከሦስት ጊዜ በላይ ምርጫ በክልሉ ለማካሄድ ታቅዶ እንደነበር ጠቁመዋል። የብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የማስፈጻሚያ ዕቅድ መሠረት ከሰኞ ሚያዚያ 21 ቀን 2016 ጀምሮ የምርጫ ቅስቀሳ እንደሚጀምር ተናግረዋል።

ፎቶ ከማኅደር፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም ጠቅላላ ምርጫ እንደሚካሄድ ገልጿል። ፎቶ ከማኅደር፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምስል NEBE

ሌላው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የቤኒሻንጉል ሕዝብ ነጻነት ንቅናቄም በበኩሉ በክልሉ በአሁኑ ወቅት 90 በመቶ በሚሆኑ አካባቢዎች ምርጫ ማካሄድ እንደሚቻል ገልጸዋል። የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አብደልሰላም ሸንግል አሶሳ ዞንን ጨምሮ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ለመወዳድር ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙ አመልክተዋል። በአሶሳ ዞን በ2013 ዓ.ም በከፊል ምርጫ ተካሂዶ እንደነበር ገልጸው በአሁኑ ወቅት በሁሉም የዞኑ አካባቢዎች ሰላም በመስፈኑ የመራጮች ምርጫ ቅስቀሳ ከሰኞ ጀምሮ እንደምጀምሩ ገልጸዋል። በ2013 በተካሄደው ምርጫ በክልሉ መተከልና ካማሺ ዞን በነበረው የሰላም እጦት ምክንያት ምርጫ ሳይካሄድ መቆየቱን ጠቁመዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብልጽግና ፓርቲ፣ የጉህዴን፣ ቦዴፓ፣ ዴ.ህ.ነ.ን፣ ኢዜማ፣ እናት ፓርቲን ጨምሮ ስምንት የሚደርሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ይሳፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። በ2013 ዓ.ም በአሶሳ ዞን የተካደው ምርጫም በኮድ ስህተትና የድምጽ መስጫ ወረቀት እጥረት ምክንያት የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ መቋጡ ይታወሳል።

ነጋሳ ደሳለኝ

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ