1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሕግ እና ፍትሕኢትዮጵያ

ለባህላዊ ዳኝነት ትኩረት የሰጠው የፍትህ ተቋማት ሽግግር

ሐሙስ፣ ግንቦት 8 2016

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በአገር አቀፍ ደረጃ የተነደፈውን የፍትሕ ተቋማት ሽግግርና የፍርድ ቤቶች የለውጥ ፍኖተ-ካርታ ሥራዎች አፈጻጸምን በተለያዩ ክልሎች በመዘዋወር እየገመገሙ ይገኛሉ ፡፡ በቀጣይ ሥራዎች ላይም ውይይት መደረጉ ተገልጧል ።

https://p.dw.com/p/4fwB8
Äthiopien Flagge
ምስል AMANUEL SILESHI AFP via Getty Images

ባሕላዊ የዳኝነት ሥርዓቶችን በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በአገር አቀፍ ደረጃ የተነደፈውን የፍትሕ ተቋማት ሽግግርና የፍርድ ቤቶች የለውጥ ፍኖተ-ካርታ ሥራዎች አፈጻጸምን በተለያዩ ክልሎች በመዘዋወር እየገመገሙ ይገኛሉ ፡፡ በምክር ቤቱ የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በሲዳማ ክልል እያደረጉ ባለው ምልከታ በፍርድ ቤቶች፣ በዐቃቢያነ ሕግ እና በፖሊስ የተከናወኑ አፈጻጸሞችን ገምግመዋል ። በቀጣይ ሥራዎች ላይም ተወያይተዋል ፡፡ ስለ ውይይቱ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ እፀገነት መንግስቱ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፦  «መንግሥት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓቶችን በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ለማስገባት አቅዶ እየሠራ ይገኛል» ብለዋል፡፡

የፍትህ አገልግሎት ከፍተኛ ችግር እንዳለበት በጥናት መረጋገጡን የጠቀሱት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢዋ "  እንደ ሀገር የደረሰብንን ሥብራት በአግባቡ መጠገን ይኖርብናል ፡፡ ለዚህ ደግሞ የፍትህ ተቋማት ሽግግር  መርሃ ግብር ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ተገብቷል ፡፡ በማህበረሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ቦታና ተቀባይነት ያላቸው ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓቶችን ማጠናከርና መደገፍ አንዱ የለውጥ ፍኖተ ካርታው አካል ተደርጓል " ብለዋል ፡፡

የኦሮሚያና የሲዳማ ክልሎች እንደ ምሳሌ

እንደሀገር የተጀመረው የፍትህ ተቋማት ሽግግርና የፍርድ ቤቶች የለውጥ ፍኖተ ካርታ ሥራዎች በተለያዩ ክልሎች ተግባራዊ በመሆን ላይ እንደሚገኝ በሀዋሳው ውይይት ላይ ተጠቅሷል ፡፡  ከሽግግሩ ግቦች መካከል ኅብረተሰቡ በፍትህ ተቋማት ላይ ተሳትፎውን ማሳደግ አንዱ መሆኑን የጠቀሱት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ እፀገነት መንግስቱ " በተለይ በተለያዩ ብሄረሰቦችና ማህበረሰቦች ውስጥ የሚገኙ ባህላዊ የፍትህ ሥርዓቶችን በመጠቀም ረገድ አበረታች ጅምሮች ተስተውለዋል፡፡ ለአብነት በኦሮሚያ ክልል ባህላዊ የፍትሕ አካላት በሕግ ዕውቅና አግኝተውና ይህም በምክር ቤት ፀድቆ ወደ ሥራ ተገብቷል ፡፡ በሲዳማ ክልል ደግሞ ሕጉ በረቂቅ ደረጃ እየተዘጋጀ ይገኛል ፡፡ በቅርቡም ጸድቆ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል ፡፡ ሌሎች ክልሎችም በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛሉ” ብለዋል ፡፡

ኢትዮጵያን የማዳን መድረክ
ኢትዮጵያን የማዳን መድረክ የተባለው ስብስብ እንዲቋቋም የጠየቀው ሀገራዊ መፍትሔ አፈላላጊ ግብረ ኃይል የመጨረሻ ግብ “በሕዝብ የተመረጠ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ማቋቋም” ነው ተብሏልምስል Ben Curtis/AP Photo/picture alliance

ጥንቃቄ የሚያሻው የባህላዊ ፍትሕ  ሥርዓት  

አቶ ብርሃኑ ጋኔቦ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህርና ተመራማሪ ናቸው ፡፡ አቶ ብርሃኑ እንደሚሉት እንደኢትዮጵያ ባሉ በጠንካራ ማህበራዊ ኑሮ ላይ የተመሠረተ ማህበረሰብ ውስጥ አብዛኞቹ የክርክር ጉዳዮች በባህላዊ ሙግት የሚቋጩ መሆናቸውን ይናገራሉ ፡፡ እነኝህን የባህላዊ ዳኝነት ሥራዎች በሕግ እንዲታቀፉ መደረጉ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ነው የሕግ መምህሩ ለዶቼ ቬለ  የተናገሩት ፡፡ በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚነሱ ሁሉም ጉዳዮች በፍርድ ቤት ይታያሉ ማለት እንዳልሆነ የተናገሩት የሕግ መመህሩ " ጉዳዮች በባህላዊ መንገድ በፍርድ ቤቶች ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉትን የጊዜ ፣ የበጀት እና አላሥፈላጊ ምልልስ ያስቀራሉ ፡፡ እንዲሁም አለመግባባቶች ተባብሰው ወዳልተፈለገ ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት እዛው በመንደርና በቀበሌ ደረጃ መፍትሄ እንዲያገኙ ያስችላል " ብለዋል ፡፡ 

ይህ ማለት ሁሉም አይነት ጉዳዮች በባህላዊ መንገድ ይፈታሉ ማለት እንዳልሆነ የጠቀሱት ብርሃኑ "በዚህ ረገድ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ብለዋል ፡፡ በተለይም የሴቶች፣ የአቅም ደካሞችና በራሳቸው መብታቸውን ማስከበርና ለራሳቸው ድምፅ መሆን የማይችሉ የማህበረሰብ ክፍሎች መብታቸው አለመጣሱን ማረጋገጥ ይገባል ፡፡ ባህላዊ የፍትህ ሥርዓቱ ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለቻቸው ዓለምአቀፍ የሰብአዊ መብቶችና በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የተቀመጡ መብቶችን በማይቃረን አኳኸን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል " ብለዋል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራትዲንሳ